የቦረና ኦሮሞ አባገዳ 72ኛው የስልጣን ሽግግር
ሰኞ፣ መጋቢት 1 2017በየስምንት ዓመት ለሚካሄደው የገዳ ስርዓት ስልጣን ርክክብ ላለፉት 8 ዓመታት በስልጣን ላይ የነበሩ የቦረና አባገዳ ኩራ ጃርሶ ኩራ ለአዲሱ ተተኪ ጉዮ ቦሩ ጉዮ ትናንት የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ስልጣን ያስረከቡት በስርዓቱ ውስጥ ሚና ያላቸው የጎሳ መሪዎች እና በርካታ እንግዶች ከተለያዩ የአገሪቱ አቅጣጫ በተገኙበት ነው፡፡
ከባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን ጀምሮ እስከ ትናንት እሁድ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በተለያዩ ባህላዊ ስርዓት ስከወን የነበረው የቦረና ባሊ (ስልጣን) የማስተላለፍ ስርዓት በትናንትናው እለት የተጠናቀቀውም በደማቅ ባህላዊ ስርዓት ነው፡፡ ምስራቅ ቦረና ዞን አረሮ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው አርዳ ጅላ በዳሳ በሚባል ስርዓቱ የመፈጸሚያ ስፍራ ለቀናት የተከናወነው ስርዓቱ በትናንትናው እለት የገዳ ስርዓት ስልጣን በመረካከብ ስጠናቀቅ የቀድሞው አባገዳ ኩራ ጃርሶ በርሳቸው የስልጣን ዘመን ስለተከናወኑ እና የሚቀሩ ስላሏቸው ይህን ብለዋል፡፡
«ሰላም ማግኘት ሰላምን ይሻል፡፡ ስኬትም እንዲሁ ያለ ሰላም አይሆንም፡፡ ለዚህ ብለን ነው በሰላም ስልጣኑን እያስረከብን ያለነው፡፡ በዚህን ወቅት ከኦሮሞ ውጪ በዚህ ደረጃ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስልጣን የሚረካከብ በዓለም የለም፡፡ ባለፉት ዓመታት መንግስት በዘረጋው ስርዓት የባህላዊ ፍርድ ቤት መመስረት፣ የልጆቻችን ገዳ ስርዓትን በየትምህርት ቤቱ መማር እና የገዳ ስርዓት በዩኔስኮ መመዝገድ እንደ ትልቅ ስኬት ሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚህ በቦረዳ ኦሮሞ የገዳ ስርዓት መከወኛ ስፍራ አርዳ ጅላ በዳሳ ደግሞ በልጆቻችን ምቹ ሆኖ እንደሚለማ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እናም በርቱ የምለውን መልእክቴን በዚሁ ላስተላልፍ” በማለት አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የገዳ ሥርዓት መመዝገብ
ስልጣኑን ከበፊቱ አባገዳ ተረክበው ለሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት ቦረናን በገዳ ባህላዊ ስርዓት ለማስተዳደር 72ኛው የቦረና አባገዳ ሆነው ኃላፊነት የተቀበሉት አባገዳ ጉዮ ቦሩ ጉዮ በበኩላቸው ባህል እና አንድነት እንዲጠናከር መስራት ዋናው ትኩረታውን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “በትልቁ ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት አንድነት እንዲኖር ነው፡፡ ልማት እና ሰላም እጅጉን ተፈላጊ ጉዳዮች ሲሆኑ የሚገኙትም በአንድነት ነው፡፡ ባህላችንም እየታደሰ ከዘመኑ ጋር እየተራመደ ልጆቻችን በእውቀት እንዲያድጉልን እንሻለን” ብለዋል፡፡
አባገዳ ጉዮ ቦሩ በስልጣን ዘመናቸው የገዳ ስርዓትን ማጠናከር ቤት ስራው እንደሚሆንም ቃል ገብተዋል፡፡
ትናንት ምስራቅ ቦረና ዞን ውስጥ በቦረና አርዳ ጅላ በተከናወነው የቦረና ገዳ ስርዓት ስልጣን ሽግግር ከኢትዮጵያም ውጪ ከኬንያ ሰሜናዊ ግዛት መርሳቢት የቦረና ጎሳዎች ታዳሚ ነበሩ፡፡ የግዛቲቱ ዋና አስተዳደሪ መሃመድ በዚህ ስርዓት ላይ ተገኝተው እንደገለጹትም፤ “እኛ ከኬንያ የመጣነው አባገዳ ቦረና ስልጣን ያስተላልፋሉ፡፡ አዲሱ ስልጣኑን የሚረከቡም ተመርቀው ስልጣናቸውን ይረከባሉ መባሉን ሰምተን ነው ይህን ደስታ ለመካፈል የመጣነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ደማቅ ስርዓት የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም የኦሮሚያ ክልል መንግስት ምስጋና ይገባዋል፡፡ በናንተ ምክንያት አሁን ዓለም እያየችን ነው፡፡ ባህላችንም እየደመቀ ነው” በማለት በስርዓቱ ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡በአዲሱ የጉጂ አባገዳ የተላለፈው የሰላም ጥሪ
በትናንቱ ባህላዊውን ስልጣን የማሸጋገር ስርዓት ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም ባህል እንዲጠናቀር ነው መልእክት ያስተላለፉት፡፡ “ይህ የገዳ ስርዓት በባህል በወጉ ተደግፎ በደንብ ተይዞ ህዝባችን ከርሰበርሳችንም ሆነ ከሌላው ህዝብ፣ ከፍጡሩም ከፈጣሪም ጋር እንዴት መንኖር እንዳለብን ስርዓት አበጃጅቶ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ አሁንም የትናንቱ ማንነታችን ላይ ከቆምን ብቻ ነው ነገያችንን መገንባት የሚቻለን፡፡ ለዚህም ነው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ባህላችን ታድሶ መንገድ እንዲይዝ በትኩረት እየሰራበት የሚገኘው” በማለት ይበልጥ ባህላዊ ስርዓቱ ላይ መስራት እንደሚገባ የገለጹት፡፡ በአዲሱ የጉጂ አባገዳ የተላለፈው የሰላም ጥሪ
አስተያየታቸው ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የፍልስፍና ባለሙያ እና በተለያዩ ጊዜያት በቦረና ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብ የሚታወቁ ፕሮፈሰር ጉዮ ዶዮ፤ ከተሃድሶ በኋላ በየስምንት ዓመቱ እየተላለፈ አሁን ላይ 72ኛው ላይ የደረሰው የቦረና ገዳ ስልጣን ትውልድንም ሆነ ሴቶችን የሚያቅፍ ብለውታል፡፡ “አንደኛው መታወቅ ያለበት ይህ ስልጣን ትውልድን የሚቅፍ እንጂ የግለሰብ አይደለም፡፡ ትናንሽ ልጆች ከወዲሁ ኃላፊነት እንዲሸከሙ እና ለስልጣን እንዲዘጋጁም ሆነው ያድጋሉ፡፡ ያለ ሴቶችም የሚፈጸም ስርዓት የለም በገዳ ስርዓት ውስት” በማለት የስርዓቱን ትውልድ አቃፊነት በአስተያየታቸው ገልጸውልናል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ