የሶሪያ ተስፋ፣የአዲስ መሪዎችዋ ቃልና ተመድ
ዓርብ፣ ጥር 16 2017የሶሪያ ጊዚያዊ መንግሥት በሐገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ታጣቂ ቡድናትና የፖለቲካ ኃይላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ባለሥልጣናቱ እየተናገሩ ነዉ።ባለፈዉ ታሕሳስ የሶሪያን የረጅም ጊዜ ገዢ የአሰድ ቤተሰብን አስወግዶ ሥልጣን የያዘዉ የቀድሞዉ አማፂ ቡድን ሁሉን አቀፍ መንግሥት እንዲመሠርት ግፊት እየተደረገበት ነዉ።የጊዚያዊ መንግሥቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ትናንት እንዳሉት ሁሉም ወገኖች የሚወከሉበት ሥርዓት ለመመሥረት ፓርቲያቸዉ እየጣረ ነዉ።በሶሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ የሶሪያ ባለሥልጣናት የሚገቡትን ቃል እንዲጠብቁ አደራ ብለዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ የፕሬዝደንት ለዉጥ፣ በአዲሱ መሪ መርሕ ደስታ-ሥጋት ቅይጥ ስሜት፣ በጋዛዉ የሰላም ብልጭታ፣ በዩክሬን-ሩሲያዎች አሸናፊ-ተሸናፊ የለሽ መቀጣቀጥ ከተቃረጠ ጊዜዉ-ጊዜ ሲያገኝ ዓለም ሶሪያ-ደማስቆ ማለቱ አልቀረም።በሽር አል አሰድ ጥንታዊ ሐገራቸዉን ለ14 ዓመታት ከልቂት ትርምስ ሞጅረዉ የማታ-ማታ የበአዝ ፓርቲያቸዉን በትነዉ ከኮበለሉ ወዲሕ አሰድን ለመጣል በአንድ አብረዉ የነበሩት ብዙ አማፂያን አንድ ሐገራቸዉን አንድ አድርገዉ የሚያቆዩበት ብልሐት እንዴትነት ብዙዎችን ብዙ እንዳነጋገረ ወር አለፈ።
ሶሪያ የብዙ ተቃራኒ ኃይላት መሻኮቻ ሥልታዊ ሐገር
ከኃይማኖት ፅንፈኞች እስከ ጎሳ አቀንቃኞች፣ ከነፃ አዉጪዎች እስከ አሐዳዊ ሥርዓት ሰባኪዎች፣ ከአረብ ብሔረተኛ-በአዚዝቶች የሻም አገዛዝን እስከሚመኙ ጥንታዊያን የሚተራመሱ፣ ኢራን-ከእስራኤሎች፣ ሱኒዎች-ከሺአዎች፣ ሩሲያ ከምዕራቦች፣ ቱርኮች-ከኩርዶች የሚሻኮቱባት ሐገር ሰላሟን ጠብቃ፣ ሁሉንም አቻችላ የግዛት አንድነቷን አስከብራ የምትቀጥልበት ብልሐት በርግጥ አሁንም በግልፅ አይታወቅም።
የበሽር አል አሰድ መንግስት ከተወገደ በኋላ የፈነጠቀዉ ሠላሟ ግን እስካሁን አልታወከም።የሶሪያ ጊዚያዊ መንግሥት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አሳአድ ሐሰን አል-ሺባኒ ትናንት እንዳሉት ሶሪያ የሁሉም ሶሪያዉያን ናት።
«የሶሪያ ሕዝብ በአናሳ ጎሳዎች አይከፋፈልም።ሶሪያ ምንም ክፍፍል የማይደረግባት፣ ሰዎች በጎሳቸዉ በማሕበራዊ ደረጃቸዉ ወይም በእምነታቸዉ የማይቀጡባት የሁሉም የሶሪያ ሕዝብ ናት።»
የልዩ መልዕክተኛዉ አደራ
ከዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ በተጨማሪሥልጣን የያዘዉ የሐያት ተሕሪር አል ሻም ከፍተኛ መሪዎች ተመሳሳይ ቃል እንደገቡላቸዉ በሶሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ጌይር ፔደርሰን አስታዉቀዋል።መሪዎቹ ከብቀላ ታቅበዉ ሁሉንም ሶሪያዊ በእኩልነት ለማገልገል፣ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይል በፖለቲካ ሥልጣኑ ለማሳተፍ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ፔደርሰን አደራ ብለዋል።ሥልጣን ላይ ያለዉ የሐያት ተሕሪር አል ሻም ቡድንና በአሜሪካ የሚደገፈዉ ኩርድ መራሹ የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይላት (SDF) የተፋጠጡበት የሰሜን ምሥራቅ ሶሪያን ሠላም ግን ልዩ መልዕክተኛዉ «አሳሳቢ» ይሉታል።
«ሰሜን ምሥራቅ ያለዉን ሁኔታ ግን ሁለችንም ትኩረት ልንሰጠዉ በጥንቃቄ ልንከታተለዉ ይገባል።በሞግዚት አስተዳደሩ ባለሥልጣናትና በSDF መካከል የድርድር ዕድል መስጠት አለብን።ቱርክና ዩናይትድ ስቴትስም ድርድሩን በመደገፍ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል።»
የእስራኤል የኃይል ርምጃ የተመድ መልዕክተኛ ማሳሰቢያ
የበሽር አልአሰድ መንግስት ከተወገደ በኋላ እስራኤል «ጦር መሳሪያ ተከማችቶበታል» ያለችዉን አካባቢ በተደጋጋሚ በጦር ጄቶች ደብድባለች።እስራኤል እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1967 ጀምሮ በኃይል ከያዘችዉ የጎላን ኮረብቶች አልፋ ሌሎች የሶሪያ ግዛቶችንም መያዟ በተደጋጋሚ ተነግሯል።ልዩ መልዕክተኛ ፔደርሰን የእስራኤልን የኃይል ርምጃ ተቀባይነት የሌለዉና መቆም ያለበት በማለት ተቃዉመዉታል።
«ልድገመዉ።ይሕ ተቀባይነት የለዉም።ከሞግዚቱ ባለሥልጣን በጣም ጠቃሚ መግለጫ ሰምተናል።ይሕ እስራኤሎች አሁን የሚያደርጉት ነገር ምንም ምክንያት ሊቀርብበት አይችልም።መቆም አለበት።»
አሉ።ዓለም ሰማቸዉ።መቆም ያለበትን የሚያቆም ኃይል መኖሩ ለብዙዎች በግልፅ አይታወቅም።
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ