የሻንጋይ ትብብር ድርጅት ጉባዔ እና አንድምታዉ
ሰኞ፣ ነሐሴ 26 2017
ለሁለት ቀናት የዘለቀዉ እና የሻንጋይ ትብብር ድርጅት ጉባዔ የተለያዩ ስምምነቶችን በማድረግ እሁድ እለት ተጠናቋል። የሁለት ቀናቱ ጉባኤ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን እና የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲን ጨምሮ ከ20 በላይ ሀገራት መሪዎች በጋራ የተሳተፉበት ነበር። ከሻንጋይ ትብብር ድርጅት ዘጠኝ አባላት መካከል ቻይና፣ ሕንድ፣ ሩሲያ እና ኢራን ይገኙበታል። የትብብር መድረኩን አልፎ አልፎ ቻይና እና ሩሲያ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ለመገዳደር እንደሚጠቀሙበት አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። የሻንጋይ ትብብር ጉባዔ
ፑቲን ከቻይናው ፕሬዝደንት ጋር ፔኪንግ ላይ ሲገናኙ በቅርቡ በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል ስለተጀመረው ግንኙነት መመካከራቸውን ረዳታቸው ዩሪ ኡሻኮቭ ተናግረዋል። ጉባኤው ከተካሔደ በኋላ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያበቃበት 80ኛ ዓመት ለመዘከር ከነገ በስቲያ ረቡዕ ወታደራዊ ትርዒት ይቀርባል። ትርዒቱን የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ዑን እንደሚታደሙበት ቻይና ቀደም ብላ አስታዉቃ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ የቻይና ፕሬዝደንት ሺ ዢን ፒንግ እና የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሁለቱ ሀገሮች በድንበር ይገባኛል የገቡበትን እሰጥ አገባ በመፍታት ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በሻንጋይ ትብብር ድርጅት ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር ሕንድ እና ቻይና በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ ከዚህ ቀደም ከተፈጠረ አለመግባባት በኋላ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል። የቻይና እና የአፍሪቃ የትብብር ጉባዔ በጆሀንስበርግ
ሁለቱ መሪዎች ከጉባኤው ጎን ለጎን የንግድ እና የመዋዕለ-ንዋይ ግንኙነታቸውን በሚያሳድጉበት መንገድ ላይ ተወያይተዋል። ሺ ዢን ፒንግ እና ናሬንድራ ሞዲ የተገናኙት ሕንድ የሩሲያን ነዳጅ ትሸምታለች በሚል ሰበብ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦቿ ላይ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር 50% ቀረጥ ከጣለ በኋላ ነው። የትራምፕ አስተዳደር ቀረጥ በመጣል የወሰዳቸው እርምጃዎች የቻይና እና የሕንድ መሪዎች የምዕራባውያኑን ጫና ለመቋቋም ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረጉን ተንታኞች ይናገራሉ።
ገበያዉ ንጉሴ / አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ