የሜርክል «እንወጣዋለን፤ አያቅተንም» አስረኛ ዓመት
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2017የቀድሞዋ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል Wir schafen das «እንችላልን ወይም አያቅተንም» በማለት ጀርመን ለ1.2 ሚሊዮን ሥደተኞች በሯን የከፈተችበት 10ኛ ዓመት ባለፈው እሁድ ታስቧል።
«ብዙ ነገሮችን አሳክተናል። ይህንንም እንወጣዋለን»
«እንችላለን፣ እንወጣዋለን» የሚለው አረፍተ ነገር ጀርመን ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ መሆንዋን ለዓለም ያሳወቀ ልዩ መለያዋ ነው። የቀድሞዋ የጀርመን መራኂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጀርመን በርካታ ስደተኞችን እንደምትቀበል ጥሪያቸውን ሲያሰሙ ትችት ከተነሳባቸው በኋላ «አያቅተንም» ያሉበት ይህ አነጋገራቸው ባለፈው ሳምንት እሁድ አስር ዓመት ደፈኗል። የያኔዋ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ መሪ ሜርክል ይህን ባሉበት በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም የአውሮጳውያኑ በጋ፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ጀርመን በመምጣት ላይ ነበሩ። አብዛኛዎቹ ከሶሪያ ከአፍጋኒስታን እና ከኢራቅ ነበር የመጡት። ጀርመን ሲደርሱም ህዝቡ በትብብር እና በእርዳታ መንፈስ ነበር የተቀበላቸው። ያኔ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በደቡብ ጀርመኑ በሙኒክ ከተማ ዋና ባቡር ጣቢያ ሲደርሱ የአካባቢው ህዝብ ወጥቶ ትናንሽ ስጦታዋችን ጭምር ይዞ ነበር እንኳን ደኅና መጣችሁ በማለት የተቀበላቸው። ይሁንና ይሁንና የዶቼቬለዎቹ ሊዛ ሄነል፣ ግያና ግሩን፣ እና ፔተር ሄለ እንደዘገቡት ከ10 ዓመት በኋላ አሁን ጀርመን ተቀይራለች። በጀርመን ለስደተኞች ያለው አመለካከት መቀየሩ ግልጽ ነው። አሁን ከምንም በላይ ጥርጣሬ እና አለመቀበል አመዝኗል።
ጀርመን በዚህ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም አላሳካችም ማለት ይቻላል። ያኔ ጀርመን ከገቡ ስደተኞች መካከል እስካሁን ስራ ያላገኙ አሉ። በስደተኞች የሚፈጸሙና በስደተኞችም ላይ የሚደርሱ ወንጀሎች በእጅጉ የሚያከራክሩና የሚያነጋግሩ ጉዳዮች ከሆኑ ሰነበተ ። እዚህ ጀርመን ፍልሰት በስሜት የሚነዳ አጀንዳ ሆኗል።
በአስር ዓመት ውስጥ ምን ያህል ስደተኞች ጀርመን መጡ?
በጎርጎሮሳዊው 2015 እና 2016 ከለላ ፍለጋ ጀርመን የመጡና ተገን እንዲሰጣቸው የጠየቁ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች ጀርመን መጥተዋል። ያኔ እንደ ጀርመን ከፍተና ቁጥር ያለው ስደተና የተቀበለ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገር የለም። ከጀርመን ቀጥሎ ኢጣልያ 204,000 ሀንጋሪ 203,000 ስዊድን 178,000 ስደተኞችን ነው ያስገቡት። በቀጣዮቹ ዓመታት ግን የተገን ጠያቂዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።
ይሁንና ጀርመን የጥገኝነት ማመልከቻ ያስገባ ሁሉ ወዲያውኑ በስደተኝነት እውቅና ያገኛል ጀርመን የመኖር መብትም ይሰጠዋል ማለት አይደለም። ጀርመን ባለፉት አስር ዓመታት ከደረሷት የተገን ጥያቄ የያዙ ማመልከቻዎች ከ56 በመቶ የሚበልጠውን ተቀብላለች። በዚህም መሠረት 1.5 ሚሊዮን ስደተኞች ጀርመን የመቆየት መብት አግኝተዋል። ከሌሎች የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ጀርመን ስደተኞችን በመቀበል ከአማካይ በላይ የሚገኘውን ደረጃ ትይዛለች። ብዙ ስደተኞችም ተቀብለዋል ከሚባሉት ቀዳሚው ስፍራ የጀርመን ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም ጀርመን በፖለቲካ ምክንያት ለሚሰደዱ ሰዎች በሕግ በግዳጅ ተፈጻሚነት ያለው ተገን የማግኘት መብት ከሚሰጡ ጥቂት ሀገራት አንዷ ናት። በፖለቲካ ምክንያት ከተሰደዱ ሰዎች በተጨማሪ በጄኔቫው ስምምነት ለምሳሌ በሀገራቸው በሚካሄድ ጦርነት ሰበብ ለሚሰደዱ ሰዎች ንዑስ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የምትፈቅድም ሀገር ናት።
ከየትኛዎቹ ሀገራት የመጡ ሰዎች ናቸው ጥገኝነት ያገኙት ?
በ2015 እና በ2016 ጀርመን ከገቡት አብዛኛዎቹ ያኔ በጦርነትና ግጭት ከተመሰቃቀሉት ከሶሪያ አፍጋኒስታንና ኢራቅ የመጡ ስደተኞች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ከሚኖሩት ሶሪያውያን ግማሹ ከጎርጎሮሳዊው 2014 እስከ 2016 ጀርመን የገቡ ናቸው። ሶሪያውያን አንድ አምስተኛው የጀርመን ዜግነት አግኝተዋል። ከ,ስር አንዱ ደግሞ ጀርመን ነው የተወለዱት።በጎርጎሮሳዊው 2022 ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ከተጀመረው የሩስያ ዩክሬን ጦርነት በኋላ ደግሞ ጀርመን 1.3 ሚሊዮን ዩክሬናውያን ስደተኞች አስጠግታለች።
የስደተኞች ቤተሰብን መልሶ ማገናኘት
በ2015 እና በ2016 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ጀርመን የገቡ ስደተኞች ቤተሰቦችም እዚህ እንዲመጡ ተደርጓል። በዚህ መሠረት ከ2015 እስከ 2017 ጀርመን 230 ሺህ የቤተሰብ መልሶ መገናኘት ማመልከቻዎች አጽድቃለች። ይሁንና ይህ አሠራር በተለይ ውስን ጥበቃ ለሚደረግላቸው ስደተኞች በአዲሱ የጀርመን መንግሥት በዚህ ዓመት በሐምሌ ወር ለሁለት ዓመታት ታግዷል።
ስደተኞች ምን ያህል ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋኅደዋል ?
የዛሬ አስር ዓመት ጀርመን የመጡት ስደተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር መዋሀድ አለመዋሃዳቸው የሚለካበት ዋነኛ መስፈርት በስራው ገበያ የመዋሀዳቸው ስኬት መሆኑን የዶቼቬለዎቹ ሊዛ ሄነል፣ ግያና ግሩን፣ እና ፔተር ሄለ ዘገባ ይጠቁማል።
ኩልያ ኮስያኮቫ በጀርመኑ የባምበርግ ዩኒቨርስቲ የፍልሰት ጉዳዮች ተመራማሪ ናቸው። ስደተኞች በስራው ገበያ የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች በጥልቀት አጥንተዋል። ጀርመን ስደተኞችን በስራው ገበያ ውስጥ መዋሀዱ ተሳክቶላታል የሚል ጥያቄ ከዶቼቬለ ቀርቦላቸው ሲመልሱ፤ ሙሉ በሙሉ አለመሳካቱን ነበር የተናገሩት።
«በከፊል አሳክታለች ነው የምለው። ወይም ለሁሉም አላሳክንም። ሴት ስደተኞችና በእድሜ የገፉት ሁኔታ መሻሻል አለበት»
በ2025 በግንቦት ወር መጨረሻ ስራ አጥነት በጀርመን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነበር ።ከጎርጎሮሳዊው ጥር 2015 ዓም ወዲህ ተገን ጠያቂዎች ከሚያመዝኑባቸው ከአፍጋኒስታን፣ከፓኪስታን፣ ከኢራን ፣ ከኢራቅ ፣ከሶሪያ ፣ከሶማሊያ እና ከኤርትራ የመጡ ስደተኞች የቅጥር ሁኔታ ከፍተኛ ነው። የስራ እድል ከፍ ያለ ነው። በዚህ ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በ2015 ዓም ጀርመን ከመጡት ስደተኞች 60 በመቶው በመጡ በሰባት ዓመቱ ስራ ይዘዋል። ግን ይህ ያልተሳካላቸውም አሉ እንደ ኩልያ ኮስያኮቫ በ2015 ጀርመን በመጡ ስደተኞች ላይ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት መሠረት ወደ ጀርመን
«ወጣት ወንዶች እድሚያቸው እስከ 45 የሚደርስ ከሌሎቹ በተለየ በስራው ገበያ መዋኃዳቸውን እናያለን። ከ45 ዓመት በላይ የሆኑት ደግሞ በጀርመን ስራ የማግኘት እድላቸው በጣም አነስተኛ ነው።»
ሌላው የኮንስታንዝ ዩኒቨርስቲው የፍልሰeት ተመራማሪ ዳንኤል ታይም ደግሞ የዛሬ አስር ዓመት ጀርመን የመጡት ስደተኞች ዝቅተኛ የስራ ክህሎት ያላቸው እንደነበሩ ያስረዳሉ
«ጀርመን የሚመጡት ተገን ጠያቂዎች በአማካይ ዝቅተኛ የስራ ክህሎት ያላቸው ናቸው። በርግጥ ከመካከላቸው ሐኪሞችም አሉ አብዛኛዎቹ ግን የዩኒቨርስቲ ትምህርትም ሆነ የሙያ ስልጠና የላቸውም። መጀመሪያ ሲመጡ ጀርመንኛ አይናገሩም። የሚያስፈልጋቸውውን የሚያሟላቸው መንግስት ነው። የሚኖሩትም በመንግስት ማኅበራዊ ድጎማ ነው። ስራ ማግኘት ብዙ ዓመታት ይወስድባቸዋል። ቢያገኙም ብዙውን ጊዜ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ስራ ነው።»
በሀገራቸው ከተሰማሩበት ሙያ ጋር ሲነጻጸር ስደተኞች ጀርመን ውስጥ በአብዛኛው የሚሰሩት በድጋፍ ሰጭነት ሲሆን ቁጥራቸው ብዙም ያልሆነ ክህሎት ያላቸው ባለሞያዎችም አሉ።ይህ የሆነበት ምክንያትም በአጠቃላይ በቂ ስልጠና አለማግኘት ብቻ ሳይሆን የቋንቋም ችግር ነው። ከዚህ ጋር ከሀገራቸው የሚያመጧቸው የትምሕርት ማስረጃዎች እውቅና አለማግኘታቸው እንዲሁም በሚኖሩበት አካባቢ የስራ እድል ዝቅተኛ መሆኑም ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው። ይህ ደግሞ በገቢያቸው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም።
የስደተኞች የቋንቋ ችሎታስ?
ከኅብረተሰቡ ጋር የመዋሀድ አንዱ መለኪያ ቋንቋ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም ጀርመን ውስጥ ላሉ ሚያዎች የጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታ አስፈላጊ ናቸው። ይሁንና የጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታን በተመለከተ በተለይ ጾታን መሠረት ባደረገ በጎርጎሮሳዊው 2020 በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት መሠረት ከሴቶቹ 34 በመቶው B1 ወይም B1 የተባለውን የቋንቋ ደረጃ የምስክር ወረቀት አግኝተዋል። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት ወንዶች ደግሞ 54 በመቶ ናቸው። ይህ በስራው ገበያም ይንጸባረቃል። ምንም እንኳን ሴቶች ብዙውን ጊዜ የተማሩ ቢሆኑም ስራ የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ ነው። ለዚህም አንዱ ምክንያት ወጣት ሴቶች ልጆች ይኖሩዋቸዋል። ልጆቻቸውንም መንከባከብ ይኖርባቸዋል።
ምን ያህል ስደተኞች የጀርመን ዜግነት አገኙ?
ከ2016 ወዲህ ተገን ከጠየቁት 414,000 ሰዎች የጀርመን ዜግነት አግኝተዋል።ከመካከላቸው 244,000 ሶሪያውያን ናቸው።
ሀነስ ሻማን በጀርመኑ የሂልድሻይም ዩኒቨርስቲ የፍልስት ተመራማሪ እንደሚሉት የጀርመን ዜግነት ካገኙት መካከል አንዳንዶቹ አሁን ሀገራቸው መግባት ይፈልጋሉ።
«የምንገኝበት ጊዜ በ2015 የመጡ በርካታ ስደተኞች ዜግነት ያገኙበት ወቅት ነው። ከመካከላቸው አንዳንዶቹ የጀርመን ዜጋ ቢሆኑም የሶሪያ ስደተኞች የቀድሞ መሪያቸው የአሳድ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ ወደ ሀገራቸው ሶሪያ ለመመለስ ያስባሉሆኖም እዚህ ንግድ የከፈቱ ልጆቻቸውም እዚህ የሚማሩ ስለሆነ ለመቆየት የወሰኑም አሉ።»
ጀርመን ስደተኞችን መቀበሏ ምን ያህል ገንዘብ አስወጣት?
ውኅደትን የተመለከቱ ዘገባዎች እንደሚሉት ጀርመን ስደተኞች ለመቀበል የምታወጣው ገንዘብ እንደ ሁኔታው ይለያያል። ወጪው 5.8 ትሪልዮን ዩሮ ነው። እውነታው ምንድነው ስደተኛው አቅም አግኝቶ ጀርመን ከስደተኞች ተጠቃሚ ከመሆንዋ በፊት ከለላ ፍለጋ ጀርመን ሲመጡ መንግስት ገንዘብ ያወጣል። ለምሳሌ በጎርጎሮሳዊው 2023 ከስደተኞች ጋር የተያያዘው ወጪ ከፌደራሉ በጀት ወደ 30 ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ነበር።
በሚያዚያ 2025 ፣ ከተገን ጠያቂዎች 43 በመቶ የሚጠጉት ቁጥራቸው ከአንድ ሚሊዮን በታች ለሆነ ጀርመን ለመሰረታዊ ደኅንነታቸው የፋይናንስ ድጋፍ አድርጋለች። ይህም ለስራ ፈላጊዎችና ራሳቸውን ማስተዳደር ለማይችሉ ሰዎች ከመንግስት የሚሰጥ ማኅበራዊ ድጎማ ነው። ይህ ገንዘብ ደግሞ በ2022 በርካታ ዩክሬናውያን ወደ ጀርመን ሲመጡ ወዲያውኑ በልዩ ሁኔታ መሰረታዊ ማኅበራዊ ድጎማ እንዲደረግላቸው ሲፈቀድ በእጅጉ አሻቀበ። በዚሁ ጊዜ መሰል ድጎማዎችን የሚያገኙ ጀርመናውያን ቁጥር በመጠኑ ቀንሶ ነበር። ያም ሆኖ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች 52 በመቶ ድርሻ ሲኖራቸው
የስደተኞች ምንጭ ከሆኑ ሀገርት የሚመጡት 17 በመቶውን ዩክሪናውያን ደግሞ 13 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ።
በጀርመን የህዝቡ ስሜት እንዴት ተቀየረ ?
የዛሬ 10 ዓመት ስደተኞችን እጁን ዘርግቶ የተቀበለው አብዛኛው ጀርመናዊ ከአስር ዓመት በኋላ ዛሬ ጀርመን ቁጥራቸው አነስተኛ የሆነ ስደተኞችን መቀበል አለባት እያሉ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ፍልሰት አሁን በጀርመን በአሉታዊነት ነው የሚታየው ።በዳሰሳው ከተካተተው 78 በመቶው በማኅበራዊ ድጎማው ላይ ጫና መፍጠሩን ሲናገሩ፤ 63 በመቶው ደግሞ ፍልሰት ለማጣኔ ሀብቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ወንጀል ያስከተለው ስጋት
በስደተኞች የተፈጸሙ ከባድ የተባሉ ወንጀሎች በጀርመን ለስደተኞች ያለው አመለካከት እንዲቀየር ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል። በ216 በበርሊ የገና ገበያ በቱኒዝያዊ የተፈጸመ ጥቃት፣ በዞሊንገን ከተማ በተካሄደ በዓል ላይ በአንድ ሶሪያዊ የደረሰ የስለት ጥቃት ፣ የስደተኞች የሽብር ጥቃት ፍራቻን አስከትሏል። ይህን ጉዳይም ቀኝ ጽንፈኛው AFD የተባለው ፓርቲ ግንባር ቀደም የምርጫ ዘመቻው ርዕስ በማድረግ አtreርፎበታል። ይህም ፓርቲውን ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ በጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ምክር ቤት ሁለተኛውንትልቁ ፓርቲ ለመሆን አስችሎታል።
የጀርመን ፖለቲከኞችም እርምጃዎችን ሚዛናዊ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። በዚህ ዓመት የመንግስት ለውጥ ከተደረገ በኋላ አዲሱ መንግስት ትኩረቱን ስደተኞች በመገደብና በማባረር ላይ አድርጓል። የድንበር ቁጥጥሩን አጥብቋል።በርካቶችንም እየጠረዘ ነው። ።
ከ2015 ዓም ወዲህ በጀርመን የፍልሰት ፖሊሲ እንዴት ተቀየረ?
ሜርክል በ2015 «እንችለዋለን ፤እንወጣዋለን »ካሉ በኋላ የጀርመን የፍልሰት ፖሊሲ ተቀይሯል። ይህም በስደተኞች ስሜት ላይም እየተንጸባረቀ ነው። 57 በመቶው በመጡበት ወቅት ጥሩ አቀባበል ተደርጎልናል ሲሉ ከሰባት ዓመት በኋላ ግን ይህ ስሜት ያላቸeው ቁጥር ቀንሶ 28 በመቶ ሆኗል።
የዛሬ አስር ዓመት እንችላለን ሲሉ ስደተኞችን ያስገቡት ሜርክል በያኔው ውሳኔያቸው የሚተቿቸው አልጠፉም እርሳቸው ግን በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ ውሳኔየ ትክክል ነበር ብለዋል ።ይህን ያደረጉትም በሰብአዊነት መሆኑን ገልጸው ሆኖም ለቀኝ ጽንፈኛው AfD ማንሰራራት አስተዋጽኦ ማ,ድረጉን አልሸሸጉም ።የፍልሰት ተመራማሪው ሻማን እንደሚሉት ጀርመን በ2015 ዓም ጀርመን ከመጡትን ስደተኞች ጉዳይ አብዛኛውን አሳክታለች ። አሁን ለገጠሟታ ችግሮች ደግሞ ብልሀት የተሞላባቸው ፖለቲካዊ መፍትሄዎች መፈለግ ያሻታል ብለዋል ።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ