በግጭት ወቅት የሚበዛው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት እና ፈተናው
ሐሙስ፣ ነሐሴ 15 2017የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ባሳለፍነው ሰኞ ነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የሐዘን መግለጫ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ሰብዓዊ ተግባሩን ሲያከናውን በነበረው ባልደረባው አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን ላይ ደረሰ ያለውን አሰቃቂ ህልፈተ ሕይወት አውግዟል። ባልደረባው ነሐሴ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ከደባርቅ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጨነቅ አካባቢ አገልግሎት ላይ በተሰማራበት ባልታወቀ ቡድን ታግቶ በተፈጸመበት ድብደባ እና ኢ-ሰብዓዊ ኣያያዝ ምክንያት ነሐሴ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ሕይወቱ ማለፉን ያሳወቀው፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በዚህ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ማዘኑን ገልጾ ለቤተሰቦቹ እና አጋር የሰብዓዊ ተቋማት ኀዘኑን አጋርቷል።
ከአቶ ሆነልኝን ጋር አብረዋቸው በሥራ ላይ እያሉ ታግተው በሕይወት ግን በተረፉ ሁለት ሠራተኞቹ መጽናናቱን የገለጸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል ለሌሎች የሚደርሱት የሰብአዊ ድጋፍ ሠራተኞች ያለ ስጋት በገለልተኝነት ሥራቸውን እንዲሠሩ ሁሉም ወገኖች ጥበቃና ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቱ በሚንርበት በግጭት ወቅት ድጋፍን ማድረስ ቀላል እንዳልሆነ ለዶይቼ ቬለ የገለጹት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ድረስ ደስይበለው፤ «በዚህን ወቅት አንዱ ፈተና የተደራሽነት ፈተና ነው» በማለት በሰላሙ ወቅት በአፋጣኝ እርዳታን የማድረስ ማዕቀፍ በግጭት ወቅት በተቃራኒው በሚፈጠሩ መስተጓጎሎች ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰድ የድጋፍ ሥራውን እንደሚያዘገይ አሳውቀዋል።
በግጭት ወቅት በሰው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እና ተጎጂዎችን ለመርዳት ከመንግሥት የፀጥታው ኃይሎችም ሆነ ከማንኛውም አካል ጋር መሥራት የሰብዓዊነት መርሆ መሆኑንም የገለጹት ሃላፊው፤ «በየትኛውም አካባቢ የኛ ሥራ ግልጽ ነው፤ ለማንም ሳናዳላ ለተጎጂዎች የምንደርስ ተቋም ስለሆንን የትኛውም አካል ጥበቃ እያደረገልን አገልግሎታችንን መስጠት ይኖርብናል»ም ብለዋል።
ያም ሆኖ በእርዳታ ሠራተኞቹ እና አገልግሎት አቅራቢ ተሽከርካሪዎቹ ላይ ጉዳት እንደሚያጋጥም ገልጸው፤ «በጎፈቃደኞቻችን እና ሠራተኞቻችን ሁልጊዜም መስክ ላይ ናቸው። አምቡላንሶቻችን እና ተሸከርካሪዎቻችንም እንዲሁ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ፈተናዎች ይገጥሙናል። ለምሳሌ ከዓመት በፊት አማራ ክልል ለእርዳታ ሥራ ድጋፍ ተሰጥቶን የተቀበልናቸው ሁለት ተሽከርካሪዎቻችን እንዳሰማራናቸው ተወስደውብን እስካሁን አልተመለሱልንም» በማለት አምቡላንሶችም ላይ አልፎ አልፎ የመሰበርና መሰል አደጋዎች በአማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልሎች ማጋጠማቸውን አስረድተዋል።
በቅረብ ጊዜ የሰብዓዊ ተቋሙን ሠራተኞች ከሕይወት አንጻር አደጋዎች ሲያጋጥሙ እምብዛም አይስተዋልም ያሉት አቶ ድረስ፤ ከሰሞኑ ያጋጠመውን የአንድ የማሕበሩን ሠራተኛ ሕልፈት ደግሞ እጅግ አስደንጋጭ ብለውታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሰሞኑ ማክሰኞ ታስቦ የሚውለውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ቀንን አስመልክቶ ይፋ እንዳደረገዉ፤ በጎርጎሮሳዊው 2024 ብቻ 383 የእርዳታ ሠራተኞ ተገድለዋል። ይህ ቁጥር ከካቻምናዉ 2023 ጋር ሲነጻፀር የተገደሉ የእርዳታ ሠራተኞች ቁጥር በ 31 በመቶ መጨመሩንም የመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ አመልክቷል። አብዛኞቹ የእርዳታ ሠራተኞች የተገደሉት ደግሞ በጋዛ ሰርጥ እና በሱዳን መሆኑን ያመለከተው ዘገባው፤ በአንድ የእርዳታ ሠራተኛ ላይ የሚሰነዘረ ጥቃት በሁሉም የእርዳታ ሠራተኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት ነው በማለት አውግዞታል። የመንግሥታቱ ድርጅት በተያዘው 2025 ዓ.ም. ደግሞ በሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከከዚህ በፊቱ ሁሉ የከፋ ሊሆን እንደሚችልም ፍንጭ መስጠቱ ይታወሳል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ