የሚያዝያ 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2017የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ መውሰዱን ገና አራት ጨዋታዎች እየቀረው አረጋግጦ የነበረው ሊቨርፑል ትናንት በቸልሲ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል ። በደረጃ ሠንጠረዥ ተከታዩ አርሰናልም በገዛ ሜዳው ኤሚሬትስ ስታዲየም በርመስን አስተናግዶ ተሸንፏል ። ማንቸስተር ዩናይትድም በብሬትፎርድ ሲሸነፍ ማንቸስተር ሲቲ ግን ድል ቀንቶታል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቅዳሜ ዕለት ከኤርቤ ላይፕትሲሽ ጋር ሦስት እኩል የተለያየው ባዬርን ሙይንሽን ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት ዋንጫውን መውሰዱን አረጋግጧል ።
አትሌቲክስ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሺያ በተለያዩ የዓለም መድረኮች ለድል በቅተዋል ። በሚያሚ ግራንድ ስላም የሴቶች ፉክክር ፍሬወይኒ ኃይሉ አሸንፋለች ። በረጅም ርቀት አትሌት ሂሩት መሸሻ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች ። በ1500 ሜትር አንደኛ የወጣችው አትሌት ፍሬወይኒ በ800 ሜትር በተካሄደው ውድድር ሦስተኛ በመውጣት ስድስት ነጥብ በማግኘት በአጠቃለይ በ18 ነጥብ የአጭር ርቀትን አሸንፋለች ።
ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ለሚ ብርሃኑ እና ብርቱካን ወልዴም ቼክ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ፕራግ ውስጥ ትናንት በተካሄደው የማራቶን ውድድር በየዘርፋቸው አሸናፊ ሁነዋል ። በወንዶች ማራቶን ውድድር አትሌት ለሚ ብርሃኑ 2:05.14 በመግባት ለድል በቅቷል ። በሴቶች ማራቶን ውድድር አትሌት ብርቱካን ወልዴ 2:20.55 በመሮጥ በአንደኝነት አሸናፊ ሁናለች ።
በሻንጋይ የዳይመንድ ሊግ ውድድር በወንዶች 5000 ሜትር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት አሸናፊ ሁነዋል ። አትሌት በሪሁ አረጋዊ በ12:50.45 አንደኛ፤ አትሌት ኩማ ግርማ 12:50.69 ሁለተኛ፤ እንዲሁም አትሌት መዝገቡ ስሜ በ12:51.86 ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። በሴቶች 800 ሜትር ደግሞ አትሌት ጽጌ ዱጉማ 1 ደቂቃ 56.64 ሰከንድ በመሮጥ አሸናፊ ሁናለች ። የሚያዝያ 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል ተብሎ የነበረው 54ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፉክክር በመሮጫ መም ችግር የተነሳ የመወዳደሪያ ቦታ እንደሚቀየር ተገልጧል ። ለመሆኑ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይስተካከላል የተባለው የመሮጪያ ቦታ ለበርካታ ወራት ሳይቀየር እንደውም ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ ላይ የተገኘውለምን ይሆን? የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ኢትዮ ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ።
እግር ኳስ
የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ አስቀድሞ መውሰዱን ያረጋገጠው ሊቨርፑል በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት ዘመን ከባዱን ሽንፈት ትናንት አስተናግዷል ። በባከነ ሰአት ኳንሳ በፈፀመው ስህተት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ጨምሮ ቸልሲ ሊቨርፑልን 3 ለ1 አሸንፏል ። በትናንቱ ግጥሚያ እድል የራቀው የሊቨርፑሉ ተከላካይ ኳንሳ በገዛ መረቡ ላይ ሁለተኛው ግብ እንዲቆጠረም ሰበብ ነበር ። ኳሷን ከቸልሲ ጫና ለማራቅ ተከላካዪ ቫን ጂክ ሲመታ ኳንሳ ፊት ለፊት ተደርቦ በገዛ መረቡ ላይ አስቆጥሯል ።
በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ተጋጥሞ ወሳኝ ድል ያስመዘገበው ቸልሲ አሁን የሻንፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን እደወሉን ከፍ አድርጓል ። ቸልሲ የትናንት ድሉን ጨምሮ በሰበሰበው 63 ነጥብ ከኒውካስል ጋር በግብ ክፍያ ብቻ በመበለጥ አምስተኛ መሆን ችሏል ። የመጋቢት 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የቀድሞ የሊቨርፑል ተጨዋች ማይክል ኦዌን ቸልሲ ሊቨርፑል ዋንጫ መውሰዱን ካረጋገጠ በኋላ መግጠሙ ዕድለኛ ነው ብሏል ። በተለይ ከረፈት መልስ ሊቨርፑል ጫና ፈጥሮ ቢጫወትም ዋንጫውን መውሰዱን በማረጋገጡ ያን ያህል ሲታገል ዐልታየም ብሏል ። በእርግጥም ትናንት ለዋንጫ የሚጫወት ይመስል ከነበረው ቸልሲ አንፃር ሊቨርፑል ጨዋታውን ቀለል አድርጎ ታይቷል ።
ቸልሲ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ ባለድል መሆናቸውን ያረጋገጡ ሁለት ቡድኖችን በማሸነፍ ታሪክ ሠርቷል ። ቸልሲ ከ12 ዐመት በፊትም የዋንጫ ባለድል መሆኑን ያረጋገጠው ማንቸስተር ዩናይትድን አሸንፎ ነበር ። ዋንጫውን መውሰዳቸውን አስቀድመው ካረጋገጡ በኋላ ሽንፈት ከደረሰባቸው ቡድኖች መካከል ደግሞ የሊቨርፑል የትናንት ሽንፈት አራተኛው መሆኑ ነው ።
አርሰናል በሜዳው ተጫውቶ በበርመስ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል ። ዌስትሀም ዩናይትድ እና ቶትንሀም አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በብሬንትፎርድ 4 ለ3 ተሸንፏል ። በአንጻሩ ማንቸስተር ሲቲ ዎልቭስን 1 ለ0 አሸንፏል ። ዛሬ ማታ ክሪስታል ፓላስ ከኖቲንግሀም ፎረስት ጋር ይጋጠማሉ ።
ሊቨርፑል፣ አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ኒውካስል እና ቸልሲ የሻምፒዮንስ ሊግ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል ። ኢፕስዊች ታወን፣ ላይስተር ሲቲ እና ሳውዝሀምፕተን ወራጅ መሆናቸው ተረጋግጧል ።
አሌክሳንደር አርኖል ከልጅነት ቡድኑ ሊቨርፑል ሊለይ መሆኑ ይፋ ሁኗል፤ ምናልባትም ለሪያል ማድሪድ ሊጫወት ይችል ይሆናል ተብሏል ። የባዬርን ሌቨርኩሰን አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ የስኬት ቆይታ በኋላ ከቡንደስሊጋው ሊለይ መሆኑ ተገልጧል ። ወደ አገሩ ስፔን አቅንቶም ሪያል ማድሪድን ሊያሰለጥን ይችል ይሆናል ተብሏል ። እንደተባለው አሌክሳንደር አርኖልድ እና ዣቪ አሎንሶ ወደ ሪያል ማድሪድ የሚያቀኑ ከሆነ የቀድሞው የሊቨርፑል ተጨዋቾች በአንድ ቡድን በአሰልጣኝ እና ተጨዋችነት ይከሰታሉ ማለት ነው ። የመጋቢት 22 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ቅዳሜ ዕለት በኤርቤ ላይፕትሲሽ ሜዳ ተጋጥሞ ሦስት እኩል የተለያየው ባዬርን ሙይንሽን ዋንጫውን መውሰዱን አረጋግጧል ። ባዬርን ሙይንሽን፣ ባዬር ሌቨርኩሰን፣ አይንትራኅት ፍራንክፉርት እና ፍራይቡርግ ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ቦታ ይዘዋል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአምስተኛ ደረጃ የአውሮጳ ሊግ ተሳታፊ ቦታን ይዟል ። ኤርቤ ላይፕትሲሽ በበኩሉ የአውሮጳ ሊግ የደርሶ መልስ ተጋጣሚ ቦታን ይዟል ። የነጥብ ልዩነቶቹ ተቀራራቢ በመሆናቸው ደረጃዎቹ ሊቀያየሩ ይችላሉ ። ሆልሽታይን ኪዬል እና ቦሁም ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ሐይድንሀይም ወራጅ ቀጣናው ግርጌ ከሁለቱ ቡድኖች በቅርብ ርቀት መገኘቱ የነዚህ ቡድኖች ቀጣይ ጨዋታዎችን አጓጊ ያደርገዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ