የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አስቸኳይ ስብሰባ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 29 2017
በኤርትራ መንግሥት ላይ የትጥቅ ትግልን በማድረግ ለዓመታት የዘለቀው ድርጅቱ ባለፉት ቅዳሜ እና እሑድ አፋር ክልል ሎጊያ ሰመራ ውስጥ ባካሄደው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ በቀይ ባሕር አፋር ህዝብ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች መክሮ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።
የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በአፋር ክልል ሎጊያ-ሰመራ አደረኩ ባለው አስቸኳይ ድርጅታዊ ስብሰባ ሰፊው የአፍሪካ ቀንድ የፀጥታና መረጋጋት አደጋ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ በሚገኙ የአፋር ሕዝብ ላይ ያደርሳል ባለው «አፈና» እና እልባቱ ላይ መምከሩን አስታውቋል። በአስመራ መንግሥት ይደርስብናል ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመቀልበስም ለሕዝቡ ህልውና መከበር የሚያደርገውን ትግል የማስቀጠል ጽኑ ፍላጎት መኖሩን የኤርትራ ተቃዋሚዎች ሕብረት እና የቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ያሲን መሃመድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። «ቀይ ባሕር አፋር ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ መብት ጥሰትና የህልውና አደጋን በማስመልከት ከዚህ በፊት ለአፍሪካ ሕብረት ያስገባነውን ደብዳቤ ሂደት ክትትል ጨምሮ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠለ ሕዝቡ በሙሉ ተፈናቅሎ አከባቢው ምድረበዳ ወደ መሆን መሸጋገሩ ስለማይቀር በሚል የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ መፍትሄ መፈለግ አለብን በሚለው ጉዳይ ተወያይተን አቅጣጫ አስቀምጠናል» ነው ያሉት።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን በኢትዮጵያ አፋር ክልል እደረገ ያለው ድርጅቱ፤ የአካባቢውን ማሕበረሰብ ያሳተፈ ውይይት ከማድረግ ጀምሮ በቅርቡ እንኳ 200 ገጽ ያለው የሰብዓዊ መብት ይዞታን የተመለከተ ሪፖርት የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማቅረቡም ይታወሳል።
ድርጅታዊ መዋቅር
የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴው በሙያ ብቃት ብሎም በስነምግባር እንዲሁም ወጣቶች እና ሴቶችን በመሪነት ሚና ላይ በማካተት የመልሶ ማዋቀር እቅድ አጽድቋል ያለው መግለጫው፤ አፈጻጸሙን የሚቆጣጠሩ ኮሚቴዎች እንዳቋቋመ ጠቁሟል። በዚህም የፖለቲካ ተሳትፎው በአገር ውስጥ እና በውጭ ሃገራት እያደገ መጥቷልም ነው ያለው። አቶ ያሲን አክለውም፤ «በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉት ትግሉን ተቀላቅለው በተለይም ውጪ ያሉት በዲፕሎማሲው አኳያ ትግሉን እንዲያግዙ ነው የተጠየቀው» ብለዋል። የፖለቲካ አቅጣጫውም ከኤርትራ የፖለቲካ ኃይሎች ጥላ ስር በትብብር መሥራትን ማጠናከር እና በጀርመን ለሚካሄደው ሴሚናር እና ፌስቲቫል ድጋፍ የሚደረግበት መንገድ ማመቻቸት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ መመከሩንም አንስተዋል።
በቀይ ባሕር አፋር ክልል በሰላማዊ ዜጎች ላይ «እየደረሰ ያለውን ስቃይ» አስመልክቶ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሞራል እና ሰብአዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲል ያሳሰበው ድርጅቱ፤ ስለቀጣይ የፖለቲካ አቅጣጫውም አመልክቷል። «በቀጣይ አዲስ አሰራርና መዋቅር ከጸጥታውም ሆነው በዲፕሎማሲው ጫና ለማሳደር ዘርግተናልም» ያሉን አቶ ያሲን የተለያዩ ሰብዓዊ ጥሪ እንዲቀርብ ማስረጃዎችን የማጠናቀር ሥራዎችም እንደሚሰሩ ነው የጠቆሙት።
በድርጅቱ የቀረቡ መፍትሄዎች እና ምክረሃሳቦች
የቀይ ባሕር አፋር ይዞታን ማስከበር፣ የክልላዊ ግንኙነቶችን ብሎም የቀይ ባሕር አፋር ሕዝብን ተሳትፎ በቀጣናው ማረጋገጥ እና አዲስ የፖለቲካ ሰነድ በኤርትራ ውስጥ ለዴሞክራሲያዊና ዜግነት-ተኮር መንግሥት ማቅረብ በቀጣይ የተቀመጡ የድርጅቱ ሥዎች እና ምክረሃሳቦችም ናቸው ተብሏል።
የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሕዝቡ ነፃነት እና ክብሩ እስኪመለስ ትግሉን እንደሚቀጥል ነው በመግለጫው ያስረዳው።
ሥዩም ጌቱ
ሽዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ