የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በድባጢ ወረዳ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 28 2017የአንድ ጸጥታ ሐይል እና አራት ሸማቂዎች ህይወት አልፈዋል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጢ ወረዳ በርበር በተባለ በአንድ ገጠራማ ስፍራ በሼነ ስም ይንቃቀሳሉ የተባሉ ታጣቂዎች ዛሬ በከፈቱት ተኩስ ጉዳቱ መድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡የጸጥታ ችግር አልፍ አልፍ የሚከሰትባት የድባጢ ወረዳ በርበር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ዛሬ ብዙ ቁጥር ያላቸወ ታጣቂዎች ወደ አካባቢው በመዝለቅ ተኩስ ከፍቶ እንደነበር ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደለጹት የተኩስ ልውውጡ ለሰዓታት የነበረው ሲሆን ታጣቂዎቹ በጸጥታ ሐይሎች ከአካቢው እንዲወጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በተደረጉ የተኩስ ልውውጥም አራት ታጣታቂዎች ሲገደሉ እና የአንድ ጸጥታ ሀይል ህይወት ማለፉን አብራርተዋል፡፡ በአካባቢው ከዚህ ቀደምም ታጣቂዎች ጉዳት ያደረሱ ሲሆን የጸጥታ ሐይሎች በቦታው በመመደባቸው አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡የወረዳው አስተዳደር ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ መንግስት ሸኔ ብሎ ከሚጠራቸው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አዛዥ አማካሪ መረጃ መረጃ ለማካተት ዶቼቬለ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
በርበር ከተባለው ስፍራ በተጨማሪም በጫቲ እና በቡሌን ወረዳ ውስጥ ሁለት ገጠራማ ስፍራዎች ላይ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ዛሬ መታየቱን የአካባቢው ነዋሪዎች አብራርተዋል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች እና የታጣቂዎች መበራከት ነዋሪውን ለከፍተኛ ስጋት መዳረጉን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ድርጊቶችን በአካባቢው መከሰቱን የገልጹት ነዋሪው የህብረሰተቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚሊሻ አባላት ቁጥርን በመጨመር ትኩረት እንዲደረግ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ በተለይም በገጠራማ አካባዎች ሚኖሩ የህብረሰተብ ክፍሎች ለጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውን በማሳንት ድርጊት እንዳይደጋገም ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት መፍትሄ እንዲበጅለት ጠይቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው የክልል የጸጥታ ዘርፍና የዞን አስተዳደር አካላት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ዶቼቬለ ያደረገው ጥረት ስብሰባ ላይ ነን በማለታቸው እና ሌሎች ደግሞ ስልክ ባለማንሳታቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ የድባጢ ወረዳአስተዳዳሪ አቶ መስፍን ተገኘ ጉዳዮ እየጣራ እንደሚገኝ ገልጸው በአካባቢው በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ሐይሎች ሰላም ማስፈናቸውን ገልጸዋል፡፡
በመተከል ዞን ከሶስት ዓመታት በፊት የነበሩ የሰላም ችግሮች ከታጣቂዎች ጋር በተደረጉ የሰላምም ስምምነቶችና ህግ ማስከበር ተግባራት በዞኑ ሰላም መስፈኑን ከዚህ ቀድም የክልሉ መንግስት አመልክተዋል፡፡ በክልሉ መተከል እና ካማሺ ዞን የነበሩ የታጣቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ከመንግስት ጋር የሰላምም ስምምነት ላይ የደረሱት በጥቅምት 2015 ዓ.ም ነበር፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ