የሰኔ 9 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሰኔ 9 2017በአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ፦ የጀርመን ከ21 ዐመት በታች ተጨዋቾች ከእንግሊዝ ጋር አንድ ጨዋታ እየቀራቸው ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል ። ሊቨርፑል በቡድኑ የዝውውር ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን ክፍያ በመፈጸም ጀርመናዊው አማካይ ፍሎሪያን ቪርትስን ሊያስመጣ ተስማምቷል ። ከመላው ዓለም የተውጣጡ 32 ቡድኖች በሚሳተፉበት የፊፋ የዓለም የቡድኖች ግጥሚያ የጀርመኑ ባዬርን ሙይንሽን በሰላማዊ ውቅያኖስ አገራት ሻምፒዮን ሺፕ ዋንጫ አሸናፊ የኒውዚላንዱ ኦክላንድ ሲቲን 10 ለ0 አበራይቷል ። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም መርሴዲስ ወደ ቀድሞ አቋሙ ተመልሷል ።
አትሌቲክስ
በስቶኮልም ዲያመንድ ሊግ በወንዶች የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ኩማ ግርማ 12:57.46 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ስዊድናዊው አንድሬስ አልምግሪን ከኩማ በ13.19 ሰከንዶች በመቅደም አሸንፏል ።
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኖርዌይ ውስጥ በነበረው የኦስሎ ዳያመንድ ሊግ የሴቶች የዐሥር ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክከር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የኔዋ ንብረት 30:28.82 በመሮጥ በአንደኛ ደረጃ ለድል በቅታለች ። ኬኒያዊቷ ሚሪያም ቼቤትን (30:32.90) ተከትላ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ጫልቱ ዲዳ (30:33.86) ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።
በተመሳሳይ የኖርዌይ የወንዶች 5 ሺህ ሜትር ዳይመንድ ሊግ ውድድር ሐሙስ ዕለት አትሌት ኩማ ግርማ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ነበር ያጠናቀቀው ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቢኒያም መሀሪ ደግሞ ሁለተኛ ። በዚህ ውድድር፦ አትሌት ሀጎስ ገ/ሕይወት አምስተኛ፣ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ ስምንተኛ እንዲሁም አትሌት መዝገቡ ስሜ ዘጠነኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል ።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የቀድሞ አንጋፋ ተጨዋቾች ሙሉጌታ ከበደ ባሳለፍነው ሳምንት ሰኔ 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የመለየቱ ዜና ብዙዎችን አሳዝኗል ። በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ዓመት የተጫወተው ሙሉጌታ ከበደ በወሎ ፔፕሲ፣ ወሎ ምርጥ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ የእግርኳስ ቡድኖች ችሎታዉን አስመስክሯል ። ይህ ታላቅ የእግር ኳስ ኮከብ ለ15 ዓመታት ከኖረበት አሜሪካን ሀገር ተመልሶ በአዲስ አበባ ከተማ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ነው ከዚህ አለም በሞት የተለየው ። ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን ።
በአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ፦ የጀርመን ከ21 ዐመት በታች ቡድን ቼክ ሪፐብሊክን ትናንት 4 ለ2 አሸንፎ ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፏል ። ጀርመን ላይ ከረፍት በኋላ ሁለት ግቦች የተቆጠሩት በተከላካዮች ድክመት ነው ። ለጀርመን ቡድን ኒክ ቮልተማደ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እና አንድ ኳስ ለግብ በማመቻቸት የምሽቱ ኮከብ ሁኖ ወጥቷል ።
የጀርመን ቡድን ከእንግሊዝ ጋር ከነገ በስትያ (ረቡዕ) አንድ ጨዋታ ቢቀረውም ከምድቡ በሰበሰበው ስድስት ነጥብ ወደ ሩብ ፍፃሜው ከወዲሁ አልፏል ። የረቡዕ ግጥሚያ ግን ማን ከጣሊያን አለያም ከስፔን ጋር ሊገጥም እንደሚችል የሚለይበት ነው ። እንግሊዝ በዚሁ ምድብ «ለ» በ4 ነጥብ ትከተላለች፤ ስሎቬኒያ በ1 ነጥብ ሦስተኛ፤ ቼክ ያለምንም ነጥብ መጨረሺያ ተሰናባች ናት ።
ከምድብ «ሀ» ጣሊያን እና ስፔን ስድስት ነጥብ ይዘው ስፔን በግብ ክፍያ ይመራል ። ተሰናባቾቹ ስሎቫኪያ እና ሮማኒያ ያለምንም ነጥብ በግብ እዳ ተበላልጠው ሦስተኛ እና አራተኛ ናቸው ። በምድብ «ሐ» ፖላንድን 5 ለ 0 ጉድ ያደረገችው ፖርቹጋል ሩብ ፍፃሜውን የመቀላቀል እድሏ ከፍተኛ ነው ። ከጆርጂያ ጋር የገጠመችው ፈረንሳይ ባለቀ ሰአት አሸንፋ ከምድቡ በፖርቹጋል በግብ ክፍያ ብቻ ትበለጣለች ። ፖላንድ ከወዲሁ መሰናበቱን ሲያረጋግጥ፥ ሦስት ነጥብ ያለው የጆርጂያ ቡድን የማለፍ ዕድሉ ገና አልመከነም ። የግንቦት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በምድብ «መ» ስድስት ነጥብ የሰበሰበችው ዴንማርክ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፏን አረጋግጣለች ። ዩክሬን በሦስት ነጥብ ትከተላለች ። ኔዘርላንድስ እና ፊንላንድ ተመሳሳይ አንድ ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ይለያያሉ ።
የዝውውር ዜና
ሊቨርፑል በቡድኑ የዝውውር ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን ክፍያ በመፈጸም ጀርመናዊው አማካይ ፍሎሪያን ቪርትስን ሊያስመጣ ተስማምቷል ። የቦሩስያ ዶርትሙንድ የእግር ኳስ ቡድን ሥራ አስኪያጅ ሐንስ-ዮአሒም ቫትስከ፦ የፍሎሪያን ወደ ሊቨርፑል መኼድ ለባዬር ሌቨርኩሰን ጉዳት ነው ብለዋል ። እንደ ፍሎሪያን ያለ ምርጥ ተጨዋች ከለቡንደስሊጋው መራቁ «ብርቱ ጥፋት» ነው ሲሉም አክለዋል ። «ወደ ባዬርን ሙይንሽን ቢዛወር እንኳን ምንም አልነበረም» ያሉት ሐንስ፦ የ22 ዓመቱ አማካይ ከቡንደስሊጋው የሚለይ በመሆኑ ቁጭታቸውን ገልጠዋል ። የእንግሊዙ ሊቨርፑል የባዬር ሌቨርኩሰን እና የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አማካይ ፍሎሪያን ቪርትስን ወደ አንፊልድ ለማስመጣት 158 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል ።
የመጀመሪያው ልዩ የዝውውር መስኮት ከፊፋ የዓለም የቡድኖች ግጥሚያ በፊት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሲዘጋ፦ ማንቸስተር ሲቲ እና ቸልሲ በበኩላቸው ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥተዋል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ የውልቭስ አጥቂ ብራዚሊያዊው ማቴዉስ ኩኛን ወደ ኦልድ ትራፎርድ ለማስመጣት 84.8 ሚሊዮን ዶላር አፍስሷል ። ባለፈው የጨዋታ ዘመን ደካማ እንቅስቃሴው ደጋፊዎቹን ያበሳጨው ማንቸስተር ሲቲ፦ በቲጃኒ ሬይጃንደርስ፣ ራያን ቼሪክ፣ ራያን ኢይት-ኑሪ እና ማርኩስ ቤትናሊ ላይ ከ157 ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥቷል ። እንግሊዝ ውስጥ ዳግም የተከፈተው የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ከ11 ሳምንታት በኋላ ሐምሌ ውስጥ ይዘጋል ።
የፊፋ የዓለም የቡድኖች ግጥሚያ
ከመላው ዓለም የተውጣጡ 32 ቡድኖች በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ 11 ከተሞች ውስጥ በሚገኙ 12 ስታዲየሞች የሚሳተፉበት የፊፋ የዓለም የቡድኖች ግጥሚያ ውስጥ በሳምንቱ መጨሪያ በይፋ ተከፍቷል ። ትናንት ከነበሩ ግጥሚያዎች መካከል የጀርመኑ ባዬርን ሙይንሽን በሰላማዊ ውቅያኖስ አገራት ሻምፒዮን ሺፕ ዋንጫ አሸናፊ የኒውዚላንዱ ኦክላንድ ሲቲን 10 ለ0 ያበራየበት ግጥሚያ የመሰል ውድድር አስፈላጊነትን አጠይቋል ። ገናና የአውሮጳ ቡድኖች ዋንጫውን ሊወስዱት እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታበት የፊፋ የዓለም ቡድኖች ግጥሚያ በየአራት ዓመቱ የሚሰናዳ ነው ። የግንቦት 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የጀርመኑ ባዬር ሙይንሽን በዐለም የቡድኖች የእግር ኳስ ጨዋታ ሲንሲናቲ ውስጥ ኦክላንድ ሲቲን 10 ለ0 የግብ ጎተራ ባደረገበት ግጥሚያ ጃማል ሙሳይላ ሦስት ግቦችን ከመረብ አሳርፎ ሔትትሪክ ሠርቷል ። ቀሪዎቹን ግቦች ኪንግስሌይ ኮማን፣ ሣቻ ቦዬ፣ ሚካኤል ኦሊሴ እና ቶማስ ሙይለር እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ደጋፊዎቻቸውን በግብ አንበሽብሸዋል ። በ15ኛው የኦሺያኒያ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ያነሳው አማተሩ ኦክላንድ ሲቲ ቡድን በግዙፉ ባዬርን ፊት መቆም ተስኖት ተሽመድምዷል ። ባዬርን በሚገኝበት ምድብ «ሐ» ቀጣይ ጨዋታ የአርጀንቲናው ቦካ ጁኒየርስ እና የፖርቹጋሉ ቤኔፊካ ሊዝቦን በነገው ዕለት የሚያደርጉት ነው ።
የፈረንሣዩ ፓሪ ሳንጃርሞ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድን 4 ለ0 ድል አድርጓል ። ዛሬ በነበሩ ግጥሚያዎች፦ የብራዚሉ ቦታፋጎ የዩናይትድ ስቴትሱ ሲያትል ሳውንደርስን 2 ለ1 አሸንፏል ። የብራዚሉ ፓልሜይራ እና የፖርቹጋሉ ፖርቶ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል ። ምሽቱን በምድብ «መ» የእንግሊዙ ቸልሲ ከሎስአንጀለስ ጋር ይገጥማል ። የግንቦት 4 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ለአንድ ወር በሚዘልቀው የፊፋ የዓለም የቡድኖች ግጥሚያ ውድድር ከየአገራቱ ሁለት ቡድኖች ብቻ ናቸው መሳተፍ የሚችሉት ። ከእንግሊዝ ቸልሲ እና ማንቸስተር ሲቲ በማለፋቸው ሊቨርፑል ምንም እንኳን የአውሮጳ ቁጥር አንድ ምርጥ ቡድን ቢሆንም ዘንድሮ በውድድሩ የተሳታፊዎች ገደብ የተነሳ መሳተፍ አልቻለም ። ከስፔን የላሊጋው ባለድል ባርሴሎና እንዲሁም የጣሊያን ሴሪኣ አሸናፊ ናፖሊም ያልተገኙበት ምክንያት በዚሁ የፊፋ ከአንድ አገር ሁለት ቡድኖች ብቻ ተሳትፎ የሚል ጥብቅ ሕግ ነው ። ቡድኖቹ ዋንጫ ማግኘታቸው ብቻ በዚህ ውድድር በቀጥታ ተሳታፊ አያደርጋቸውም ይላል ፊፋ ። እንደ ፊፋ መስፈርት ከሆነ ከየአገራቱ ሁለት ቡድኖች የሚመረጡት የሊጎቻቸውን ዋንጫ ስለወሰዱ ብቻ ሳይሆን፤ ባለፉት አራት ዓመታት ባሳየቱት ብቃት ጭምር ነው ።
ሊዮኔል ሜሲ በቅዳሜው ግጥሚያ ለቡድኑ የፈየደው ነገር አልነበረም
ቅዳሜ ምሽት የግብጹ አል አህሊ ከዩናይትድ ስቴትሱ ኢንተር ሚያሚ ጋር ተጋጥሞ ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። የ37 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ምርጥ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በቅዳሜው ግጥሚያ ለቡድኑ የፈየደው ነገር አልነበረም ። ፊፋ የ40 ዓመቱ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶም ከሣዑዲ ዓረቢያው አል አህሊ ቡድን ወጥቶ ሌላ ቡድን በመቀላቀል ወደ ውድድሩ እንዲመጣ ልዩ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ለዐሥር ቀን ቢከፍትም ሮናልዶ አልተጠቀመበትም ። ይልቁንስ ፖርቹጋላዊው አጥቂ በአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ ለአገሩ ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ግብ በማስቆጠር ከስፔን ጋር ሁለት እኩል ነጥብ እንዲጋሩ በማስቻል በመለያ ምት አገሩ ዋንጫ እንድታነሳ አስችሏል ።
ፖርቹጋል በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከስፔን ጋር ሁለት እኩል በተለያየችበት የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ የፍጻሜ ግጥሚያ አቻ የምታደርገውን ወሳኝ ግብ በ61ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነበር ። በጀርመን ባዬርን ሙይንሽን አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ፖርቹጋል በመለያ ምት ስፔንን 5 ለ3 ድል አድርጋም ዋንጫውን እንድታነሳ አስችሏል ።
የመኪና ሽቅድምድም
በነሐሚልተን ጊዜ ገናና የነበረው ማርቼዲስ ወደ ቀደመ ገናናነቱ የተመለሰ ይመስላል ። ትናንት በካናዳ የሞንትሪያል ግራንድፕሪ ሽቅድምድም መርቼዲስ አንደኛ አና ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ትናንት ጆርጅ ረስል አንደኛ ሲወጣ፥ የቡድን አጋሩ የ18 ዓመቱ አዳጊ ኪሚ አንቶኖሊ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የዐለም ባለድሉ ማክስ ፈርሽታፐን የሁለተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል ። ላንዶ ኖሪስ የባለፈው ሳምንት ፉክክር አሸናፊ የማከላረን ቡድኑ አሽከርካሪ ኦስካር ፖያስትሪን ለመቅደም ባደረገው ሙከራ ከመንገዱ ጠርዝ አጥር ጋር ተላትሞ ከውድድር ውጪ ሁኗል ። የፌራሪ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ ትናንትም በስድስተኛ ደረጃ አጠናቅቋል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ