የተቃዋሚዎች ወቅታዊ ውይይቶች ለኢትዮጵያ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ያመላክቱ ይሆን?
እሑድ፣ ሐምሌ 27 2017ግጭት ጦርነት እንደ አዙሪት በሚመላለሱባት ኢትዮጵያ ለፖለቲካዊ ችግሮች አሁንም ዘላቂ መፍትሔ ባለመበጀቱ ሌላ ግጭት ፣ አሁንም ሌላ ጦርነት ይቀሰቀስ ይሆን የሚለው ስጋት አይሏል። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው የሁለቱ ዓመታት ጦርነት የፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ገና አልጠገገም። ፖለቲከኞቹ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ከመነጋገር ይልቅ አሁንም የኃይል አማራጭን እየተመለከቱ መሆኑ ፖለቲካ ወለድ ቀውሱ ገና ማብቂያውጋ አለመድረሱን ያመላከተ ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሀገር ውስጥ የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ ያሉትን ጨምሮ መቀመጫቸውን በውጭ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ለኢትዮጵያ ምስቅልቅል የማህበረ ፖለቲካ እና ኤኮኖሚ ችግሮች መፍትሄ ያመላክታል ያሉትን የኦን ላይን የውይይት መድረኮች በተከታታይ እያካሄዱ ነው።
ፍጹም የፖለቲካ እና የዓለማ ልዩነት ያነገቡ እነዚሁ ቡድኖች በውይይቶቻቸው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ቀውስ ዘላቂ መፍትሄ የሚሏቸውን የተለያዩ ሃሳቦች እያቀረቡ ሲሆን በዋናነት ግን አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ካለፈ በኋላ ስለሚኖር የሽግግር ስረዓት መምከሩን ትኩረት ሰጥተዉበታል።
መሰል በፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚደረጉ ውይይቶች ለሀገሪቱ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት የአቋም እና የዓላማ ልዩነትን ወደ ጎን ትቶ ለውይይት መቀመጡ በበጎ ጎኑ የሚወስዱ እንዳሉ ሁሉ ውይይቶቹ አካታች አለመሆናቸው እና ከውይይት ባሻገር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል የሚል ትችት ሲቀርብባቸውም ይሰማል።
ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ በሀገር ውስጥ የሚገኙ እና በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳያሳትፍ የሚደረግ ንግግር እና ውይይት ምን ያህል ዉጤት ሊያመጣ ይችላል የሚል ጥያቄም ያስነሳል።
የሆነ ሆኖ በአንድ ወቅት በጠላትነት ይፈላለጉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ታጣቂ ቡድኖች በአንድ የውይይት መድረክ ተገናኝተው ሃሳባቸውን ማንሸራሸራቸው ለውይይት እና ድርድር በር ሊከፍት እና በሂደት ሁሉም ሊሳተፉ የሚችሉበት የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት መሰረት ይጥላል የሚል ተስፋ ያደረጉም ጥቂቶች አይደሉም።
ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች እያካሄዱ የሚገኙት ሀገራዊ እና ወቅታዊ ውይይቶች ለኢትዮጵያ ዘላቂ መፍትሄ ከማበጀት አንጻር ምን ሚና ይኖራቸዋል ? የዚህ ሳምንት የእንወያይ ዝግጅታችን ርዕሰ ነው።
በውይይቱ ላይ
ዶ/ር ራሔል ባፌ ፖለቲከኛ
ዶ/ር ሄኖክ ገቢሳ የህግ ባለሞያ እና የፖለቲካ ተንታኝ
ፕ/ር ጌታቸው መታፈሪያ የዓለማቀፍ ግንኙነት መምህር
አቶ አያና ፈይሳ የወቅታዊ ጉዳይ እና የፖለቲካ ተንታኝ
አወያይ ጋዜጠኛ ታምራት ዲንሳ