የመጋቢት 8 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ መጋቢት 8 2017በደቡብ ኮሪያ የሴዑል ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም አሸናፊ ሁነዋል ። በባርሴሎና ማራቶንም ድል ተገኝቷል ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ ልምምዱን ዛሬ አድርጓል ። ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። ኢትዮጵያ በሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ሳታልፍ ቀርታለች ።
በእንግሊዝ የካራባዎ ዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ ኒውካስትል ትናንት በአሌክሳንደር ኢሳቅ ወሳኝ ግብ ሊቨርፑልን አሸንፏል ። ፌዴሪኮ ኪዬሳ በጨዋታው ፍጻሜ ለሊቨርፑል የመጽናኛውን ግብ አስቆጥሯል ። ከሻምፒዮንስ ሊግ ለተሰናበተው ሊቨርፑል አሁን የቀረው አንድ እድል የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫ ነው ። ተከታዩ አርሰናል በለንደን ደርቢ ቸልሲን አሸንፏል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ የመሪው ባዬርን ሙይንሽን ነጥብ መጣል ለተከታዬ ባዬር ሌቨርኩሰን መልካም አጋጣሚ ሁኗል ። ዶርትሙንድ ዳግም ሽንፈት ገጥሞታል ።
አትሌቲክስ
ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ትናንት (መጋቢት 07 ቀን፣2017 ዓ.ም) በተካሄደው የሴኡል ማራቶን በሁለቱም ፆታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሁነዋል ። በተለይ በሴቶች ፉክክር፦ ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት ብቃታቸውን ዐሳይተዋል ። በውድድሩ፦ አትሌት በቀለች ጉደታ (2:21.36) አንደኛ፣አትሌት ፍቅርተ ወረታ ሁለተኛ (2:22.54) እንዲሁም አትሌት መስታወት ፍቅር ሦስተኛ (2:23.10) ደረጃውን በመጠቅለል በተከታታይ ገብተዋል ።
በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት ፉክክር፦ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሀፍቱ ተክሉ (2:05:42) ከኬንያውያን አንገት ለአንገት ተናንቆ በአንደኛነት አሸንፏል ። ኬንያውያኑ ፌሊክስ ኪርዋ እና በርናርድ ኪፕሮፕ ኮይች ከሀፍቱ በሁለት እና በስምንት ሰከንድ ልዩነት የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። በዘንድሮው የሴኡል ማራቶን ከሰባት አገራት የተውጣጡ 170 አትሌቶች በአጠቃላይ ከ66 አገራት 40,000 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል ። የመጋቢት 01 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ትናንት ስፔን ውስጥ በተከናወነው የባርሴሎና ማራቶንም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል ። በወንዶች ፉክክር አትሌት ተስፋዬ ድሪባ ከበርካታ ኬንያውያን ተፎካካሪዎች መሀከል (02:04:13) አንደኛ በመውጣት ሲያሸንፍ፤ በሴቶች ፉክክር አትሌት የብርጓል መለሠ(02:20:47) ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ኬኒያዊቱ ሻሮን ቼሊሞ (02:19:33)በመሮጥ በአንደኛነት አሸንፋለች ። በወንዶች ፉክክር፦ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶችት መኳንንት ዐየነው 6ኛ እንዲሁም ካሳሁን ኃይሉ 10ኛ ከማጠናቀቃቸው ውጪ ኬንያውያን ከ2ኛ እስከ 9ኛ በመግባት አሸናፊ ባይሆኑም ብርታታቸውን ዐሳይተዋል ።
እግር ኳስ
የኒውካስትል ቡድን ከ70 ዓመታት ወዲህ የአገር ውስጥ ዋንጫን በእጁ አስገብቷል ። ቡድኑ ላለፉት 55 ዓመታት ሲመኘው የነበረውን ታላቅ ውጤት አስመዝግቧል ። ትናንት በነበረው የካራባዎ የፍጻሜ ግጥሚያ ሊቨርፑልን 88,513 ሰዎች በታደሙመበት የዌምብሌ ስታዲየም 2 ለ1 በማሸነፍ ዋንጫውን ወስዷል ።
ለኒውካስትል ቀዳሚዋን ግብ የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ክፍለ ጊዜ ሲጠናቀቅ በ45ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ዳን በርን ነው ። አሌክሳንደር ይሣቅ ደግሞ ከረፍት መልስ በ52ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛዋን አስቆጥሯል ። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው አራተኛ ደቂቃ ላይ ፌዴሪኮ ኪዬሳ ለሊቨርፑል የማስተዛዘኛዋን ግብ በማግባት ቡድኑን በዜሮ ከመሸነፍ ቢታደግም፤ ኒውካስትሎች የትናንቱን ጨዋታ ማሸነፋቸው በእርግጥም የሚገባቸው ነበር ። የየካቲት 24 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት የትናንቱን የዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ በተመለከተ ተጠይቀው ሲመልሱ፦ «አናዳጅ ውጤት፤ የሚያበሳጭ እንቅስቃሴ» ሲሉ በቡድናቸው መናደዳቸውን አልሸሸጉም ። ባለፉት ውድድሮች ከኤፍ ኤ ካፕ እና ከሻምፒዮንስ ሊግ ፉክክር ለተሰናበተው ሊቨርፑል የትናንቱ ውጤት በእርግጥም ለአሰልጣኙ እጅግ የሚያበሳጭ ነበር ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊጉ 29 ጨዋታዎች ሊቨርፑል ዋንጫ የማግኘት እድሉን አስፍቶ 70 ነጥብ ሰብስቧል ። አርሰናል ትናንት ቸልሲን በለንደን ደርቢ ገጥሞ በሚኬል ሜኒኖ 20ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ አሸንፏል ። ነጥቡንም ወደ 58 ከፍ በማድረግ ከሊቨርፑል በ12 ነጥብ ርቀት ተጠግቷል ። ሊቨርፑል ከቀሪ ጨዋታዎቹ በአራቱ ካልተሸነፈ በቀር አርሰናልም ሆነ በ54 ነጥብ በሦስተኛ ደረጃ የሚከተለው ኖቲንግሀም ፎረስት ዋንጫውን የማንሳት እድል የላቸውም ። ከተለያዩ የዋንጫ ፉክክሮች የተሰናበተው ሊቨርፑል በእጁ ለማስገባት ሰፊ ዕድል ያለውን የፕሬሚ,ር ሊግ ዋንጫ እንዲህ በቀላሉ አሳልፎ ይሰጣል ማለት ይከብዳል፥ የኳስ ነገር ግን ዐይታወቅም ።
ትናንት በነበሩ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች የተሸነፈው ቸልሲ በ49 ነጥብ የአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ኢፕስዊች ታወንን ቅዳሜ ዕለት በሜዳው 4 ለ2 ድል ኩም ያደረገው ኖቲንግሀም ፎረስት በ54 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ነው ። ከትናንት በስትያ ብራይተንን በሜዳው ኢቲሀድ ስታዲየም ጋብዞ አንድ እኩል የተለያየው ማንቸስተር ሲቲ በ48 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ትናንት ሊቨርፑልን በካራባዎ ዋንጫ ያሸነፈው ኒውካስትል ከብራይተን ጋር በእኩል 47 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ኢፕስዊች ታወን፣ ላይስተር ሲቲ እና ሳውዝሐምፕተን በተሰናባች ቀጣና ውስጥ ተደርድረዋል ። የየካቲት 17 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ቡንደስሊጋ
ሽቱትጋርት ላይ በባከነ ሰከንድ በተቆጠረ ግብ ባዬር ሌቨርኩሰን ከመሪው ባዬርን ሙይንሽን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ችሏል ። ቦሁም ውስጥ የፍራንክፉርት ነውጠኛ ደጋፊዎች ጨዋታው በሰአቱ እንዳይጀምር መሰናክል ሁነዋል ። በቡንደስሊጋ ታሪክ ላለፉት 15 ዓመታት በሜዳቸው ባሼር ሌቨርኩሰንን ማሸነፍ የተሳናቸው ሽቱትጋርቶች ትናንት የቆየ ታሪካቸውን የሚያድሱ መስለው ነበር ። ቀዳሚዎቹን ሁለት ግቦች በማስቆጠር ሽቱትጋርት ከረፍት መልስም 2 ለ0 እየመራ ነበር ። በ62ኛው ደቂቃም ሌቨርኩሰን 3 ለ1 እየመራ ነበር ። ብዙም አልቆየ ጨዋታው ወደ 3 ለ2 ሲቀየር ። የማታ ማታ የበረቱት ባዬር ሌቨርኩሰኖች በስተመጨረሻ መደበኛ 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው ፓትሪክ ሺክ ባስቆጠራት ግብ ሽቱትጋርትን በሜዳው 4 ለ3 አሸንፈዋል ።
በዚህም መሠረት፦ ባዬር ሌቨርኩሰን ነጥቡን ወደ 56 ከፍ አድርጎ ከመሪው ባዬርን ሙይንሽን በስድስት ነጥብ ብቻ መራቅ ችሏል ። ከፍራይቡርግ ጋር ሁለት እኩል የተለያየው ማይንትስ በ45 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በቦሁም ሜዳ የ3 ለ1 ድል የቀናው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በተመሳሳይ 45 ነጥብ ሁኖም በግብ ክፍያ 4ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። 42 ነጥብ ሰብስቦ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ ዶርትሙንድን 2 ለ0 ኩም አድርጓል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ35 ነጥቡ ደረጃው 11ኛ ነው ። ቦሁም በ20 ነጥብ 16ኛ ወራጅ ቀጣና ግርጌ ላይ ይገኛል ። ሐይደንሀይም ከበታቹ 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሆልሽታይን ኪዬልን ትናንት 3 ለ1 አሸንፎ በደረጃው ቦታ ተቀያይሯል ። ሆኖም ሁለቱም 17 እና 19 ነጥብ ብቻ ይዘው ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ ። የየካቲት 10 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የኢትዮጵያ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ቡድን በዓለም ዋንጫ ወደ መጨረሻው ማጣርያ ሳያልፍ ቀርቷል ። አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በነበረው ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ከካሜሩን ጋር የገጠመው የኢትዮጵያ ቡድን የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዶ ሳያልፍ ቀርቷል ። በደርሶ መልስ ድምር ውጤት የካሜሩን ቡድን 6 ለ2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል ።
የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን
የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን ዋሊያዎቹ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከግብጽ እና ከጅቡቲ ጋር ለሚኖራቸው ግጥሚያ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምድ አድርገዋል ። የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ በቦታው ተገኝቶ ነበር ። የዛሬው ልምምድ በሁለት መልኩ የተከፈለ እንደነበር ገልጧል ።
ዖምና አንደኛው ልምምድ በመከላከል እና መልሶ ማጥቃት ላይ ያተኮረ ልምምድ መሆኑን ጠቅሷል ። በሁለተኛው የልምምድ ምእራፍም ቡድኑ በሁለት ተከፍሎ በመከላከል ላይ ያተኮረ ጨዋታ ሲያሠሩ መመልከቱን ጠቅሷል ። ዖምና በቦታው ተገንቶ እንደተመለከተው ከሆነ ስታዲየሙ «በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሠርቶ» ይጠናቀቃል የሚለው በተግባር የታየ አለመሆኑ ታውቋል ። እንደውም የሜዳው ሣር ውኃ ከማጣት የተነሳ በሚመስል ወይቦ ወደ ቢጫነት ተቀይሯል፥ የመሮጫ መሙም ጭራሽ የነበረውም ተነስቷል ።
የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን
አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን የባዬርን ሙይንሽን አማካይ ተጫዋች ሌዎን ጎሬትርስካን የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን እንዲቀላቀል ባለፈው ሣምንት ጥሪ አስተላልፈዋል ። ብሔራዊ ቡድኑ በአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ ለሩብ ፍጻሜ ከጣሊያን ጋር የደርሶ መልስ ግጥሚያ አለው ። የየካቲት 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የ30 ዓመቱ ሌዎን ጎሬትስካ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2023 ጀምሮ ለብሔራዊ ቡድኑ አልተሰለፈም ። ጀርመን ያሰናዳችው የዩሮ 2024 የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ ላይ አልነበረም ። ለሌዎን ጎሬትስካ አሰልጣኙ ጥሪ ያስተላለፉት ሐሙስ ዕለት ነው ። ከጣሊያን ጋር የደርሶ መልስ ግጥሚያው የፊታችን ሐሙስ እና እሁድ ይካሄዳል ።
አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን ለሌዎን ጥሪውን ያስተላለፉት በርካታ ተጨዋቾቻቸው ገሚሱ በመጎዳቱ እና በመታመሙ ነው ተብሏል ። ካይ ሐቫርትስ፣ ፍሎሪያን ቪርትስ፣ ማትክ-አንድሬ ተር ስቴገን፣ ኒክላስ ፉይክሩግ፣ ቤንጃሚን ሔንሪሽስ እና አሌክሳንዳር ፓቭሎቪች ጎዳት ከደረሰባቸው አለያም ከታመሙት መካከል ይገኙበታል ።
የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የጣሊያን አቻውን በሩብ ፍጻሜው የሚያሸንፍ ከሆነ ሙይንሽን እና ሽቱትጋርት ውስጥ በሚካካሄዱየግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ተሳታፊ ይሆናል ። ሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ለረቡዕ፤ ግንቦት 27 እና በነጋታው ቀጠሮ ተይዞላቸዋል ። የፍጻሜ ግጥሚያው እሁድ ሰኔ 1 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ቱሪን ጣሊያን ውስጥ ይካሄዳል ። የጥር 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ፎርሙላ አንድ
በአውስትራሊያ ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም፦ ሌዊስ ሐሚልተን በፌራሪ ተሽከርካሪው በ7ኛ ደረጃ አጠናቀቀ ። የማክላረኑ አሽከርካሪ ላንዶ ኖሪስ የትናንቱን ሽቅድምድም አሸንፎ 25 ነጥብ አግኝቷል ። በአንጻሩ ሌዊስ ሐሚልተን ያገኘው አንድ ነጥብ ብቻ ነው ። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን ሁለተኛ በማጠናቀቅ 18 ነጥብ አግኝቷል ። የመርሴዲሱ ጆርጅ ሩሴል ሦስተኛ በመውጣት 15 ነጥብ አግኝቷል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ