"በላይተር ፀጉራቸው እየተቃጠለና ሰውነታቸው እየተለበለበ ያሉ አሉ"፤ የሚያንማር ተመላሽ
ዓርብ፣ መጋቢት 5 2017መጋቢት 3 ቀን 2017 ዓ ም ከሚያንማር ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ 43 ኢትዮጵያዊያን አንዱ ስሙ እንዲጠቀስ የማይፈልገው የሻሸመኔ ወጣት ነው። ታሪኩ እንዲህ ነው፤ በንግድ አስተዳደር ምሩቅ የሆነውን ወጣት አንድ ኢትዮጵያዊው ደላላ አውስትራሊያ ሄዶ የመስራት እድል እንዳለው ያግባባዋል። እሱም በዚህ ተደስቶ እንደተነገረው በመጀመሪያ ታይላንድ ሀገር ለአንድ ወር ያህል ለመቆየት እና 200 ሺ የኢትዮጵያ ብር ለመክፈል ይስማማል። ጉዞም ይጀምራል። ብዙም ሳይቆይ ግን ደላላው የገዛ ወንድሙን ከአጭበርባሪዎች እጅ ለማስለቀቂያ እንደተጠቀመበት ይገነዘባል። “ሶስት ሰው ካመጣህ ወይም 600 ሺ ብር ከከፈልክ ትለቀቃለህ ይሉታል። ይህንን እዚህ ላለው ወንድሙ ነግሮት ኖሮ፤ እዛ የታገተው ልጅ እኛን አስይዞ እሱ ካለበት ቦታ ወጣ።”
ገንዘብ የመዝረፍ የግዳጅ ስራ
ወደ ታይላንድም ሳይሆን ወደ ሚያንማር የተወሰደው ይኼው ወጣት ወዲያው በበይነ መረብ ሰዎችን እንዲያታልል ይደረጋል። የተለያዩ ቆኖጃጂት ሴቶችን ምስል በመውሰድ እና የግል ገፅ በመክፈት የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን እንደ ፍቅረኛ በማቅረብ ማታለል እና ለድርጅቱ ገቢ ማስገኘት ግዴታው ነበር። “በአጠቃላይ ስራው ገንዘብ መዝረፍ ነው። ከአውሮጳውያ፣ አሜሪካውያን፣እንዲሁም ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ ፣ ኢራቅ ፣ ሳዑዲ አረቢያ ፣ ቱርክ… ከተለያዩ ሀገራት”» ይላል ወጣቱ ሁሉም ያነጋገርናቸው ወጣቶች በተመሳሳይ የማጭበርበር እና የግዳጅ ስራ ተሰማርተው እንደነበር ገልፀውልናል። ስራው ወንድም ፣ ሴትም አይልም። “ 18 ሰዓት ነበር የምንሰራው። ለእኛ በሴት አቅም ከባድ ነበር። ስራው አንድ ነበር። እሱም ስራ ካልተገኘ ግርፊያ አለ። ከፍለን መውጣት ብንፈልግ ሌላ ገንዘብ እንጠየቅ ነበር። ያለ ደሞዝ አሳለፍን። እግዚያብሔር ይመስገን አሁን ከዛ ወጥተናል። “
“ለጊዜው ስሜ ይቆይ” ያለችን ይቺው ወጣት ኢትዮጵያዊት ገና ወደ ሀገሯ አልተመለሰችም። በአሁኑ ሰዓት እዛው ሚያንማር የሚገኝ ወታደራዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ትገኛለች። ልክ እንደ እሷ በተመሳሳይ የሚያንማር አማፂ ቡድን መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኘው ፤ ማይክ በሉኝ ያለን ኢትዮጵያዊ ይገኛል። እሱ እንደሚለው በመጠለያው ውስጥ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ 252 ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።
የሚያንማር አማፂ ቡድን እጅ የሚገኙ 252 ኢትዮጵያውያን
„እዚህ ያለው ማህበረሰብ ላይ ኮሚቴ ስለሆንኩ ትክክለኛውን ቁጥር አውቀዋለው። 252 ነን። “ ያለን ማይክ አንድ አመት ከሶስት ወር በስራ ላይ አሳልፏል። „አንሰራም ብለን ከወጣን ደግሞ አንድ ወር ሊሆነን ነው። በፊት አልሰራም ብሎ መውጣት አይቻልም ነበር። ግን አንፈልግም ብለን በምንወጣበት ሰዓት በታይላንድ የሚታገዘው የሚያንማር አማፂ ቡድን አገኘን እና ይዞን ወጣ ይኼው ከለላ ሰጥቶን አለን። በ24 ሰዓታት ውስጥ ሁለት ጊዜ ምግብ ይሰጡናል። “
በዚህ ሳምንት ወደ ሀገሩ የተመለሰው የሻሸመኔ ወጣት እንደገለፀልንም ከታይላንድ ጋር በቅርበት የሚሰራ የሚያንማር አማፂ ቡድን ጠፍተው ሲያመልጡ ታድጓቸዋል። ለታይላንድ ካስረከባቸው አንድ ወር በኋላም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ችለዋል። “ለስምንት ወር ያክል እዛ ድርጅት ስንሰራ አንድ ብር ተከፍሎን አናውቅም። ለ20 ሰዓት ነበር እንሰራ የነበረው። ለመፀዳዳት እና ለምግብ ብቻ ነበር የሚፈቀድልን። ይህን ሁሉ ታግሰን ታግሰን አንድ ሌሊት ከሞትንም እንሙት ብለን ሁላችንም ተነጋገርን እና (25ቱ ኢትዮጵያውያውያን ናቸው። የተወሰኑ ከፊሊፒንስ እና ባንግላድሾችም ነበሩ) ተሰብስበን ሮጥን። አይን ጨፍኖ እንደመሮጥ ነበር። በጭለማ ነበር ተራራውን የሮጥነው። ግማሽ መንገድ እንደሮጥን የጊቢው ጠባቂዎች ይዘው እየደበደቡን በካቴና አስረው ወደ ክፍል ሊያስገቡን ሲሉ አማፂዎቹ ደርሰው ከዛ ግቢ ሊያስወጡን ችለዋል”
በእንደዚህ አይነት መንገድ ከተረፉ እና ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱት ኢትዮጵያውያን መካከል ሌላው ፋኑኤል ይባላል። ለ 6 ወራት ያህል ሚያንማር ከቆየ በኋላ ወደ ሀገሩ መመለስ ችሏል።
በሚያምነው ጓደኛው የተታለለው ወጣት
„ ወደ ታይላንድ ስሄድ ሱፐር ማርኬት እንደምሰራ፤ የገንዘብ ደረሰኝ በኮምፒውተር እንደምሰራ በቪዲዮ ተቀርፆ ተልከውልኝ ነው ወደ ታይላንድ የሄድኩት። “ የሚለው ፋኑኤል ያታለለው ከምንም በላይ የሚያምነው ጓደኛው እንደነበር ነግሮናል። „ታይላንድ እንደገባሁ በትንሽዬ መርከው ወደ ሚያንማር አስገብተው በቁጥጥራቸው ስር አዋሉኝ። ስልኬን ቀሙኝ። ያለሁበትን ቦታ አላውቅም ነበር። ፓስፖርቴን ተቀበሉኝ። እኔን አሲያዘና እሱ ወጣ ማለት ነው። “
ፋኑኤል እንደነገረን ሚያንማር ውስጥ ይሰራበት በነበረበት ቦታ ፈተና ያልነበረው ምግብ ብቻ ነው። በብዛት ኢትዮጵያውያን ሩዝ እና የዶሮ ስጋ አልፎ አልፎም አሳ ይመገቡ ነበር። ከአሰሪዎቻቸው ጋር የሚግባቡት ደግሞ „አንድ ቻይንኛ የሚችል ጋናዊ እያስተረጎመልን ነበር። ” ይላል ፋኑኤል።
ስራዋ የባቡር ቲኬት መቁረጥ እና ደንበኞችን ማስተናገድ እንደሆነ ተነግሯት ለጉዞ የተነሳሳችው፤ ወጣት ሴት የምታውቀው ስራው ህጋዊ እንደሆነ እና 1000 ዶላር እንደሚከፈላት ነበር። ነገር ግን ያለ ክፍያ መስራት ብቻ ሳይሆን፤ የሚጠበቅባቸውን ስራ ካላሟሉ «ፀሀይ ላይ ለረዥም ሰዓታት እንዲቆሙ እና በኤሌክትሪክ ገመድ ይገረፉ» እንደነበርም ገልፃልናለች። “ብዙ ብር አውጥቼ ነው ወደዚህ የመጣሁት። ለደላላ፤ ለአይሮፕላን ቲኬት ከፍያለሁ። 10 ወር ሙሉ ያለደሞዝ ነው የቆየሁት። እና መንግሥት ከዚህ ሀገር ቢያስወጣን ብዬ ነው መንግሥትን የምለምነው።”
አብሯት በመጠለያ የሚገኘው ማይክ የሚያስተላልፈውም ጥሪ ተመሳሳይ ነው። “የእኛን ጉዳይ የሚመለከተው ቶኪዮ ያለው (የኢትዮጵያ)ኤምባሲ ነው። ይህንን እንዲያደርግልን መጠየቅ ከጀመርን ቆይቷል። በቻልነው መጠን እየለፋን ነው። ግን አንድ ወር ሊሆነን ነው። መንግሥት ምንም አልሰራም አይደለም። ቀድመው የወጡ ልጆችም አሉ ። ግን እኛን ችላ ብሎናል። ታይላንድ እስከምንገባ ነው የሚጠብቀው። እኛ ታይላንድ ብንገባ እኮ በራሳችን ጉዳዮን መጨረስ እንችላለን። እዚህ ጋር ግን ምንም በራሳችን ማድረግ አንችልም። “
እንደ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፃ ሰኞ ዕለት 32 ፣ ዕሮብ ዕለት ደግሞ 43 ኢትዮጵያውን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል። ሚያንማር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን የማስመለሱ ሥራ ፈታኝ እንደሆነም መንግሥት አስታውቋል።
አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያን አደጋ ላይ ናቸው
“ከ 2000 በላይ ኢትዮጵያዊያን አሉ። ቢያንስ 10 በመቶው ነው ስራውን አውቆ የሚመጣው። ….እና ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ። እኔ ለሌሎች የምመክረው፤ አገራችን ላይ ያለው ነገር በእርግጥ ውጪ ሀገር ለስራ የሚያስመኝ ነው። ግን እንደእኔ ተሸውደው እንደዚህ አይነት ስቃይ ውስጥ እንዳይገቡ ነው። ብዙ በኤሌክትሪክ ገመድ ተገርፌያለሁ። ጭለማ ክፍል ተቀምጬያለሁ። እዛ የሚቀበላቸው የቅርብ ሰው ከሌለ በቀር ስደትን እንዳይሞክሩ። እኛ የነበርንበት የቀሩ አሁንም ድርጅቱ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ በላይተር ፀጉራቸው እየተቃጠለና ሰውነታቸው እየተለበለበ ነው። መንግሥት ለእነሱ እንዲደርስላቸው እና እናንተም በሚዲያቹህ እንድትጮሁላቸው ነው ማስተላለፍ የምፈልገው።“ ይላል። በሚያንማር በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን በቅርብ በሚያውቋቸው ደላሎች ሳይቀር ተታለው ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፣ እየከፈሉም ይገኛሉ።
ልደት አበበ
እሸቴ በቀለ