የመጋቢት 29 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ መጋቢት 29 2017ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ድረስ ለሚወጡ አትሌቶች በአጠቃላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሽልማት በተዘጋጀበት አዲሱ የግራንድ ስላም የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያውያን ድል የቀናቸው ነው ። የፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል ሽንፈት አስተናግዷል ። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ማክስ ፈርሽታፐን ተጨማሪ ድል ተቀዳጅቷል ። ከገና ጨዋታ ጋር በሚመሳሰለው የሆኪ ስፖርት ሊግ አሌክሳንደር ኦቬችኪን በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረ ወሰን ሰብሯል ። በርካታ ደጋፊዎቹ አድናቆታቸውን ቸረውታል፤ ምእራባውያን የመገናኛ አውታሮች አሌክሳንደር የፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ደጋፊ መሆኑን አጉልተዋል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽን እና ተከታዩ ባዬር ሌቨርኩሰን እንዲሁም አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሽንፈት ገጥሞታል ።
አትሌቲክስ
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች በተከናወኑ የማራቶን ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል ። ጀርመን ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው የቤርሊን ግማሽ ማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ አሸናፉ ሁነዋል ።
በሴቶች የግማሽ ማራቶን ፉክክር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃውን ኢትዮጵያውያቱ ተቆጣጥረዋል ። አትሌት ፎትየን ተስፋይ 1:03.35 ሮጣ በመግባት የቦታውን ክብረ ወሰን ጭምር አሻሽላ በአንደኛነት ለድል በቅታለች ። አትሌት ፍታው ዘራይ 1:07.01 ሁለተኛ እንዲሁም አትሌት ዓለምአዲስ እያዩ 1:07.12 ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ለድል በቅተዋል ።
በወንዶች ተመሳሳይ የግማሽ ማራቶን ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት ገመቹ ዲዳ ርቀቱን 58:43 ሮጦ በመግባት በአንደኝነት አሸንፏል ። ኬኒያዊው አትሌት ሪቻርድ ኤቲር ከገመቹ በ47 ሰከንዶች ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። የሦስተኛ ደረጃው ለጀርመን የሚሮጠው አትሌት አማናል ጴጥሮስ ሁኗል ።
ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው የቪዬና ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሀፍታሙ አባዲ በ2:08.28 በመግባት በአንደኝነት አሸንፏል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሞጎስ ጡዑማይ በ2:10.33 ሮጦ በማጠናቀቅ ሦስተኛ ደረጃ ማግኘቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐሳውቋል ።
የግራንድ ስላም ፉክክር
በአጠቃላይ የ12,6 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በተዘጋጀበት እና በአራት የተለያዩ ከተሞች በተለያዩ ጊዜያት በሚደረገው የግራንድ ስላም ውድድርም ኢትዮጵያውያን ከወዲሁ ድል እየቀናቸው ነው ። ጃማይካ ኪንግስተን ከተማ ውስጥ ከዐርብ መጋቢት 27 ቀን፣ 2017 ዓ.ም እስከ እሁድ ለሦስት ቀናት በተካሄደው የግራንድ ስላም ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአሸናፊዎቹ ተርታ ተመድበዋል ። በአራቱ ከተሞች ፉክክር ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበ አትሌት በየውድድሩ የ100,000 የአሜሪካ ዶላር ይሸለማል፤ 2ኛ ለወጣ አትሌት የ50,000 እንዲሁም ለሦስተኛ ደረጃ የ30,000 ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቷል ። እስከ ስምንተኛ ደረጃ ድረስ የወጡ አትሌቶች በወንድም በሴትም ፉክክር ተሸላሚ ይሆናሉ ።
የግራንድ ስላም ፉክክር በውድድር ኮሚቴው የቀደመ ብቃታቸው በተለያየ መንገድ ተገምግሞ የተመረጡ 48 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ነው ። እነዚህ አትሌቶችም በግራንድ ስላማ አራት የተለያዩ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ የወሰኑ ናቸው ። ያም ብቻ አይደለም ሌሎች 48 ተፎካካሪዎችም የቅርብ ጊዜ ብቃታቸው ታይቶ በውድድር ኮሚቴው ይመረጣሉ ። እነዚህ 96 አትሌቶች በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ ፉክክሮች የተሻለ ነጥብ ለማምጣት በአራት የተለያዩ ከተሞች ይወዳደራሉ ። የግራንድ ስላም ቀጣይ ውድድሮች ከአንድ ወር በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ሚያሚ፤ ከዚያም ግንቦት መጨረሻ እና ሰኔ አጋማሽ ላይ ፊላዴልፊያ እና ሎስ አንጀለስ ውስጥ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዟል ። ለመሆኑ የግራንድ ውድድር ነጥብ አሰጣጥ እና ይዘቱ ምን ይመስላል? ከኢትዮጵያስ እነማን ተሳታፊ ናቸው፣ ምን አይነስት ውጤታት አስመዘገቡ? የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ኢትዮ ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ።
የግራንድ ስላም ፉክክር በጃማይካ ኪንግስተን
ጃማይካ ኪንግስተን ከተማ ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ በተከናወነው የወንዶች 3000ሜትር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሀጎስ ገብረ ሕይወት 7: 51.55 በመሮጥ አሸንፏል ። አራተኛ ደረጃ ይዞ ባጠናቀቀበት በመጀመርያው የ5000 ሜትር ረጅም ርቀት የሰበሰበውን ነጥብ 17 በማድረስ በኪንግስተኑ ፉክክር በአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሁለተኛ የወጣው ጥላሁን ኃይሌ በድምር ውጤት አራተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል። በሌላ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ አሸናፉ ሁናለች ።
በጃማይካ ኪንግስተን በተደረገው የ5000 ሜትር ረጅም ርቀት ግራንድ ስላም ትራክ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በአንደኝነት ለድል የበቃች 14:54.88 ሮጣ በመግባት ነው ። በ3000ሜትር ረጅም ርቀትም በተመሳሳይ በአንደኝነት ያጠናቀቀችው ይህችው ብርቅዬ አትሌት እስካሁን ያገኝችውን ነጥብ 24 በማድረስ የርቀቱ ባለድል ሁናለች ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጽጌ ገብረሰላማ 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ድርቤ ወልተጂም በዚሁ ውድድር አሸንፋለች።
በሴቶች 1500 ሜትር አጭር ርቀት በተደረገው ውድድር አትሌት ድርቤ 4: 04.51 በመግባት ነው በበላይነት ያጠናቀቀችው ። አትሌት ድርቤ በ800 ሜትር 2ኛ የወጣችበት ውጤትም ተደምሮላት በአጠቃላይ ነጥቧ 20 አድርሳለች።
እግር ኳስ
የፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል ከረዥም ጊዜ ተከታታይ ድል በኋላ ትናንት ሽንፈት አስተናግዷል ። የፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዡን በ73 ነጥብ የሚመራው ሊቨርፑል የ3 ለ2 ሽንፈት የደረሰበት ስምንተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ፉልሀም ነው ። እንዲያም ሆኖ ግን ተከታዩ አርሰናል በኤቨርተን ሜዳ አንድ እክል በመውጣት ነጥብ በመጣሉ አሁንም ከሊቨርፑል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት እንደተራራቀ ነው ። አርሰናል በሊቨርፑል በ11 ነጥብ ተበልጦ 62 ነጥብ ሰብስቧል ። በ57 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት ቅዳሜ ዕለት በአስቶን ቪላ የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ።
ከብሬንትፎርድ ጋር ትናንት ያለምንም ግብ የተለያየው ቸልሲ በ53 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ከበታቹ ማንቸስተር ሲቲ በ52 ነጥብ ይገኛል፤ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ትናንት ያለምንም ግብ ተለያይቷል ።
ከ31 ግጥሚያዎች 10 ነጥብ ብቻ ማግኘት የቻለው ሳውዝሐምፕተን ከወዲሁ መውረዱን አረጋግጧል ። ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ከበላዩ ላይስተር ሲቲ በ17 እንዲሁም ኢፕስዊች ታወን በ20 ነጥብ ይገኛሉ ። ከወራጅ ቃጣናው ጠርዝ አንድ ከፍ ብሎ በ17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዎልቭስ 32 ነጥብ አለው ። ዛሬ ማታ ክሪስታል ፓላስ ከኒውካስል ጋር ተስተካካይ ግጥሚያቸውን ያደርጋሉ ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባዬር ሌቨርኩሰን ቅዳሜ ዕለት ሐይደንሀይምን 1 ለ0 ድል አድርጓል ። በ68 ነጥብ ደረጃውን የሚመራው ባዬር ሙይንሽን አውግስቡርግን 3 ለ1 ማሸነፍ ችሏል ። በዚህም መሰረት ከባዬር ሌቨርኩሰን ጋር የስድስት ነጥብ አላቸው ። በ48 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በቬርደር ብሬመን የ2 ለ0 ሽንፈት ደርሶበታል ። ትናንት ሳንክት ፓውሊ እና ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ቅዳሜ ዕለት ሽቱትጋርት ቦሁምን 4 ለ0 ድል አድርጓል ። ላይፕትሲሽ ሆፈንሀይምን 3ለ1 ቢያሸንፍም በ45 ነጥቡ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ከበላዩ በ46 ነጥብ የሰፈረው ማይንትስ ከሆልሽታይን ኪየል ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል ።
የበረዶ ላይ ሆኪ ስፖርት
ከገና ጨዋታ ጋር በሚመሳሰለው የአሜሪካው የበረዶ ግግር ላይ ብሔራዊ የሆኪ ሊግ ፉክክር ሩስያዊው አሌክሳንደር ኦቬችኪን በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረ ወሰን ሰብሯል ። በርካታ ደጋፊዎቹ አድናቆታቸውን ችረውታል፤ ምእራባውያን የመገናኛ አውታሮች አሌክሳንደር የፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ደጋፊ መሆኑን አጉልተዋል ዘግበዋል ። አሌክሳንደር በዋይኔ ግሬትዝኪ ተይዞ የቆየውን በአንድ የውድድር ዘመን 894 ግቦችን የማስቆጠር ክብረወሰን ነው የሰበረው ። ከዩክሬን ወረራ በኋላም አሁንም የፑቲን ደጋፊ እንደሆን የተጠየቀው አሌክሳንደር፦ «እንግዲህ ፕሬዚደንቴ ናቸው» ሲል መልስ ሰጥቷል ።
የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን ተጨማሪ ድል ተቀዳጅቷል ። ሱዙኪ መወዳደሪያ ስፍራ ውስጥ ትናንት በተደረገው የጃፓን ግራንድ ፕሪ ፉክክር አንደኛ የወጣው ማክስ ፈርሽታፐን እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች በሰበሰበው ነጥብም ይመራል ። ላንዶ ኖሪስ እና ዖስካር ፒያስትሪ በማክላረን ተሽከርካሪያቸው የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። ዘንድሮ ለፌራሪ የፈረመውና ለበርካታ ዓመታት በመርሴዲስ ተሽከርካሪ ለድል የበቃው ሌዊስ ሐሚልተን የስድስተኛ ደረጃ አግኝቶ አጠናቋል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ