የሰላም መታጣት እና የፖለቲካው ቀውስ አዙሪት በኢትዮጵያ
እሑድ፣ ሐምሌ 30 2015ማስታወቂያ
ኢትዮጵያ ከፖለቲካ አዙሪት መውጣት ከተሳናት ከራረመች። ዜጎች በሀገሪቱ በጎ ዜና ለመስማት እንደናፈቁ ዘመናት ተፈራረቁ። ከሁለት ዓመታ በላይ የዘለቀው ጦርነት እና የጦርነት ወሬ የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፎ፤ ሃዘኑ በወግ ሳይረሳ፤ ጦርነቱ ያወደመው ንብረት እና ያበላሸው የማኅበረሰቡ መስተጋብር መፍትሄ ሳይበጅለት፤ ሕዝቡ ዳግም ጦርንነት ሊያስተናግድና የጦርንም ወሬ ይሰማ ዘንድ ከተገደደበት ወቅት ላይ ደርሷል። የፀጥታው ስጋት ከከረመበት አካባቢ የተረጋጋ ይመስል ወደነበረው የሀገሪቱ ክፍል ሳይቀር መዛመቱ በኦሮሞ ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም ጋምቤላ ክልል ሳያበቃ አማራ ክልል ላይ ጸንቷል። ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ የዜጎች ከቦታ ቦታ በሰላም ወጥቶ መግባት እጅግ አዳጋች እየሆነ መምጣቱም ይነገራል። እያደር የሚለዋወጠው የሸቀጦች ዋጋ መናር ሸምቶ አዳሪውን ግራ ሲያጋባ፤ በዘንድሮው የእርሻ ወቅት በማዳበሪያ ዕጥረት አብዛኛው መሬት በዘር አለመሸፈኑ መጪውን ዓመት አሳሳቢ እንደሚያደርገው የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። የሰላም መታጣት እና የፖለቲካው ቀውስ አዙሪት በኢትዮጵያ የዶቼ ቬለ የእንወያይ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
ሸዋዬ ለገሠ