የምክክር ኮሚሽን ሥራውን በትግራይ ክልል እንዴት እያካሄደ ነው?
ዓርብ፣ ሰኔ 27 2017የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና ቃል ዐቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ዛሬ አርብ ሰኔ 27 ቀን ለጋዜጠኞች እንዳሉት "ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች የመቅረጽ ሥራ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው"። ኮሚሽኑ ከዚህ ሁሉ አስቀድሞ ግን በትግራይ ክልል "ነባራዊ ኹኔታው አስቸጋሪ" ቢሆንም በክልሉ ሥራውን ለማጠናቀቅና አጀንዳዎችን ለማሰባሰብከሚመለከታቸው ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን፣ "በተደጋጋሚ" ተደርጓል ያሉት ግልጽ ደብዳቤ ለጊዜያዊ አሥተዳደሩ ፕሬዝዳንት ተጽፎ መግባቱንና ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ምክክር በግጭት ወቅት፣ ድህረ ግጭት እና ከግጭት በፊት እንደሚከናወን ያስታወሱት ኃላፊው፣ የኢትዮጵያው ሂደትም በሦስቱም ሁናቴዎች እያለፈ ያለ ነው ብለዋል። በትግራይ ክልል ያለው ነባራዊ ኹኔታ አመቺ ካልሆነና ተሳትፎ ባይኖር ምን እንደሚሆን ተጠይቀው "ጫና እንደሚኖር" የገለፁት አቶ ጥበቡ "የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በክልሉ ምክክሩ ይቀጥላል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 4500 ሰዎች ይሳተፉበታል የሚባለው ዋናው ጉባኤ የሚከወንበት የአሰራር ሥርዓት እየተበጀለት መሆኑንም ተጠቅሷሳ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ አጠቃላይ ምክክሩንም ሆነ በዚህ ረገድ በትግራይ ክልል ይጠበቃል ያሉትን ጉዳይ ጠቅሰው ነበር።
"ሁሌ የማይገኝ ዕድል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሲለመን የነበረ ጉዳይ ነው። አሁን ዕድል መጥቷል እንጠቀምበት። ትግራይ በሚመለከት ግን በፍጥነት ወደ ውይይት መግባት እንዳለባቸው ይሰማኛል"።
ኮሚሽኑ ትጥቅ አንግበው ከመንግሥት ጋር የሚዋጉ ኃይሎች አጀንዳቸውን ይዘው እንዲቀርቡ፣ ከለላም እንዲደረግላቸው ለማድረግ ጥሪ ቢያደርግም አሁንም "ፈቃዳቸውን በግልጽ ያሳዩበት ሁኔታ የለም" ተብሏል። በሌላ በኩል የክስ ሂደታቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው የሚከታተሉ የጊዜ ቀጠሮ እሥረኞች ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሊደረግ ስለመሆኑ አቶ ጥበቡ ታደሰ አረጋግጠዋል። በምን መልኩ? ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያ ባይሰጡበትም።
ከጅምሩ ከተቋሙ ኃላፊዎች አሰያየምም ሆነ በኮሚሽኑ አወቃቀር ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ ያነሱ፣ በሂደት ራሳቸውን ከተሳትፎ ያገለሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉበት፣ ነፍጥ ያነሱት እና በውጪ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ጉልህ ተሳትፎ ባላደረጉበት፣ ዋናው ጉባኤ ላይ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ታዛቢ እንዲኖር ይደረግ እንደሆን የተጠየቁት የኮሙሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና ቃል ዐቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ሥራው የሀገር ውስጥ እና "ታዛቢ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም" ሲሉ መልሰዋል። ምንም እንኳ ኮሚሽኑ ከተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያገኝ መሆኑ ቢታወቅም።
በአዋጅ የተመደቡለትን ሦስት የሥራ ዓመታት ከ አምስት ወራት በፊት ያጠናቀቀው ምክክር ኮሚሽኑ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም በአስቸኳይ የምክር ቤት ጉባኤ ለአንድ ዓመት እንደተራዘመለት ይታወሳል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ