የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ የተጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ለዓመት አራዘመ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 23 2017የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ የተጣለውን የጦር መሣሪያ ግዢ ማዕቀብ ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዘመ። የርስ በርስ ጦርነት አፋፍ ላይ ቆማለች የሚል ሥጋት ባረበበባት ደቡብ ሱዳን ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲራዘም ምክረ-ሐሳብ የቀረበው በአሜሪካ አማካኝነት ሲሆን የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያጸደቀው በጠባብ የድምጽ ልዩነት ነው።
ከ15 የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባላት መካከል ትላንት ዓርብ በነበረው ድምጽ አሰጣጥ ዘጠኙ የውሳኔ ሐሳቡን ደግፈዋል። የውሳኔ ሐሳቡ ያገኘው የድጋፍ ድምጽ ለመጽደቅ ከሚያስፈልገው ዝቅተኛው ነው። ስድስት ሀገራት ማለትም ሩሲያ፣ ቻይና፣ አልጄሪያ፣ ሴራ ሊዮን፣ ሶማሊያ እና ፓኪስታን ድምጸ ተዓቅቦ አድርገዋል።
በክራይስስ ግሩፕ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ዳንኤል አኬች የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ የጦር መሣሪያ ግዢ ማዕቀቡን ማራዘሙ በደቡብ ሱዳን ሊከሰት የሚችለውን ግጭት መጠን ለመቀነስ የሚያግዝ ጠቃሚ እርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል።
ማዕቀቡ የተራዘመው በመላ ሀገሪቱ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት ላየለባት ለደቡብ ሱዳን ወሳኝ በሆነ ጊዜ እንደሆነ የገለጹት ተንታኙ የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት ታማኝ ኃይሎች እና የምክትል ፕሬዝደንት ሪየክ ማቻር ተከታዮች የጦር መሣሪያ ፍለጋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በደቡብ ሱዳን ላይ የተጣለው የጦር መሣሪያ ግዢ ማዕቀብ፣ የባለ ሥልጣናት የጉዞ ዕገዳ እና ሀብት የማንቀሳቀስ ክልከላ ለአንድ ዓመት የተራዘመ ሲሆን እስከ ግንቦት 23 ቀን 2018 የሚቆይ ይሆናል።
ማዕቀቡ ፍጹም እንዳልሆነ የሚያምኑት ዳንኤል አኬች የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሪየክ ማቻርን በቁም እስር አውሎ በተቃዋሚዎቹ ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማጠናከር ከባድ እንደሚሆን መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ገልጸዋል።
በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዑክ ኒኮላስ ሐይሶም እየተባባሰ የመጣው የኪር እና ማቻር ባላንጣነት ወደሚመሯቸው ኃይሎች ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ማምራቱን ባለፈው ወር አስጠንቅቀው ነበር።
በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የበረታው የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት፣ ሥም ማጥፋት እና የጥላቻ ንግግር ፖለቲካዊ እና የብሔር ውጥረት ማባባሱን ኒኮላስ ሐይሶም ገልጸዋል። እነዚህ ሁኔታዎች ከ400,000 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን በጎርጎሮሳዊው ከ2013 እስከ 2016 የተካሔደ ግጭት የሚያስታውሱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
አርታዒ ልደት አበበ