የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት USAID ልኡካን የትግራይ ጉብኝት
ሐሙስ፣ ነሐሴ 25 2015በትግራይ ያለውን ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ለማቃለል የተባበሩት መንግስት ድርጅትን ጨምሮ ሁሉም ዓለምአቀፍ እርዳታ አቅራቢ ተቋማት አፋጣኝ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ። ትላንትና ዛሬ በመቐለ ተገኝተው ጉብኝት ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲሁም የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት USAID ልኡካን በትግራይ ያለው የከፋ ያሉትን ሰብአዊ ቀውስ ለማቃለል እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በ2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት፥ በትግራይ ካደረሰው ውድመት በተጨማሪ፥ ጦርነቱ ከቆመ በኃላም ቢሆን ያላበቃ ከባድ ሰብአዊና ማሕበራዊ ቀውስ አስከትሏል። እንደ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር እና ሌሎች ግብረሰናይ ድርጅቶች መረጃ ከአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ 90 በመቶ የሚሆን እርዳታ ፈላጊ ሲሆን፣ 1 ሚልዮን ገደማ የሚሆን በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬው የተፈናቀለ ህዝብ ደግሞ ከጦርነቱ መቆም አስር ወራት በኃላም ቢሆን ወደቦታው እንዳልተመለሰ ይገለፃል። በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ለመታዘብ፣ የተቋረጠው የምግብ እርዳታ አቅርቦት ለማስቀጠል የሚረዳ የተባለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲሁም የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት USAID ልኡካን ከትላንት ጀምሮ በተለያየ ቡድን በትግራይ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ።በትግራይ ክልል የእርዳታ ስርቆትና የእርዳታ መቋረጥ ስጋት
በትግራይ በጦርነት የወደመውን ሀብት መልሶ ለመመለስ እንዲሁም ድጋፍ ፈላጊዎች መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በተባበሩት መንግስትታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበርያ ተቋም ልኡካን የገለፁት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በምግብ እርዳታ አቅርቦት ላይ የተጣለ እገዳ እንዲነሳም ከዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑ ገልፀዋል። "በሚልዮኖች የሚቆጠር ህዝብ፣ ከአጠቃላይ ህዝቡ ወደ 90 በመቶ የሚጠጋ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ነው። ለዚህ የሚሆን የምግብ እርዳታ አቅርቦት ከተቋረጠ ደግሞ ስድስት ወራት አልፈዋል። ይህ መቀየር ያስፈልጋል። ይህ ለማድረግ ደግሞ ከተለያዩ የተባበሩት መንግስት ድርጅት ተቋማት እንዲሁም USAID ጋር የምግብ እርዳታ አቅርቦት እገዳው እንዲነሳ እየሰራን ነው" አቶ ጌታቸው ብለዋል።አቶ ጌታቸው ረዳ ከተባበሩት መንግስት ድርጅት ከፍተኛ ልኡካን ጋር በነበራቸው ውይይት እንዳነሱት ከጦርነቱ መቆም በኃላም ቢሆን በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬአቸው አለመመለሳቸው፥ በተፈናቃዩ ህዝብ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ የተወሳሰበ ማሕበራዊ ቀውስ ፈጥሮ እንዳለ አንስተዋል። አቶ ጌታቸው "በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ተኹኖም ቢሆን ትምህርት እንዲጀመር አድርገናል።ትግራይ፤ የተቋረጠዉ የምግብ እርዳታ እንዲቀጠል ተጠየቀ
ትምህርት መጀመር የመደበኛ ሕይወት ወይም ሁኔታ ማሳያ ስለሆነ ነው፥ እንዲጀመር ያደረግነው። ይሁንና በርካታ የትግራይ ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መጠልያ ሆነው ስላለ ፈታኝ ሆኖብናል" ብለዋል። ልኡኩ የመሩት በተባበሩት መንግስትታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበርያ ተቋም ኦቻ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ራማዝ አላክ ባሮዝ በበኩላቸው በትግራይ ላለው የተወሳሰበ ማሕበራዊ ቀውስ መፍትሔ ሊሆን የሚችል የተፈናቀሉት ወደቦታቸው መመለስ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል። "ዘላቂ መፍትሔው ሊሆን የሚችለው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬአቸው የሚመለሱበት ሁኔታ መፍጠር እና አምራች እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ይህ ከተደረገ ከጤና ስርዓት ፣ ከትምህርት እና ሌሎች አስፈላጊዎች ጋር በተገቢው ማገናኘት የሚቻል ዕድል አለ። የተልእኳችን ዓላማም ይህ ነው" ብለዋል።የተባበሩት መንግስት ልኡኩ ትላንት በመቐለ ሰብዓካሬ የተፈናቃዮች መጠልያ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን፣ ተፈናቃዮቹ አፋጣኝ እርዳታ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በመወከል ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልኡኩ ጋር የተገኘት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራር ተመስገን ተሻለ በበኩላቸው ከውጭ ድጋፍ በተጨማሪ ሰብአዊ ቀውሱ ለማቃለል የኢትዮጵያ መንግሰት ይሰራል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካው ዓለምአቀፍ እድገት ኤጀንሲ USAID የኢትዮጵያ አዲሱ ዳይሬክተር ስኮት ሄክላንድ ዛሬ በመቐለ ተገኝተው በሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ጉዳዮች ከግዚያዊ አስተዳደር እና ሌሎች ጋር መነጋገራቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ