የሚያዝያ 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2017ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ መውሰዱን ገና አራት ጨዋታዎች እየቀሩት አረጋግጧል ። በላሊጋው በቀዳሚነት የሚገሰግሰው ባርሴሎና ደግሞ የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫን ከሪያል ማድሪድ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ መንትፏል ። በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ በተሰጠው የለንደን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ ክብረ-ወሰን በመስበር ጭምር አሸናፊ ሁናለች ። የፓሪስ ኦሎምፒክ የማራቶን ባለድሉ ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ በተሳተፈበት የወንዶች ፉክክር ግን ድሉ የኬንያውያን አትሌቶች ሁኗል ። ተጨማሪ ዘገባዎችንም አካተናል፥
አትሌቲክስ
ለንደን ውስጥ እሁድ የሚያዝያ 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በተከናወነው በለንደን ማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ የዓለም ክብረወሰንን ጭምር በማሻሻል አሸንፋለች ። ትእግስት አሸናፊ የሆነችው የበቃችው ርቀቱን 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ ሮጣ በመግባት ነው ። የሴቶች ማራቶን የምንጊዜም ክብረ-ወሰን ተይዞ የቆየው በኬንያዊቷ ሯጭ ሩትዝ ቼፕንጊትች ነበር ።
ሩትዝ ባለፈው ዓመት የቺካጎ ማራቶን ውድድርን ያጠናቀቀችው 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ በመሮጥ ነበር፥ ከትናንቱ የትእግስት ሰአት ልዩነቱ የስድስት ሰከንድ ነው ። የባለፈው ዓመት የለንደን ማራቶን ባለድል ደግሞ ኬንያዊቷ ፔሬስ ጂፕቺርቺር ነበረች ። ፔሬስ 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ16 ሰከንዶች በመሮጥ የሴቶች ብቻ የዓለም ክብረ ወሰንን ባስመዘገበችበት ወቅት ትዕግሥት አሰፋ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታ ነበር ። ትናንት ደግሞ የለንደን ብቻ ሳይሆን የሴቶች የምንጊዜም ክብረወሰንን ሰብራለች ።
የሁለተኛ ደረጃውን ከትእግስት በሁለት ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ተቀድማ ያገኘችው ኬንያዊቷ አትሌት ጆይሲሊን ጄፕኮስጊ ናት ። በትናንቱ የለንደን ማራቶን ውድድር ታሸንፋለች በሚል ቅድመ-ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ትውልደ ኢትዮጵያ ኔዘርላንዳዊቷ አትሌት ሲፈን ሐሰን ከትእግስት ሦስት ደቂቃ ከዐሥር ሰከንዶች ዘግይታ በመግባት (በ2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ) ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ኢትዮጵያዊቷ ሄቨን ኃይሉ አራተኛ ወጥታለች።
በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ በተሰጠው የወንዶች ለንደን ማራቶን ፉክክር ግን ኬንያዊው አትሌት ሰባስቲያን ኪማሩ ሳዌ ርቀቱን 2 ሰአት ከ2 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ በማጠናቀቅ ለድል በቅቷል ። ኡጋንዳዊው አትሌት ጄኮብ ኪፕሊሞ ከሰባስቲያን በአንድ ደቂቃ ከዐሥር ሰከንድ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሌላኛው ኬኒያዊ አትሌት አሌክሳንደር ሙንያዎ የአገሩ ልጅን በአንድ ደቂቃ ከ53 ሰከንድ ተከትሎ በሦስተኛነት አጠናቋል ። ትውልደ ሶማሊያው ኔዘርላንዳዊ ሯጭ አብዲ ናጊዬ ከአሌክሳንደር እኩል ሰአት ገብቶ የአራተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የፓሪስ ኦሎምፒክ የማራቶን ባለድሉ አትሌት ታምራት ቶላ 2 ሰአት ከ4 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ በመግባት አምስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ በዐሥረኛ ደረጃ (2:09:01)አጠናቅቋል ።
እግር ኳስ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት ቦሁም ከዑኒዮን ቤርሊን ጋር አንድ እኩል ቬርደር ብሬመን ከሳንክት ፓውሊ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል ። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች፦ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ላይፕትሲሽን 4 ለ0 ጉድ አድርጓል ። ቮልፍስቡርግ በፍራይቡርግ የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ። መሪው ባዬርን ሙይንሽን ሜዳው አሊያንትስ አሬና ውስጥ ማይንትስን 3 ለ0 ድል አድርጓል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሆፈንሀይምን 3 ለ2 ሲያሸንፍ፤ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ በ17ኛ ደረጃ በሚዳክረው ሆልሽታይን ኪዬል የ4 ለ3 ያልተጠበቀ ሽንፈት ገጥሞታል ። ከባዬርን ሙይንሽን በስምንት ነጥብ ተበልጦ በ67 ነጥቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባዬር ሌቨርኩሰን አውግስቡርግን 2 ለ0 ድል አድርጓል ።
የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ
የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ገና ሳይጠናቀቅ ሊቨርፑል የዋንጫ ባለድል መሆኑን ከወዲሁ አረጋግጧል ። የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አሰልጣኝነት አዲስ ታሪክ አስመዘገቡ ። ምንም እንኳን ኔዘርላንዳውያን አሰልጣኞች በአውሮጳ ሊጎች ስኬታማ ቢሆኑም፦ የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ግን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ታሪክ ቡድናቸውን ለዋንጫ ድል በማብቃት የመጀመሪያው ኔዘርላንዳዊ ሆነዋል ። የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም፤ የስፖርት ዝግጅት
የ46 ዓመቱ አሰልጣኝ፦ ሊቨርፑል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከአራት ዙር ጨዋታዎች አስቀድሞ ዋንጫውን ማንሳቱን እንዲያረጋግጥ አስችለዋል ። በእርግጥም ከጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ አንድን ቡድን መረከብ ሁልጊዜም እጅግ ፈታኝ ነው ። ሆኖም ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ እንደውም የተሻሉ ተተኪ አሰልጣኝ መሆናቸውን አስመስክረዋል ። በዚህ ድላቸውም ከኔዘርላንድ ውጪ ያሰለጠኗቸው ቡድኖቻቸው ዋንጫ እንዲያገኙ ማብቃት ከቻሉ አሰልጣኞች ተርታ ተሰልፈዋል ።
አሰልጣኝ ሪኑስ ሚሼልስ፣ ዮሐን ክሩይፍ፣ ሌዎ ቤንሐከር፣ ሉዊ ቫን ጋል እና ፍራንክ ሪክያርድ ከኔዘርላንድ ውጪ ቡድኖቻቸው ለዋንጫ ድል ያበቁ አሰልጣኞች ናቸው ። አሰልጣኝ ዮሐን ክሩይፍ እና ፍራንክ ሪክያርድ የስፔን ሊግ ዋንጫ አሸናፊዎች ነበሩ ። ከሁለት ሳምንት በፊት ሰኞ በ82 ዓመታቸው ያረፉት ሌዎ ቤንሐከር ደግሞ በላሊጋው የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ሁነው ቡድናቸውን ለዋንጫ ማብቃት ችለዋል ።
ሌላኛው አሰልጣኝ ሉዊ ቫን ጋል በስፔን ላሊጋ ባርሴሎናን እንዲሁም በጀርመን ቡንደስሊጋ ባዬርን ሙይንሽንን ለድል በማብቃት ስማቸው የገነነ ነው ። ሆኖም ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የማንቸስተር ዩናይትድ የሁለት የጨዋታ ዘመን ቆይታቸው የተሰናበቱት ገናና ስማቸው ጠልሽቶ ነው ። ልክ እንደ ሉዊ ቫን ጋል ሁሉ ሌላኛው የኔዘርላንድ አሰልጣኝ ሩድ ቫን ኒስተርሎይ በፕሬሚየር ሊጉ ስኬት ርቋቸዋል ። ያም ብቻ አይደለም ባለፉት 12 ግጥሚያዎቹ በዐሥራ አንዱም ማሸነፍ የተሳነው ቡድናቸው ላይሰር ሲቲ ወራጅ ቃጣናው ውስጥ እጣ ፈንታውን ይጠባበቃል ።
የኔዘርላንዳዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ስኬት
በነገራችን ላይ እነ ፍራንክ ደ ቦይር፣ ሩድ ጉሊት፣ ጉስ ሒድኒክ፣ ዲክ አድቮካት እና ሮናልድ ኮይማን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አሰልጣኝነት ተፈትነው የወደቁ የኔዘርላንድ አሰልጣኞች ናቸው ። ከነዚህ ሁሉ ኔዘርላንዳውያን አሰልጣኞች መካከል ግን አንዱ ጎልማሳ ተሳክቶላቸዋል ። አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ። በቀያዮቹ ደጋፊዎቹ ጢም ብሎ በሞላው አንፊልድ ስታዲየሙ ውስጥ ሊቨርፑል ቶትንሀም ሆትስፐርን 5 ለ1 ሲያደባይ ዋናው ሰው ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ነበሩ ። ሊቨርፑል የትናንት ድሉ 20ኛ የዋንጫ ድሉ ሁኖ ተመዝግቦለታል ።
አምስቱን ግቦች ሉዊስ ዲያዝ፣ አሌክሲስ ማክ አሊስተር፣ ኮዲ ጋክፖ እና የግብ ቀበኛው መሐመድ ሣላኅ ከመረብ አሳርፈዋል ። የሊቨርፑልን ብርቱ የማጥቃት ጫና መቋቋም የተሳነው ቶትንሀም ሆትስፐር በግራ ተመላላሹ ዴስቲኒ ኡዶጂ ስህተት አምስተኛ ግብ በገዛ መረቡ ላይ ተቆጥሮበታል ። ብቸናዋን የማጽናኚያ እና ቀዳሚ ግብ በ12ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ዶሚኒክ ሶላንኬ ነው ።
ሆኖም ሊዊስ ዲያዝ ብዙም ሳይቆይ በአራት ደቂቃ ውስጥ ሊቨርፑልን አቻ ካደረገ በኋላ ቶትንሀም ሆትስፐር የቀያዮቹን ውርጅቢኝ መቋቋም ተስኖት 5 ለ1 ተፍረክርኳል ። በዚህም ሊቨርፑል ከእንግዲህ ማንም ሊደርስበት የማይችለውን 82 ነጥብ በመሰብሰብ ዋንጫውን ከወዲሁ መውሰዱን አረጋግጧል ። ያም ብቻ አይደለም ። ግብጻዊው ግብ አዳኝ ሞሐመድ ሳላኅ በ28 ከመረብ ያረፉ ኳሶቹ በኮከብ ግብ አግቢነት የሚደርስበት አልተገኘም ። የኒውካስሉ አሌክሳንደር ኢሳቅ በ22 እንዲሁም የማንቸስተር ሲቲው ኧርሊንግ ኦላንድ በ21 ሞሐመድ ሣላኅን ይከተሉታል ።
ሊቨርፑል በቀጣይ አራት ጨዋታዎች ከቸልሲ፣ ከአርሰናል፣ ከብራይተን እና ክሪስታል ፓላስ ጋር ይጋጠማል ። ጨዋታዎቹ ዋንጫ መውሰዱን ላረጋገጠው ሊቨርፑል የሚቀይረው ነገር የለም ። ለብዙዎቹ ግን እጅግ ወሳኝ ግጥሚያ ነው ። የሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም. የስፖርት ዝግጅት
አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ በቀጣ የሻፕሚዮንስ ሊግ ተሳታፊ ከሚሆኑ አምስት የፕሬሚየር ሊግ ቡድኖች መካከል ላለመውጣት ከሊቨርፑል ጋር የሞት ሽረት ግጥሚያ ማድረጉ የማይቀር ነው ። ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል 67 ነጥብ ቢኖረውም ስድስተኛ ደረጃ ላይ ያለው ኖቲንግሀም ፎረስት እንደ ቸልሲ 60 ነጥብ አለው ። 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አስቶን ቪላም በ57 ነጥቡ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የመግባት እድሉ ገና አልተጨናገፈም ። አርሰናል በቀጣይ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ሁለት ጨዋታዎችን የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። ስለዚህ ከሊቨርፑል ጋር የሚያደርገው ጨዋታው ለአርሰናል የሞት ሽረት ነው ።
እንደ ፉልሀም ሁሉ 51 ነጥብ ያለው ብራይተንም ቢሆን በሻምፒዮንስ ሊግ አለያም በአውሮጳ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን አራቱንም ግጥሚያዎቹን አሸንፎ የሌሎቹን መሸነፍ ይጠብቃል ። 45 ነጥብ ሰብስቦ 12ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ክሪስታል ፓላስ ግን ከሊቨርፑልም ጋር ሆነ ከሌሎች ቡድኖች ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎችን አሸነፈም ተሸነፈም የሚፈይድለት ነገር አይኖርም ።
ባርሴሎና የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫ ባለድል
እጅግ ድንቅ በሆነ ቀዳሚ ግብ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ በስፔን የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫ ድልን ከባርሴሎና ጋር ተቀዳጁ ። ለባርሴሎና ቀዳሚዋን ግብ በ28ኛ ደቂቃ ላይ ከርቀት አክርሮ በመምታት በድንቅ ሁኔታ ከመረብ ያሳረፈው ፔድሪ ነው ። ኳሷን ሰባት ተጨዋቾች ለመከላከል ከተደረደሩበት መሀል አሳልፎ ለፔድሪ ያቀበለው ላሚና ያማል ብቃቱን ዐሳይቶበታል ። ከረፍት መልስ በ70ኛ ደቂቃ ኬሊያን እምባፔ አቻ የምታደርገውን ግብ እስካስቆጠረ ድረስ ሪያል ማድሪድ አንድ ለዜሮ እየተመራ ነበር ። ኬሊያን እምባፔ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል አቅራቢያ ተጠልፎ የተገኘውን ቅጣት ምት ራሱ መትቶ ግሩም በሆነ ሁኔታ ከመረብ አሳርፏል ። የባርሴሎናን አሸናፊነት መንፈስ ላይ ውኃ የቸለሰ አጋጣሚ፥ የሪያል ማድሪዶችን ያነቃቃ አጋጣሚ ።
አፍታም ሳይቆይ በ77ኛው ደቂቃ ላይ አውሬሊየን ቾውሚኒ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሮ ድሉ የሪያል ማድሪድ መሰለ ። አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ኬሊያን እምባፔን ከተቀያሪ ወንበር ወደ ሜዳ ማስገባታቸው በእርግጥም ፍሬ ማፍራቱን ዐሳይቷል ። ቢያንስ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ ። የመጋቢት 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
84ኛው ደቂቃ ላይ የባርሴሎናን ተስፋ ያንሰራራ ግብ በፌራን ቶሬስ ተቆጠረ ። ኳሷን እንደተለመደው ዙሪያውን ከከበቡት ተጨዋቾች መሐከል አሾልኮ ለፌራን ያቀበለው ላሚና ያማል ነው ። ፌራን ቶሬዝ ተከላካዩ ሩዲገር እና ግብ ጠባቂው ቲቦ ኮቱዋን አታሎ ኳሷን ከመረብ አሳርፏል ። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪውም ሁለቱ ኃያላን ቡድኖች ሁለት እኩል እንደሆኑ ዘለቁ ። አሁን ጨዋታው በአቻ ተጠናቅቆ ወደ መለያ ምት ማምራቱ አይቀርም የሚለው የብዙዎች ግምት ሆነ ።
የሁለቱም ቡድን ተጨዋቾች ተዳክመዋል ። ምናልባትም የመለያ ምቱ ቶሎ በደረሰ ይሉም ይሆናል ። ሁሉም ነገር ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ ። ጁሌስ ኩንዴ በሴቪያ ሰማይ እኩለ ሌሊት የባርሴሎና ደጋፊዎችን ያስፈነጠዘውን ግብ አስቆጠረ ። ርችቱ ተንቦገቦገ ። ተጨዋቾቹ ጁሌስ ኩንዴን ለማቀፍ ሜዳውን ወረሩት ። ስታዲየሙ በደስታ ተደበላለቀ ። በዚያ ግን አላበቃም ።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ኬሊያን ምባፔ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ወደቀ ። የመሐል ዳኛው ጣታቸውን ለፍጹም ቅጣት ምት ሲያመለክቱ የመሥመር ዳኛው ግን ባንዲራቸውን ከፍ አድርገው ነበር፤ ከጨዋታ ውጪ ምልክት ለማሳየት ። ፍጹም ቅጣት ምቱም ሳይሰጥ የመሐል ዳኛው ፊሽካቸውን ነፉ፥ ጨዋታ ተጠናቀቀ ።
ሪያል ማድሪዶች አበዱ ። በተለይ ወደ መጨረሻ አካባቢ ተቀይሮ የወጣው አንቶኒዮ ሩዲገር ንዴቱን መቆጣጠር አቅቶት ለተጎሻሸመ ሰውነቱ የተሰጠውን በላስቲክ የተከማቸ በረዶ ወደ ዳኛው በተነ ። እናም በተፈጠረው ትርምስ ሦስት የሪያል ማድሪድ ተጨዋቾች ቀይ ካርድ ተሰጣቸው ። የስፔኑ ተከላካይ ሉቃስ ቫስኩዌዝ፣ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተከላካዩ አንቶኒዮ ሩዲገር እና የእንግሊዙ አማካይ ጁድ ቤሊንግሀም ። ምናልባትም አንቶኒዮ ሩዲገር ባሳየው ጠባይ ከበድ ያለ ቅጣትም ሊጠብቀው ይችላል ።
በላሊጋውም ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ በአራት ነጥብ ርቆ በ76 ነጥብ ይመራል ። ከቀሪ አምስት ጨዋታዎቹ በሁለተኛው የፊታችን እሁድ ሳምንት ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ ጋር ዳግም ይገናኛል ። ሪያል ማድሪድ የኮፓ ዴል ሬይ ሽንፈቱን ለመበቀል ብቻ ሳይሆን የላሊጋውን ዋንጫ ላለማጣት በባርሴሎና ላይ የተሳሉ ጥርሶቹን ይበልጥ ሞርዶ ነው ወደ ሜዳ የሚገባው ። የኮፓ ዴል ሬይ አሸናፊው ማለትም ባርሴሎና እና ተከታዩ ሪያል ማድሪድ፤ እንዲሁም ከላሊጋው የዋንጫ አሸናፊ እና ሁለተኛ የሚወጣው ቡድን በስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫ ግጥሚያ ይፋለማሉ ። ያው እኒሁ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ መሆናቸው ነው ።
በነገራችን ላይ በሴቶች እግር ኳስ ግጥሚያም ባርሴሎና ቸልሲን 4 ለ1 በድምሩ 7 ለ1 ድል አድርጎ ለዋንጫ ፍጻሜ አልፏል ። በደርሶ መልስ ኦሎምፒክ ሊዮንን ስድስት ለአንድ ረትቶ ለፍጻሜ ከደረሰው የእንግሊዙ አርሰናል ጋር ባርሴሎና ከሦስት ሳምንት በኋላ ለዋንጫ ይፋለማል ። ባርሴሎና ዳግም በሴቶቹም ይቀናው ይሆን?
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሐይ ጫኔ