የቀይ ባህር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 17 2017የቀይ ባህር አፋር ሕዝብ በኤርትራ መንግስት ለከፋ ሰብአዊ ጥሰትና ስደት መዳረጉን የቀይ ባህር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ገለፀ ። ድርጂቱ ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባቀረበዉ ተማፅኖም በኤርትራ መንግስት ላይ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል ። ድርጅቱ የኤርትራ አፋሮች ስልታዊ የሆነ የዘር ጭፍጨፉ እየተካሄደብን ነዉ ብሏል ። የኤርትራ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቻችን ከመቀማት በዘለለ በግዳጅ ዉትድርና ማሰማራትና ያለ ፍርድ በእስስር ማቆየት ርምጃዎችን እየወሰደብን ነዉ ሲልም ገልጿል ።
በኤርትራ የሚኖሩ የቀይ ባህር አፋሮች ለከፋ ሰብአዊ ጥሰት እና ስደት እየተዳረጉ ነው ሲል የቀይ ባህር አፋሮች ዲሞክራሲ ድርጅት አሳወቀ፡፡ ድርጅቱም 120 ገጽ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ዝርዝር መረጃ ለአፍሪቃ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስገብቷል፡፡
300,000 የሚደርሱ የቀይ ባህር አፋሮች የኢሳያስ አፈወርቂን አገዛዝ በመሸሽ በስደት ላይ ይገኛሉ ያሉት የድርጅቱ ሥራ አስፈፀሚ ኮሚቴ አባል አቶ ያሲን መሀመድ የቀይ ባህር አፋርን ማንነት እና የሚኖርበትን አካባቢ ዴሞግራፊ የመቀየር ሥራ እየተሠራ ነው ይላሉ፡፡
‹‹የቀይ ባህር አፋር ሕዝብ ታፍነው የተወሰዱ፣ አስገድዶ መድፈር የተፈፀመባቸው፣ በጅምላ የተጨፈጨፉ ከዚያም ተርፎ እስከ 300,000 የሚደርስ ህዝብ ተሰዶ ይገኛል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ማንነትን የመቀየር፣ የአካባቢውን ዴሞግራፊ የመለወጥ ግፍ እየተፈፀመብን ነው፡፡››
የቀይር ባህር አፋር የሚኖርበት አካባቢ ከየመን ከሳውዲ አረቢያን እና ሌሎች ሀገራት ጋር የሚያገናኝ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም ባህርን መሰረት አድርጎ የሚኖር ህዘብ ቢሆንም በኤርትራ መንግስት በሚወሰድበት ርምጃ ለከፋ ሰብአዊ ቀውስ መዳረጉን የቀይ ባህር አፋር ዴሞክራሲ ድርጅት ቃል አቀባይ አቶ አሊ አህመድ ይገልፃሉ፡፡
‹‹ አፋር ወደ የመን፣ ሳውዲ አረቢያ ጎረቤት ነው ይገናኛል፤ አሁን ከእነሱ ጋር መገናኘት አቁሟል፤ ስለዚህ ለእኛ ይሄ ዘር ማጥፋት ነው ውስን ቦታ ውስጥ መሰቃየት፤ ሰው በስቃይ እንዲሞትም ህክምና የለም፣የውሃ ጉድጓድም አይቆፈርም፤ አሁን ወደ የመን መሄድ አይቻልም፤ ወደ ጅቡቲም፤ ወደ ኢትዮጵያም ትልቅ እስር ቤት ውስጥ ነው ያለው ህዝቡ፡፡››
ለአፍሪቃ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረብነው አቤቱታ በቀይ ባህር አፋሮች ላይ በኤርትራ መንግስት እየደረሰ ያለውን እንግልት በሚገባ ያሳያል የሚሉት አቶ ያሲን መሀመድ አለም ዓቀፉ ማህበረሰብም በኤርትራ መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃሉ፡፡
‹‹120 ገጽ የሚሆን በቀይ ባህር አፋር ላይ የሚፈፀም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለአፍሪካ ኮሚሽን አቅርበናል፡፡ ተገቢ መልስ እንደሚሰጡንም ቃል ገብተውልናል፡፡ አሁን ደግሞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀይ ባህር አፋር ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እንዲረዳልን እና ተገቢ እርምጃ እንዲወስድልን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡››
አሁን ላይ በአፍሪቃ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኤርትራ መንግስት ላይ እየተደረገ ያለው ክትትል ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በሀገሪቱ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግን እየበረከቱ መጥተዋል ይላል፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ለሰራው ስራ ምስጋና እያቀረብን እንደዚሁም የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀረቡለት የተለያዩ መረጃዎች አሉኝ፤ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ግን በኤርትራ የሚወሰደው ሰብዓዊ ጥሰት የከፋ መሆኑ ነው፡፡››
የቀይ ባህር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የኤርትራ መንግስት በቀይ ባህር አፋሮች ላይ እያደረሰ ነው ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ለአፍሪቃ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሪፖርት ቢያደርግም በኤርትራ መንግስት በኩል ግን ስለ ጉዳዩ የተባለ ነገር የለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም የፊታችን ቅዳሜ የቀይ ባህር ዴሞክራሲ ድርጅት በአዲስ አበባ ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ እሰጣለሁ ብሏል፡፡
ኢሳያስ ገላው
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ