የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች እና አውዳመት
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11 2017የትንሳኤን በአልን ለማክበር በደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች በመጠለያ ጣቢያቸዉ እያደረጉት ያለዉ ዝግጂት ዛሬ እና ከአመታት በፊት ለወግ ማዕረግ በበቁበት ልጂ ወልደዉ ለመሳም በቻሉበት ቤት ንብረት ባፈሩበት የተፈናቀሉበት ስፍራ ምን ይመስላል ስንል ቆይታ አደረግን
ቤት ያፈራዉን አዘጋጂተዉ ከወዳጂ ዘመድ ጋር በአልን በቤታቸዉ ያሳልፉ የነበሩ እነኝህ በደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ በሚገኙ የስደተኛመጠልያ ጣቢያ ዉስጥ የሚኖሩ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ትናንት ሌላ ቀን ሆኖ ዛሬ ሁለት ወር የፆሙትንየትንሳኤ በአል ዋዜማ ላይ ሆነዉ በመጠለያ ጣቢያ የበአሉ ዝግጂት ይህንን ይመስላል።
«ሲገኝማ ዳቦዉ ስጋዉ ጠላዉ ነበር ታዲያ ከየት ይገኛል አርሰንማ አግኝተን እናዉቅ ነበር ዛሬ ከየት ይምጣ ያ ልምድ ከየት ይገኝ ሰማይ በሩጫ ይደረሳል? የት ይገኛል መላዉ ጠፍቶብን እንጂ ፋሲካማ እንዴት ነበር ሁለት ወር ተፁሞ ዝም ብሎ ይዋላል እንዴ እና መላዉ ጠፋን የት እንድረስ ወደ ማን ይነገራል ሀብታም የሉ አበድሩን አንል ማን ያዉቀናል ማን ያበላል ማን ያጠጣል ማን ያበድራል እና በጣም ችግር ላይ ነን»
ለትንሳኤ በአል የተደረገ ድጋፍ
በሰሜን ወሎ ጃራ የስደተኛ ጣቢያ የሚኖሩ ተፈናቃዮችም ቤት ያፈራዉን አዘጋጅተን ከትንሳኤዉ በረከት ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል ሲሉ ይገልፃሉ።
«ባለን ነገር ለክብሩ ዝግጁ ነን ዝም ብለን ልንዉል ነዉ ስንል ትናንት ደረቅ በቆሎ አምጥተዉ ሰጡን እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ካምፑ እንዳለ ሌላ ነገር ነዉ በደስታ ስጋና ወተት ያንን ነገር ትቶ ይህ ደረቅ በቆሎ መገኘቱ በጣም ትልቅ ደስታ ነዉ»
በተለይም በመጠለያ ጣቢያ ዉስጥ ያለፉትን አራትና አምስት አመታት ያሳለፉ ህፃናት ልክ እንደትናንቱ ዛሬም የትንሳኤ በአልን አምሮና ተዉቦ ለማሳለፍ ቤተሰቦቻቸዉን አልባሳት ግዙልን ጥያቄ ያቀርባሉ
የልጆች ጥያቄ መበርታት
«ስድስት ቤተሰብ ነኝ ልጆቼ አሁን ለበአል ምን ለብሰን ነዉ የምንዉለዉ እያሊ ነዉ የወለጋዉ ትዝ ይላቸዋል እነዛ ዘመዶቻችን ይጠሩ ነበር እያሉ አእምሮሮቸዉ እየተበላሸ ነዉ እዚህማ ደረቅ በቆሎ ቆርጥመን እንዉላለን የወለጋዉማ ከዚያ ከዚህ ሙክት ታርዶ ከዘመድ ጋር እየተደሰትን እንዉላለን»
የቱርክ ካምፕ የአማራ ክልል ተፈናቃዮች የድረሱልን ጥሪ
የትንሳኤ በአል በቤታቸዉ ከወዳጃ ዘመድ ጋር ማሳለፍ የለመዱ አርሶደሮች ዛሬ ላይ በአጥር ተከልለዉ በሚኖሩበት መጠለያ ጣቢያ ዉስጥ በትናንት ትዉስታ እየኖሩ ትንሳኤኖ እለቱን በማሰብ እንደሚያሳልፉ ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም በድምቀት የሚከበረዉ ትንሳኤ
«ምን አለኝና እዘጋጃለሁ አሁን ሲኖር ነዉ እንጂ የሚዘጋጂ ሰዉ ምን ምን አለኝ እና ምን አለኝ አገሬማ ምን የመሰለ ፍየል አርጄ ልጆቼ ጋር እዉላለሁ አማቾቸን እጠሬለሁ በጥሩ ሁኔታ እኖራለሁ ጌታ ያዉጣልን ቀን እንጂ ጨለማዉ ገብተን የለም እንዴ»
በሀይቅ መካነ ኢየሱስ መጠለያ ጣቢያ ዉስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች የትንሳኤን በአል ለማክበር ምንም ዝግጅት የለንም ይላሉ።
«አንድ ነገር ዝግጂት የለንም አንድ ነገር በምናችን ከየት አምጥተን እናዘጋጀዋለን የበአል ዝግጂት የሚባል ነገር ምንም የለም ዛሬ የልጆቻችን አጠያየቅ ብቻ ጭንቅላታችንን ይነካዋል»
የትንሳኤ በአልን ለአመታት በቤታቸዉ ከወዳጂ ዘመድ ጋር ያሳለፉ እነኝህ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች የመጣን ሰሞን ማህበረሰቡ በበአል ከኛ ጋር እያሳለፈ ደስታዉን ሲያጋራን የቆየ ቢሆንም ዛሬ ላይ ግን የብርሃነ ትንሳኤዉን በረከት በማሰብ እዕለቱን እናከብራለን ብለዋል።
ኢሳያስ ገላው
ታምራት ዲንሳ