ባህርዳር-አማራ ክልል የግንባታ ሥራ ቀዝቅዟል፣ ሰራተኞች ተቸግረዋል
የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር ኃይልና የፋኖ ታጣቂዎች በአማራ ክልል የገጠሙት ጦርነት የክልሉን ህዝብ ምጣኔ ሐብታዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ እየጎዳዉ ነዉ።በክልሉ በተለይ በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሐብቶችና ሠራተኞች እንደሚሉት በርካታ ባለሐብቶች ክልልሉን እየለቀቁ ሸሽተዋል፣ እዚያዉ የሚገኙ ባለሐብቶችና ሠራተኞችም ሥራ አጥተዋል። ባህር ዳር ዉስጥ የሚኖሩ አንድ ባለሙያ እንዳሉት ደግሞ ሥራ ከለቀቁ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል።በየግንባታ ኩባንያዉ ይሠሩ የነበሩ ባለሙያዎች፣ የቀን ሰራተኞች፣ የግንባታ ቁሳቁስ አቅራቢዎች ሥራ በማቆማቸዉ ገቢ አጥተዉ መቸገራቸዉን አስታዉቀዋል።በአማራ ክልል ሁለተኛ ዓመቱን ባገባደደዉ ጦርነት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።በሺሕ የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል።በጦርነቱ ምክንያት የበርካታ የክልሉ ወረዳዎች የጤና፣ የትምህርት፣ የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ተቋርጠዋል ።
ናይሮቢ-የUSAID ርዳታ መቋረጥ ሐኪም ቤት ሊዘጋ ነዉ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ USAID በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉን የአሜሪካ የርዳታ ድርጅትን በመዝጋታቸዉ አፍሪቃ ዉስጥ በመድሐኒት እጦት የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ተነገረ።የሕክምና ባለሙያዎችና የርዳታ ድርጅቶች እንዳሉት USAID የሚሰጠዉ መድሕኒትና የህክምና መሳሪዎች በመቋረጣቸዉ ሐኪም ቤቶች እየተዘጉ፣ ሠራተኞች እየተባረሩ፣ ሕሙማንም እየተሰቃዩና እየሞቱ ነዉ።ቱርካና የተባለዉ የኬንያ ሰሜናዊ ግዛት የሆስፒታል ሐላፊ ኢኪሩ ኪዳሊዮ እንደሚሉት ሆስፒታላቸዉ በተለይ ለኩፍኝና ለHIV-ኤድስ ሕሙማን የሚሰጠዉ መድሐኒት አልቆበታል።
ጁባ-5 ሕፃናት በርዳታ እጦት በኮሌራ ሞቱ
የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF)ና የብሪታንያዉ ግብረ ሠናይ ድርጅት (Save the Children) እንዳስታወቁት ደግሞ የአሜሪካ ርዳታ በመቋረጡ ልጆች በኮሌራ በሽታ እየሞቱ ነዉ።ሴቭ ዘ ችልድረን እንዳለዉ ርዳታዉ በመቋረጡ ምሥራቃዊ አኮቦ ግዛት ዉስጥ ከነበሩት 27 ክሊኒኮች 7ቱን ዘግቷል።ከ600 መቶ የሕክምና ባለሙያዎች 200ዉን ቀንሷል።የጤና አገልግሎቱ በተቋረጠባቸዉ አካባቢዎች ከሚኖሩ የኮሌራ ሕሙማን 5 ልጆች ሰሞኑን ሕክምና ለማግኘት ረጅም ርቀት ሲጓዙ መንገድ ላይ ሞተዋል።የዩናይትድ ስቴትሱ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅት USAID በዓመት 43 ቢሊዮን ዶላር በጀት ነበረዉ።ድርጅቱ የሚሰጠዉ ሰብአዊ ርዳታ ከዓለም አጠቃላይ የሰብአዊ ርዳታ 40 በመቶዉን ይሸፍን ነበር
ካይሮ-የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የመን ዉስጥ 10 ሰላማዊ ሰዎች ገደለ 16 አቆሰለ-TV
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በየመን የወደብ ከተማ ሁዴይዳሕ ላይ ትናንት በከፈተዉ የአየር ድደባ በትንሹ 9 ሰላማዊ ሰዎች ገደለ፤ ሌሎች 16 አቆሰለ።የጀርመኑ ዜና አገልግሎት DPA ከሁቲ ቡድን ጋር ግንኙነት አለዉ የሚባለዉን አል-ማሲራሕ ቴሌቪዥን ጣቢያን ጠቅሶ እንደዘገበዉ የአሜሪካ ጦር የሁዴይዳሕን መኖሪያ አካባቢዎች ደብድቧል።ጦሩ ከሁዴይዳሕ በተጨማሪ ርዕሠ ከተማ ሰነዓንና ኢብድ አዉራጃን መደብደቡም ተዘግቧል።በሁለቱ አካባቢዎች የተገደለ ሰዉ ግን የለም።የሁቲ ተዋጊዎች ባንፃሩ አል ጆፍ በተባለዉ ግዛት ዛሬ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ሰዉ አልባ የጦር አዉሮፕላን(ድሮን)መትተዉ መጣላቸዉን አስታዉቀዋል።ሁቲዎች ባንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ የአሜሪካንን ሰዉ አልባ አዉሮፕላን መትተን ጣልን ሲሉ የዛሬዉ ሶስተኛቸዉ ነዉ።የአሜሪካ ጦር አዉሮፕላኖቹ ሥለመመታታቸዉ የሰጠዉ ማረጋገጪያ፣ ማስተባበያም የለም።
ዴር አል በላሕ-የእስራኤል ጦር ጋዛ ዉስጥ 23 ፍልስጤሞች ገደለ
የእስራኤል ጦር ዛሬ ጋዛ ሰርጥ ላይ በከፈተዉ የዓየር ጥቃት 23 ፍልስጤሞችን ገደለ።የአሜሪካዉ ዜና አገልግሎት አሶስየትድ ፕሬስ አል አሕሊ የተባለዉ ሆስፒታል ጠቅሶ እንደዘገበዉ ከሟቾቹ ዉስጥ 8ቱ ሴቶች፣ 8ቱ ልጆች ነበሩ።የጋዛ የጤና ሚንስቴርም የእስራኤል የጦር ጄቶች ሺጃያሕ በተባለዉ ቀበሌ የነበረ አንድ ባለ 4 ደርብ መኖሪያ ሕንፃን አዉድሞ 23 ሰላማዊ ሰዎች መግደሉን አረጋግጧል።የእስራኤል ጦር አካባቢዉን የደበደበዉ አንድ የሐማስ ባለሥልጣን ለመግደል እንደሆነ አስታዉቋል።የባለሥልጣኑን ሥምም ሆነ በጥቃቱ ሥለመገደል አለመገደሉ ግን እስከ ማምሻዉ ድረስ ያለዉ የነገር የለም።
በርሊን-የጀርመን ተጣማሪ መንግስት ሥምምነት
የጀርመን ወግ አጥባቂ የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ሕብረት/ክርስቲያን ሶሻል ሕብረት (CDU/CSU)ና የመሐል ግራዉ የሶሻል ዴሞክራቶች (SPD) ፓርቲዎች ተጣማሪ መንግስት ለመመሥረት ተስማሙ።ባለፈዉ የካቲት በተደረገዉ አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያና የሶስተኝነት ደረጃን የያዙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጣማሪ መንግስት ለመመሥረት ለ6ሳምንታት ሲደራደሩ ነበር።የተጣማሪዉ መንግሥት መራሔ መንግስት ይሆናሉ ተብለዉ የሚጠበቁት የክርስቲያን ዴሞክራቶቹ ሕብረት (CDU) መሪ ፍሬድሪሽ ሜርስ ዛሬ እንዳስታወቁት መንግስታቸዉ ጀርመንን ከገጠማት ችግር ለማዉጣት፣ ሕዝቧን ለማስደሰት አበክሮ ይጥራል።
«በሐገራችን አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ እንዳለን እናዉቃለን።ይሁንና የድርድሩ ሒደት፣የድርድሩ ዉጤትና ዛሬ የምናቀርበዉ የተጣማሪ መንግስት ስምምነት ከዚሕ ችግር መዉጣት እንደምንችል ለኔ በግሌ መታመኛ ሆኖኛል። ዳግም ብርቱ፣ጠንካራና አስተማማኝ ሐገር መሆን እንፈልጋለን።ዜጎችዋ ሥራቸዉን የሚወዱባት፣በማሕበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መሳተፋቸዉን የሚወዱባት ሐገር እንድንሆን እንፈልጋለን።ባጭሩ ባለፈዉ ጊዜ ከነበረዉ የተሻለ የምትሆን ሐገር መሆን እንፈልጋለን።»
ተጣማሪዉ መንግስት የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ለማሳደግ፣ የመከላከያ ኃይሉን ለማጠናከር፣ በስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ለማድረግ በሚረዱ መርሆች ላይ ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል።
ቤጂንግ/ዋሽግተን-የዩናይትድ ስቴትስና የዓለም የንግድ ጦርነት ተባብሷል
ዩናይትድ ስቴትስ በንግድ ተሻራኪዎችዋ ሐገራት ሸቀጦች ላይ የጣለችዉ የቀረጥ ጭማሪ የዓለምን የንግድ ሥርዓት እያቃወሰዉ ነዉ።የቀረጥ ጭማሪዉ የተለያዩ የአክሲዮን ገበያዎች፣ የነዳጅና የከባድ ሸቀጦችን ዋጋ፣ ዝዉዉርና ገበያን አዘበራርቆታል።የአዉሮጳ ሕብረት፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጅ ማሕበርና መንግሥታት ባንድ በኮል አፀፋ ጭማሪ ለማድረግ ሲዘጋጁ በሌላ በኩል የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን «ልብ ለማራራት» ከትራምፕ መስተዳድር ጋር ለመደራደር እየጠየቁ ነዉ።የዓለም ሁለተኛ ሐብታም ቻይና ግን ዛሬ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሐገሯ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የ84 በመቶ ጭማሪ አድርጋለች።ቻይና ባለፈዉ ሳምንት አርብ እንዳስታወቀችዉ ከአሜሪካ በምታስገባቸዉ ሸቀጦች ላይ ለመጨመር ያቀደችዉ ቀረጥ 34 በመቶ ብቻ ነበር።የትራም መስተዳድር በቻይና ሸቀጦች ላይ የጣለዉ ቀረጥ ወደ 104 ከመቶ ሲደርስ ግን ቻይናም የ50 በመቶ ጭማሪ አድርጋ አጠቃላይ ቀረጡን 84 ከመቶ አድርሳዋለች።የቻይና የንግድ ሚንስቴር ዛሬ እንዳለዉ ዩናይትድ ስቴትስ በቻይና ላይ የንግድና የኤኮኖሚ ገደብ መጣሏን ከቀጠለች ቻይና ለአፀፋ እርምጃ ፅኑ ፍላጎት፣ ዝግጅትና አቅሙ አላት።
ቤጂንግ-የሁለቱ ሐብታም ሐገራት ወታደራዊ ፍጥጫም እንደቀጠለ ነዉ
የዓለም አንደኛና ሁለተኛ ሐብታም ሐገራት ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና በፖለቲካና ወታደራዊ መሥክ የገጠሙት እሰጥ አገባም እየባሰ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ፔት ሐግሴት በቅርቡ ቻይና ጃፓንንና ደቡብ ኮሪያን ታስፈራራለች፣ ዩናይትድ ስቴትስ የፓናማ ወደብን ለመጠቅለል የምታደርገዉን ጥረት ታደናቅፋለች በማለት ወንጅለዋል።ሚንስትሩ ከቤጅንግ «ሊሰነዘር የሚችል» ያሉትን «ሥጋት» ለመቋቋም ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቿ «ዝግጁ ናቸዉ» ብለዋልም።የቻይ መከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ዣንግ ሺኦጋንግ አሜሪካንን በስም ሳይጠቅሱ የሚመለከታቸዉ ያሏቸዉ ሐገራት ከስሕተት እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል።
«የሚመለከታቸዉ ሐገራት የሐሰት አስተያየት ከመስጠት እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።የእስያ-ፓስፊክ አካባቢን ለጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር መጠቀሚያ ማድረጋችሁን አቁሙ።የጉድኝነት ፖለቲካና ወታደራዊ ፍጥጫን አቁሙ።በአካባቢዉ የሚኖረዉን ሕዝብ ፀጥታና ደሕንነት ማወካችሁን አቁሙ።»
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ