የቀጠለው የጤና ባለሞያዎች ጥያቄና የጤና ሚኒስቴር ምላሽ
ዓርብ፣ ግንቦት 8 2017ሰሞኑን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፊል ያሉትን የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ላይ ያሉት የጤና ባለሞያዎች ያነሷቸው የደሞዝ፣ የጥቅማ ጥቅም እና ምቹ የሥራ ሁኔታ ጥያቄዎች ምላሽ ካላገኙ ሙሉ አድማ እንደሚያደርጉ አስጠነቀቁ ። ጥያቄያቸው ያልተገባ መልክ እየተሰጠው መሆኑን የገለፁት ባለሞያዎቹ መፍትሔው ማነጋገር እና በቂ ምላሽ መስጠት ብቻ ነው ብለዋል ። የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ፦ «ብዙዎቹ በሐሰተኛ መረጃ የተወናበዱ» ሲል በመደበኛ የሥራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ወደ ሥራ እንዲመለሱ አሳስቧል ። ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተባለው ሲቪክ ድርጅት የጤና ባለሞያዎቹ የሥራ ላይ መብቶች ጥያቄዎች «በአፋጣኝ ትኩረት እንዲሰጣቸው» ብሏል ። ኢሕአፓ እና ኦፌኮ ፓርቲዎች በበኩላቸው ጥያቄዎቹ ፍትሐዊና ሕጋዊ መሆናቸውን በመግለጽ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል ።
ከድንገተኛ፣ ከጽኑ ሕሙማን፣ ከጨቅላ ሕፃናት እና ከማዋለጃ ክፍል አገልግሎቶች በስተቀር «ከፊል» ያሉትን የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ላይ መሆናቸውን እየገለፁ ያሉት የጤና ባለሞያዎች ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ሙሉ የሥራ ማቆም ወደ ማድረግ እንደሚያመሩ እየገለፁ ነው፥ ጥያቄያቸው ካልተመለሰ። አንድ የጤና ባለሞያ እንዳሉት ይህ የሚሆን ከሆነ ግን ጉዳቱ አስከፊ ነው ።
«አንድ የህክምና ተቋም አገልግሎት አቆመ ማለት ጊዜ የማይሰጥ ሁኔታ ይኖራል ። ትንሽ ከበድ ያለ ነው»
የጤና አገልግሎት «መቼምና በምንም ሁኔታ መቋረጥ ከሌለባቸው ማኅበራዊ አገልግሎቶች አንዱ» መሆኑን ትናንት የገለፀው የጤና ሚኒስቴር «በጥቂት የማስተማሪያ የጤና ተቋማት በመደበኛ የሥራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ የተወሰኑ» ያላቸው ባለሞያዎች እንዳሉ መረዳቱን፣ ከእነዚህ መካከል «ብዙዎቹ በሐሰተኛ መረጃ የተወናበዱ ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ ጥፋትን ዓላማቸው ያደረጉ» እንደሆነም ገልጿል ። ባለሞያዎቹ እንደሚሉት ግን ጥያቄያቸው በመንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት እንዱህ መታየቱ አሳዝኗቸዋል ። «ጥያቄው ግልጽ ሆኖ ሳለ ፖለቲከኞች እዚህ ውስጥ ገብተው፣ ጠምዝዘው ሌላ ስያሜ ለማሰጠት መሞከራቸው በጣም ያሳዝናል ።»
የኢትዮጵያ የጤና ባለሞያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት መለሠ ባታ ማኅበራቸው ይህንን ንቅናቄ እየመራ አለመሆኑን ጠቅሰው የማኅበሩን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ብዙዎች እየታሠሩ፣ ማስፈራሪያም እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጿል። «በተለያዩ ሆስፒታሎች ከፊል የሥራ ማቆም አድርገዋል ። እና ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያየ የፀጥታ ኃይል ተመድቦ እያስፈራሯቸው፣ ማስታወቂያ እየተጻፈ ነው ።» የባለሞያዎቹ የቀጣይ ዕቅድ ምን እንደሆነም ጠይቀናቸው መልሰዋል ። «ባለሞያው ከሰኞ ጀምር ወደ ሙሉ ሥራ ማቆም ነው እንሄዳለን እያለ ያለው ።»
የሲቪክ እና የፖለቲካ ድርጅቶች ጥሪ
ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተባለው ሲቪክ ድርጅት የጤና ባለሞያዎቹ የሥራ ላይ መብቶች ጥያቄዎች «ሕግን መሰረት ያደረጉ እና አግባብነት ያላቸው ናቸው» ብሏል። ድርጅቱ «ባለሞያዎቹ ያነሷቸው የመብት ጥያቃዎች ተገቢነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ ሁኔታ ግን በዝቅተኛ የደሞዝ መጠን የሚሠሩ ሰራተኞችን እንዱሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ህክምና የማግኘት መብት የሚጋፋ ፣ ታካሚዎችን አደጋ ላይ የሚጥል እና ቀላል የማይባል ማህበራዊ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል እሙን ነው» ብሏል ። ሌላ የጤና ባለሞያ ውይይትን እንደ መፍትሔ አስቀምጧል ።
መንግሥት የጤና ባለሞያውን ዘላቂ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት ላይ መሆኑን ያስታወቀው የጤና ሚኒስቴር "በሥራ ገበታቸው ላይ ባልተገኙ እንዲሁም በጤና ተቋሙም ሆነ ከጤና ተቋሙ ውጭ ሆነው ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩት" ባላቸው ላይ "አስፈላጊ ሕጋዊ እርምጃ" እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ጥያቄው "ትክክለኛ የመብት ጥያቄ በመሆኑ ምላሽ ይሰጠው" ብሏል ባወጣው መግለጫ። የኤሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ "ጥያቄውን በቅንነትና በግልፅነት መመለስ እንጂ ፍረጃ፣ እሥር እና የኃይል እርምጃ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም" ሲል መሰል ርምጃዎች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ጠይቋል ።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ