የብሔራዊ ባንክ ገዥ በትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገበያ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ እንደሚወረስ አስጠነቀቁ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 30 2017የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ገዥው ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ በትይዩ ገበያ እየገሰገሰ የሚገኘውን ውጪ ምንዛሪ ተመን ለመቆጣጠር ዘመቻ ከፍተዋል። ዘመቻው በሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት አለመኖሩን ማስተማመኛ መስጠት፣ ሕገ-ወጥ በተባሉ የሐዋላ አስተላላፊዎች በኩል የሚላክ ገንዘብ እንደሚወረስ ማስጠንቀቅ እና ዶላር በጨረታ ማቅረብ የመሳሰሉ እርምጃዎችን የሚያካትት ነው
ትላንት ማክሰኞ ባካሔደው የውጪ ምንዛሪ ጨረታ ብሔራዊው ባንክ በአማካኝ አንድ ዶላር በ138 ብር ለባንኮች ሸጧል። በጨረታው 150 ሚሊዮን ዶላር ለሽያጭ ያቀረበ ሲሆን የተሳተፉ 28 ባንኮች “ሁሉም የሚፈልጉትን የውጪ ምንዛሪ እንዳገኙ” የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ተናግረዋል።
ለባንኮች የተሸጠው ዶላር ከዚህ ቀደም በተካሔዱ ጨረታዎች ከቀረበው ሦስት እጥፍ የሚልቅ መሆኑን የታዘቡት የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ባለፈው ቅዳሜ ከሰጠው ማሳሰቢያ ጋር ተደማምሮ ብሔራዊ ባንክ “እየጨመረ የመጣውን የትይዩ ገበያ የምንዛሪ ተመን ለማረጋጋት ሙከራ እያደረገ” መሆኑን እንደሚጠቁም አስረድተዋል።
“ጨረታ አሸንፈው የውጪ ምንዛሬ ያገኙ ባንኮች በጨረታ ያገኙትን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ጨምረው በሚቀጥሉት ሳምንታት ለደንበኞቻቸው በበቂ ሁኔታ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል” ሲሉ አቶ ማሞ ዛሬ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካለፈው መጋቢት አንስቶ በሁለት ሣምንት አንድ ጊዜ የውጪ ምንዛሪ በጨረታ ለባንኮች ሲሸጥ ቆይቷል። ባንኩ 50 ሚሊዮን ዶላር ለ11 ባንኮች ያከፋፈለበት ስምተኛው ጨረታ የተካሔደው ሰኔ 18 ቀን 2017 ነበር። በወቅቱ አንድ ዶላር በ136 ብር ከ60 ሣንቲም አማካኝ የጨረታ ዋጋ ተሸጧል። ስድስት ሣምንታት ገደማ ዘግይቶ በተካሔደው ጨረታ ብሔራዊ ባንክ ዶላር በጨረታ የሸጠበት ዋጋ ከትይዩው ገበያ ተመን አኳያ የ32 ብር ገደማ ልዩነት አለው።
ጨረታው ይፋ ከተደረገ በኋላ በትይዩው ገበያ ዶላርን የመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች የምንዛሪ ተመን ለውጥ አሳይቷል። በተለያዩ አካባቢዎች እስከ 174 ብር ይመነዘር የነበረው አንድ የአሜሪካ ዶላር ወደ 170 ብር ገደማ መመለሱን ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። መቀመጫቸውን በብሪታኒያ ያደረጉት ዶክተር አብዱልመናን በትይዩው ገበያ የፓውንድ ምንዛሪ በብሔራዊ ባንክ ጨረታ ምክንያት የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም “መሠረታዊ ለውጥ” እንዳልሆነ ታዝበዋል። ከጨረታው በፊት በ213 ብር ይመነዘር የነበረው ፓውንድ በሦስት ብር ገደማ ቀንሶ ወደ 209 ብር ገደማ ዝቅ ብሏል።
“ብሔራዊ ባንክ ካቀረበው ዶላር እና ባለፈው ሣምንት ካወጣው መግለጫ አኳያ [የታየው የምንዛሪ ለውጥ] ምንም ማለት አይደለም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የትይዩው ገበያ የውጪ ምንዛሪ ተመን አካሔድ ወደነበረበት ሊመለስ እንደሚችል ያምናሉ። “ባንኮች በጨረታ 150 ሚሊዮን ዶላር አግኝተዋል። ይህ ዶላር በሚፈልጉ ሰዎች ላይ የሚጨበጥ ነገር ካመጣ የምናየው ይሆናል። ነገር ግን የያዘውን አካሔድ የሚቀጥል ይመስላል” ሲሉ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ “አንድ ወጥ የተዋሀደ የውጪ ምንዛሪ ገበያ እንዲኖር” ይፈልጋል። ዕቅዱ መደበኛ እና ትይዩ ገበያዎች ተዋህደው ሊፈጠር የሚችለውን ግብይት በባንኮች የሚከወን ማድረግ ነው። የብሔራዊ ባንክ ገዥ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ግኝት እያደገ በመሆኑ ነጋዴዎችም ሆኑ የውጪ ሀገር ተጓዦች ወደ ትይዩው ገበያ ማማተር እንደማያስፈልጋቸው ማረጋገጫ ለመስጠት ሞክረዋል።
ባለፈው ዓመት ባንኮች ለንግድ ማኅበረሰቡ ያቀረቡት የውጪ ምንዛሪ በእጥፍ ጨምሮ በየወሩ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር እየሰጡ እንደሚገኙ አቶ ማሞ ተናግረዋል። ለግል ዘርፍ የሚቀርበው የውጪ ምንዛሪ “በከፍተኛ ሁኔታ” እያደገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ማሞ ብሔራዊ ባንክ “እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ የውጪ ምንዛሪ” እንደሚያቀርብ ቃል ገብተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ “የንግዱ ማህበረሰብ ለውጪ ምንዛሪ ፍላጎቶቻችሁ መደበኛውን የባንክ ሥርዓት እንድትጠቀሙ አጥብቀን እንመክራለን” ሲሉ ተደምጠዋል። “አብዛኞቹ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ይህንኑ እንደሚያደርጉ ብናውቅም አንዳንዶቹ ግን ይህን አካሔድ እየተከተሉ ባለመሆናቸው ከትይዩ ወይም ሕገ-ወጥ የውጪ ምንዛሪ ገበያዎች ይልቅ ወደ መደበኛው የባንክ ሥርዓት እንዲመለሱ አበክረን እናስገነዝባለን” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ነጋዴዎች “የውጪ ምንዛሪ ተደራሽነትን በተመለከተ በባንኮች ላይ ብዙ ቅሬታ እንዳላቸው” ያመኑት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ከባንኮች በቂ የውጪ ምንዛሪ ያላገኙ ወደ ትይዩው ገበያ እንደሚሔዱ መግለጻቸውን ተናግረዋል። አቶ ማሞ በማብራሪያቸው “እነዚህ ቅሬታዎች እና ችግሮች በአብዛኛው መፍትሔ አግኝተዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ባንኮች የውጪ ምንዛሪ ሲፈቅዱ ከኤልሲ ዋጋ በላይ በብር ተቀማጭ እንዲደረግ ይጠይቃሉ” በሚል አስመጪዎች የሚያቀርቡትን ቅሬታም “ባንኮች እንዲህ አይነት አስገዳጅ ጥያቄ እንደማያቀርቡ አረጋግጠዋል” ሲሉ አስተባብለዋል። “በዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊት የሚሳተፉ ባንኮች ካሉ ለብሔራዊ ባንክ ጥቆማ” እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ማሞ እንደሚሉት ብሔራዊው ባንክ “ወደ ትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገበያ የሚገባውን እና የሚዘዋወረውን የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚከታተልበት ጠንካራ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት” ዘርግቷል። ገዥው “በሕገ-ወጥነት በዚህ ኢ-መደበኛ ገበያ የሚጠቀሙ ወገኖች ከድርጊታቸው ካልታቀቡ በስተቀር በቅርብ ክትትል ገንዘባቸውን እስከ መውረስ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ለማስገንዘብ ይፈልጋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ብሔራዊው ባንክ በዩናይትድ ስቴትስ የሚንቀሳቀሱ አራት የሐዋላ አስተላላፊዎችን ባለፈው ቅዳሜ “በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር” ወንጅሏል። ድርጅቶቹ በውጪ ሀገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች በሚሰበሰብ ገንዘብ “ሕገ-ወጥ ተግባራትን ይደግፋሉ” የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ሸገይ፣ አዱሊስ፣ ራማዳ ፔይ (ካሕ) እና ታጅ የተባሉት የገንዘብ አስተላላፊዎችን በውጪ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት መጠቀም እንዲያቆሙ ያሳሰበው ብሔራዊ ባንክ በአሜሪካ “አግባብነት ያላቸው የህግ አስፈጻሚ አካላት ምርመራ እንዲያከናውኑ” ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል። ከአሜሪካ በተጨማሪ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች “የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ታማኝነትን ሆነ ብሎ ለመሸርሸር እና የገበያ ዋጋን ለማዛባት” ያለሙ ድርጊቶች መኖራቸውን አቶ ማሞ ገልጸዋል።
“ከቅርብ ቀናት ወዲህ በተለይ በዱባይ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ ከገበያ ሁኔታ ያፈነገጠ የትይዩ ገበያውን የሚያስፋፉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች እንዳሉ በውል ስለተረዳን ይህን ተከታትለን ጠንካራ እርምጃዎችን እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከትይዩ ገበያ ጋር ግብግብ የገጠመው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ በተደረገ በዓመቱ ነው። በውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት ለይፋ እና ትይዩ ገበያዎች የተራራቀ ተመን ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ እንደማይችል የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ይናገራሉ። የሁለቱ ገበያዎች የውጪ ምንዛሪ ተመን ልዩነት እየሰፋ የሚሔደው በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ በተንሠራፉ “የአሠራር ግድፈቶች እና ሌብነት” ምክንያት እንደሆነ ይሞግታሉ።
“በመደበኛ እና በትይዩ ገበያዎች መካከል ያለውን የምንዛሪ ተመን ልዩነት ያመጣውም፤ የገፋውም በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ያለ ቅጥ ያጣ እና መስተካከል ያልቻለ የአሠራር ጉድለት እና sepeculation ነው” የሚሉት አቶ ጌታቸው የገንዘብ ሽሽት (capital flight) ሌላው ምክንያት እንደሆነ አክለዋል።
በባንኮች የሚከወነው ይፋዊ የምንዛሪ ግብይት ሥርዓት “በገበያ ሕግ እየሠራ ነወይ?” ሲሉ የሚጠይቁት የፋይናንስ ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን በበኩላቸው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት “የገበያው አወቃቀር” አንደኛው ችግር እንደሆነ ይፋ ማድረጉን ጠቅሰዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት “በባንኮች መካከል ውድድር አለመኖር የሸቀጦች ላኪዎች እና የሐዋላ ተቀባዮችን ከመሳሰሉ የውጪ ምንዛሪ ባለቤቶች በቂ ያልሆነ የውጪ ምንዛሪ እንቅስቃሴ” እንደሚፈጥር ገልጾ ነበር።
ይህ ጉዳይ በቀጥታ በፋይናንስ ኢንደስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ከያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሚና ጋር የተያያዘ ነው። ዶክተር አብዱልመናን “በገበያ ሕግ አይመራም” ሲሉ የሚተቹት መንግሥታዊው ንግድ ባንክ በይፋዊ የውጪ ምንዛሪ ግብይት ዋጋ የመተመን ሚና አለው። ሌሎቹ ባንኮች በአንጻሩ የንግድ ባንክን አካሔድ ይከተላሉ። በዚህ ምክንያት ይፋዊ የሚባለው የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት የገበያውን ትክክለኛ ሁኔታ እንደማያሳይ ዶክተር አብዱልመናን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ባንኮች የሚያስከፍሉት “ከፍተኛ የአገልግሎት ክፍያ” እና በይፋዊው ገበያ በቂ የውጪ ምንዛሪ አለመገኘት ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑ የፋይናንስ ባለሙያው አስረድተዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሪፖርቱ “የካፒታል አካውንት ዝግ መሆን” በይፋ እና ትይዩ ገበያዎች መካከል ለሚታየው የተመን ልዩነት አስተዋጽዖ እንዳለው መጥቀሱን የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን “ነገር ግን የካፒታል አካውንት በቅርቡ ክፍት ሊሆን እንደማይችል ይታወቃል” ሲሉ ተናግረዋል።
ዶክተር አብዱልመናን በባንኮች የሚከወነው ይፋዊ የውጪ ምንዛሪ ግብይት “የገበያ ሕግን ተከትሎ የሚሔድ ቢሆን ኖሮ” ከትይዩ ገበያ ጋር ያለው ልዩነት “የተቀራረበ” ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። “ከሞላ ጎደል” እውነተኛ የገበያውን ሁኔታ የሚያንጸባርቀው የትይዩ ገበያ የምንዛሪ ተመን እንደሆነ ዶክተር አብዱልመናን ያምናሉ። የፋይናንስ ባለሙያው እንደሚሉት ሁለቱን የውጪ ምንዛሪ ተመኖች ማዋሀድ “ለመንግሥት ከባድ ፈተና ይሆናል።”
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓትን ጨምሮ “አጠቃላይ የኢትዮጵያን ማሻሻያ በእጅጉ እየነቀፈ እንደሆነ፤ ከማሻሻያው የመጀመሪያ ዓመት በኋላ የውጪ ምንዛሪ ግኝት እንደሚቀንስ” የብሔራዊ ባንክ ገዥ “ሐሰተኛ ወሬ የሚነዙ ወገኖች አሉ” ሲሉ ተደምጠዋል። የብሔራዊ ባንኩ ገዥ “አሉባልታ” ያሏቸውን ጉዳዮች “መሠረተ-ቢስ” ሲሉ አጣጥለዋል።
“ድርጅቱ ስለ ሀገራት በሚያወጣቸው ዘገባዎች ሁሉ እንደሚያደርገው ሀገራት ሊያጋጥማቸው ስለሚችለው ሥጋት አጠቃላይ አስተያየት ይሰጣል” ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ “እኛም ሆን ሌሎች ሀገራት የሚያጋጥማቸው የጂዖፖለቲካ፣ የንግድ ወዘተ ሥጋቶች መኖራቸው የታወቀ ስለሆነ በዚህ ረገድ የተሰጠው አስተያየት የተለመደ እና ለእኛ የተለየ አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።
“የዓለም የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያ ከቶውንም አልነቀፈም። በባንኮች የብር የውጪ ምንዛሪ ተመን ላይ ችግር መኖሩንም አላነሳም” የሚሉት አቶ ማሞ “በባንኮች ያለው የብር የውጪ ምንዛሪ ተመን ከኢኮኖሚያዊ መርኆዎች አንጻር በትክክለኛው ቦታ ላይ እንደሚገኝ፤ እንዲያውም የባንኮች የብር የውጪ ምንዛሪ ተመን በ4.5 በመቶ ከዋጋው በታች እንደሆነ ወይም ብር ከመውረድ ይልቅ ሊጠነክር እንደሚገባ በቴክኒካው ግምገማው አሳይቷል” ሲሉ ሞግተዋል።
“ቀጣይ የውጪ ምንዛሪ ግኝት እና የውጪ ምንዛሪ ተመንን በተመለከተ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል አንዳችም አሉታዊ ግምገማ ወይም ሥጋት የለም” ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ ባለፈው አንድ ዓመት ሥራ ላይ በቆየው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት “አተገባበር የተለየ እና አዲስ ሥጋት ሊኖር አይገባም” ሲሉ መግለጫቸውን በዐይነ ቁራኛ ለሚከታተሉ ሁሉ ማስተማመኛ ለመስጠት ሞክረዋል።
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ግን በይፋ እና ትይዩ ገበያዎች መካከል ያለውን የውጪ ምንዛሪ ተመን ልዩነት ለመቆጣጠር ብሔራዊ ባንክ በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ የሰፈኑ ችግሮችን የሚያስወግዱ “ቁርጠኛ” እርምጃዎች መውሰድ እንዳለበት ይመክራሉ። የምንዛሪ ሥርዓቱን በተጨባጭ በገበያ ሕግ እንዲመራ ማድረግም ሌላው የቤት ሥራ ነው።
አርታዒ ፀሐይ ጫኔ