የቲቢ ክትባትን ለኮቪድ-19 ?
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 28 2012የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በዓለም ላይ በርካታ ተመራማሪዎች ለበሽታው ክትባትና መድሃኒት ለማግኘት ምርምር በማድረግ ላይ ናቸው። እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት እስካሁን በመላው ዓለም 102 የክትባት ምርምር ሥራዎች አሉ። የጀርመን የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ማኅበር ደግሞ ቁጥሩን 115 ያደርሰዋል። ከሰሞኑም የጀርመን ተመራማሪዎችም ቲቢን ለመከላከል የተቀመመ አንድ አዲስ ክትባት ኮቪድ-19ን ለመከላከል ይረዳል እንደሁ ምርምር በማድረግ ላይ ናቸው። በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ VPM1002 ተብሎ የሚጠራው ይህ አዲስ ክትባት የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር ይረዳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል ሲሉ ጀርመናዊው ተመራማሪ ፕሮፌሰር እሽቴፋን ካውፍማን ይገልፃሉ።
«በመጀመሪያ ደረጃ በእርግጥ ያሰብነው የቲቢ በሽታን የሚከላከል ክትባት ማግኘትና በሰው ላይ ሙከራ ማድረግ ነው። ነገር ግን ክትባቱ በአጠቃላይ የበሽታ መከላከላከያ አቅምን በማጠናከር ሌሎች በሽታዎችን መከላከል እንደሚችል በዝርዝር ማረጋገጥም ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሁላችንን የሚያጣድፈን ነገር የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ማግኘት ነው»።
ቲቢን በመከላከል ረገድ Bacille Calmette-Guérin (BCG) በምህፃሩ (ቢሲጂ) ተብሎ የሚጠራው ክትባት ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ጥቅም ላይ ውሎ ቆይቷል። የቢሲጂ ክትባት በተለይ ቲቢ በሽታ ባለበት አካባቢ ላሉ ሕፃናት በጣም አስፈላጊ ሲሆን፤ በሽታውን ለመከላከል ብቸኛውና ተቀባይነት ያለው ክትባትም ነው። እስከአሁን ድረስም በዓለም ላይ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሆነ የክትባት መጠን ጥቅም ላይ ውሏል።
አዲሱና VPM1002 ተብሎ የሚጠራው ክትባትም በዚህ ነባር ክትባት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተመራማሪው ያስረዳሉ።
«ዋናው ነገር ክትትል በተደረገባቸው ጥናቶች ቢሲጂ በእርግጥ በተሐዋሲ የሚመጡ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን መከላከል እንደሚችል ታይቷል። በዚህም መሠረት የአዲሱ ክትባት ይዘት በቢሲጂ ላይ የተመረኮዘ ሆኖ ይሰራል። እናም ይህ ክትባት በተሐዋሲ አማካኝነት የሚመጡ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል አቅም ማነቃቃትና ማጠናከር ይችላል።»
በጀርመን ሀገር ማክስ ፕላንክ በተባለው የተላላፊ በሽታዎችና የሥነ-ህይወት ምርምር ተቋም የሚገኙ የሳይንስ ሊቃውንት ቢሲጂን በዘረ-መል ለውጥ በማሻሻል ክትባቱን አዳብረውታል፡፡ በሰው ላይ የሚደረገውን ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ካጠናቀቀ ፣ ይህ ክትባት በቀጣይ ዓመታት በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የሚቀጥፈው ቲቢም ይሁን፤ የኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል ይውላል።
የተላላፊ በሽታዎችና የሥነ-ህይወት ተመራማሪው ሽቴፋን ካውፍማን በክትባቱ አማካኝነት መሠረታዊ የሰውነት የመከላከል አቅምን በማጎልበት ቲቢን ለመከላከል ይፈልጋሉ። እንደ ተመራማሪው አንድ ክትባት በሁለት አይነት መንገድ የሰውነት መከላከያዎችን ያነቃቃል። አንደኛው በሽታ አምጪ ተዋህሲያንን በፍጥነት ሊገድል የሚችል በተፈጥሮ የሚገኝ ልዩ የበሽታ መከላከያ ሲሆን ሌላው ደግሞ ከሌላ ወገን የተሰጠ ልዩ የበሽታ መከላከያ ነው። በእነዚህ ሁለት የበሽታ መከላከያዎች መካከል ያለው መስተጋብርም የሰውነትን የመከላከል አቅም የተሻለ እንዲሆን ያስችላል። ተመራማሪው በዚህ ላይ ተመስርተው ፤ ክትባቱ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ያለውን ውጤታማነት በማጥናት ላይ ናቸው።
« የተላፊ በሽታዎች ጥናት እንደያሳየው የቢሲጂ ክትባት ከህፃናት ሞትና ህመም መቀነስ ጋር ይያያዛል። ነገር ግን ቤሲጂ ሌሎች በሽታዎችን መከላከል ስለመቻሉ በቀጥታ የሚያያዝ ነገር አይደለም። ነገር ግን በጥናቶቻችን ያገኘናቸው ቢሲጄ የኮቪድ-19 በሽታን መከላከል ስለመቻሉ መላ ምቶች አሉ። በመጨረሻም በምርምር ማረጋግጥ ፈለግን የተገኘው ውጤትም አጥጋቢ ነው። »
ይህ የመከላከያ ክትባትም በአይጦች ላይ የተሞከረ ሲሆን ፤ የበሽታ መከላከያ ስርዓትን በማነቃቃት እንደ ኮቪድ-19 ያሉ በተሐዋሲ አማካኝነት የሚከሰቱ በሽታዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንሰ እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል።
ፓውል ኤርሊሽ የተባለው የምርምር ተቋምም VPM1002 የተባለውን ክትባት ሦስተኛ ዙር ሙከራውን በሰው ላይ አድርጓል። የሃኖቨር ከፍተኛ የሕክምና ትምህርት ቤትን ጨምሮ በጀርመን ሀገር በሚገኙ የተለያዩ ክሊኒኮችም በዚህ ክትባት ላይ ተመሳሳይ ሙከራ አድርገዋል።
ፕሮፌሰር ክሪስቶፍ ሽንድለር የሚመሩት የጥናት ቡድንም አዲሱ የቲቢ ክትባት በግንቦት ወር መጀመሪያ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓት በተለዬ ሁኔታ የሚያነቃቃ ስለመሆኑ ሙከራ ያደርጋል ። ይህም ክትባቱ እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ከባድ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን መከላከል እንደሚችል በደንብ ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ያኮብ ቦሽ የተባሉ የምርምር ቡድኑ አባል ገልፀዋል።
በመጀመሪው ሀገር አቀፍ ጥናትም በተለዬ ሁኔታ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ 1000 ሰዎች በጥናቱ ተሳትፈዋል።
በሁለተኛው ሀገር አቀፍ ጥናት ደግሞ ዕድሜያቸው ከ 60 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች የተሻሻለውን የቲቢ ክትባት VPM1002 በመስጠት ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ መታቀዱን የጥናቱ መሪ ፕሮፌሰር ሽንድለር ገልጸዋል። በዚህ ጥናትም ከመላው ጀርመን ሁለት ሺህ ሰዎች ይሳተፋሉ ።
ምርምሩ የተሳካ ከሆነም ፣ እንደ ፕሮፌሰር ካዉፍማን VPM1002 በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ መጠን ሊመረት ስለሚችል ውጤታማ የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት እስኪገኝ ድረስ መሸጋገሪያ ሊሆን ይችላል ። የቲቢ መከላከያ ክትባት እጥረትንም ይፈታል ይላሉ።
«እኛ በሚሊዮን ስለሚቆጠሩ ክትባቶች እየተናገርን አይደለም ፣ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአስር እስከ መቶ ሚሊዮን የክትባት መጠን ነው። ያ በጣም አስፈላጊ ነው።ይህ የቲቢ ክትባት ቢሲጂ በጣም አነስተኛ በመሆኑ ለኮቪድ-19 በሽታ ጥቅም ላይ ከዋለ የዓለም ጤና ድርጅት በአሁኑ ጊዜ የቲቢ በሽታ ባለባቸው ሃገራት የሚገኙ ህፃናት ክትባት ላያገኙ ይችላሉ የሚል ስጋት አለው።» ይላሉ ፕሮፌሰር ሽቴፋን ካውፍማን።
አዲሱን VPM1002 ክትባት እንዲያመርትም በዓለም ላይ ትልቁ የበሽታ መከላከያ አምራች ለሆነው፤ የህንድ የሲረም አምራች ተቋም ፈቃድ ተሰጥቶታል። ተቋሙም የምርት ሥራውን ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል።
ነባሩ የቢሲጂ የቲቢ ክትባት ቀደም ሲል በምሥራቃዊ የጀርመን ግዛቶችና በምሥራቅ አውሮጳ ሃገራት ክትባቱ ለህፃናት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን አሁንም ድረስ በዋናነት በአፍሪካ እና በእስያ የቲቢ በሽታን ለመከላከል ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ይህ ክትባት ግዴታ በሆነባቸው ሃገራት በኮሮና ወረርሽኝ የመያዝ ዕድል ምን ያህል ነው? የሚለውንም ተመራማሪዎቹ በማጤን ላይ ናቸው።
«የ ኮቪድ-19 በሽታ በከፍተኛ ደረጃ ባየለበት ወቅት አንዳንድ ተመራማሪዎች የቢሲጂ ክትባት ግዴታ በሆነባቸው ሃገራት ውስጥ የኮቪድ አደጋዎች ዝቅተኛ መሆናቸውን፣ የቢሲጂ ክትባት ከሌለቸው አገሮች የበሽታው የመከሰት አጋጣሚ ያነሰ መሆኑን በቀጥታ ተመልክተዋል። በእርግጥም ጉዳዩ እዉነትነት ያለዉና ተያያዥነት ያለው ይመስላል።» ይላሉ ካውፍማን።
እነዚህን ምልከታዎች በመተርጎም ረገድ ግን ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ካውፍማን ያስረዳሉ።
«ሆኖም እነዚህን ምልከታዎች በማጠቃለል ረገድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ጥናቶች የተካሄዱት በብዙ መንገድና ሁኔታ በሚለያዩ አገሮች መካከል ነው። ስለዚህ የግዴታ የቢሲጂ ክትባት መኖሩን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም ። ነገር ግን ያንን ለመፈተሽ የሚያበረታታ ነው። እኛም አሁን ያንን ማድረግ እንፈልጋለን።»
ምንም እንኳን በአዲሱ ክትባት ላይ እስካሁን የተደረገው የምርምር ውጤት አዎንታዊ ቢሆንም ፣እንደ ፕሮፌሰር ካዉፍማን ምርምሩን መቀጠል ያስፈልጋል። የሃኖቨር የህክምና ተመራማሪዎችም ይህ አዲስ የቲቢ ክትባት VMP1002 ተስፋ ሰጪ ነው ብለው ያምናሉ። ለዚያ ግን ክትባቱ በሰውነት ውስጥ የበሽታ መከላከያ ምላሽን ለማሻሻል እና የኮቪድ-19ን በሽታ ለመከላከል ውጤታማ ስለመሆኑ የመጨረሻውን በሰዎች ላይ የሚደረግ ሙከራና የጥናት ውጤት መጠበቅ ያስፈልጋል። እናም ይላሉ ሽቴፋን ካውፍማን ምርምሩ በጀርመን ወይም በሕንድ ብቻ ሳይወሰን ልክ እንደ ተሐዋሲው ስርጭት በመላው ዓለም መቀጠል አለበት።
ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ