የመጋቢት 15 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ መጋቢት 15 2017በቻይና ናንጂንግ ከተማ የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ ዩናይትድ ስቴትስ እና ኖርዌይን ተከትላ በሦስተኛ ደረጃ አጠናቃለች ። Ethiopiaበግብጽ የ2 ለ0 ሽንፈት ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከጅቡቲ ጋር ዛሬ ማታ ሞሮኮ ውስጥ ይጋጠማል ። በአውሮጳ የኔሽንስ ሊግ እግር ኳስ በግማሽ ፍጻሜው ጀርመን ከፖርቹጋል ሙይንሽን አሬና ውስጥ፤ ስፔን ከፈረንሳይ ጋር ደግሞ ሽቱትጋርት አሬና ውስጥ ይጋጠማሉ ።
አትሌቲክስ
ቻይና ናንጂንግ ከተማ ውስጥ ትናንት (መጋቢት 14 ቀን፣2017 ዓ.ም) በተጠናቀቀው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ ብሪታንያ እና ጣሊያንን አስከትላ ከዓለም በ3ኛ ደረጃ አጠናቃለች ። ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሠንጠረዥ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ኖርዌይ ቀጥላ በሁለት የወርቅ እና ሦስት የብር ሜዳሊያዎች የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ለኢትዮጵያ ከተገኘው አምስት ሜዳሊያዎች ውስጥ በአትሌት በሪሁ ኃይሉ ከተገኘው የብር ሜዳሊያ በስተቀር የተቀሩት በአጠቃላይ በሴት አትሌቶቻችን የተገኙ ናቸው ። ሁለቱን የወርቅ ሜዳሊያዎች ያስገኙት ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ጉዳፍ ጸጋዬ ናቸው ።
በሴቶች የ3000 ሜትር ርቀት ፍጻሜ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ድል ተጎናጽፋ የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ የፈጀባት ጊዜ (8:37.21)ነው ። ብርቱ ፉክክር በታየበት የ3000 የፍጻሜ ሩጫ፦ ሜትር አሜሪካዊቷ ሼልቢ ሁሊሃን ፍሬወይኒ ኃይሉን በአንድ ነጥብ አምስት ሰከንድ ተከትላ ሁለተኛ ወጥታለች ። የአውስትራሊያዋ ሯጭ ጄሲካ ሁል ከሼልቢ በሁለት ማይክሮ ሰከንድ ተበልጣ ነው ሦስተኛ የወጣችው ። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብርቄ ኃየሎም አሜሪካዊቷ ዊትኒ ሞርጋንን ተከትላ የአምስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።
በ1500 ሜትር ርቀትም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በ(3:54.86) ሮጣ ስታጠናቅቅ ክብረወሰን ጭምር በመስበር ነበር ። የአገሯ ልጅ አትሌት ድርቤ ወልተጂ ጉዳፍን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች ። አትሌት ድርቤ ወልተጂ ከጉዳፍ በአራት ነጥብ ዐርባ አራት ሰከንድ ተከትላ በመግባት (3:59.30) የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች ። ብሪታንያዊቷ አትሌት ጆርጂያ ሁንተር ቤል ሦስተኛ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሁናለች ።
የኢትዮጵያ አመርቂ ድል
በወንዶች የ3000 ሜትር የፍጻሜ ሩጫ ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት በሪሁ አረጋዊ (7:46.25)በመሮጥ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል ። ኖርዌያዊው አትሌት ጄኮብ ኢንገርብሪግስተን በሪሁን ቀድሞ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው ከአንድ ሰከንድ ባነሰ 16 ማይክሮ ሰከንድ ለጥቂት ቀድሞ ነው ። የአውስትራሊያው ኪይ ሮቢንሰን ሦስተኛ ደረጃ ሲያገን፥ አንደኛ ከወጣው ኖርዊያዊ አትሌት የተቀደመው በአንድ ሰከንድ ብቻ ነበር ። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ቢንያም መሐሪ እና ጌትነት ዋለ ኤርትራዊው ዳዊት ሠዓረን ከመሀል አድርገው 9ኛ እና 11ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቅቀዋል ። የጀርመኑ ሣም ፓርሶናስ 12ኛ ደረጃ አግኝቷል ።
በትናንትናው የ800 ሜትር የሴቶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት ንግሥት ጌታቸው ሁለተኛ በመሆን ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች ። የገባችበት (1:59.63) የግሏ ምርጥ ሰአት ሁኖ ተመዝግቧል ። በውድድሩ ከፍተኛ ቅድመ ግምት አግኝታ የነበረው የአምና ሻምፒዮና ጽጌ ዱጉማ (2:04.76) ስድስተኛ በመሆን አጠናቃለች ። የ800 ሜትር ርቀት የፍጻሜ ውድድሩን አሸንፋ (1:58.40) የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው የደቡብ አፍሪቃዋ ሯጭ ፕሩደንስ ሴክጎዲሶ አሸንፋለች ። የፖርቹጋሏ ፓትሪሺያ ሲልቫ (1:59.80) በሦስተኛ ደረጃ የነሐስ ተሸላሚ ሁናለች ።
በአጠቃላይ የሜዳሊያ ሠንጠረዥ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው ዩናይትድ ስቴትስ ናት ። 6 የወርቅ 4 የብር እና 6 የነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 16 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች ። ተከታዩዋ ኖርዌይ በ 3 የወርቅ እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 4 ሜዳሊያዎች ነው የሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው ። ከአፍሪቃ የሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ መግባት የቻሉት፦ ደቡብ አፍሪቃ እና ቡርኪና ፋሶ ብቻ ናቸው ። ደቡብ አፍሪቃ በአንድ የወርቅ እና በአንድ የነሐስ በድምሩ ሁለት ሜዳሊያዎች 11ኛ ደረጃ አግኝታ አጠናቃለች ። ቡርኪናፋሶ በአንድ ብቸኛ የነሐስ ሜዳሊያ እንደ ጀርመን ሁሉ የ27ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች ። ሉክዘምበርግ፤ ፖርቹጋል እና ዩክሬንም በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ ደረጃቸው እንደ ቡርኪናፋሶ እና ጀርመን 27ኛ ነው ። ኬንያ ከሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውጪ ናት ።
እግር ኳስ
ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሞሮኮ ውስጥ ከግብጽ ጋር ተጋጥመው 2 ለ0 የተሸነፉት ዋሊያዎቹ ዛሬ ማታ እዛው ሞሮኮ ውስጥ ከጅቡቲ ጋር ይጋጠማሉ ። ግብፅ በ13 ነጥብ ለዓለም ዋንጫ ማለፏን ከወዲሁ አረጋግጣለች ። በዐርቡ ግጥሚያ ሁለቱን ግቦች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ያስቆጠሩት የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሣለህ እና አህመድ ሣይድ ናቸው ። እስካሁን በምጀርመንድቡ እያንዳንዱ ቡድን አምስት ጨዋታዎችን አከናውኗል ። ኢትዮጵያ በ3 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ናት ። ዛሬ የምትገጥማት ጅቡቲ በአንድ ብቸኛ ነጥብ የመጨረሻ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። ሴራሊዮን በ8 ነጥብ ሦስተኛ፤ እንዲሁም ጊኒ ቢሳዎ በስድስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ።
በአውሮጳ የኔሽንስ ሊግ እግር ኳስ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ የጀርመን ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈ ። ትናንት ማታ በሁለተኛው አጋማሽ በጣሊያኖች ጫና የተፈጠረበት የጀርመን ቡድን ተጨዋቾች በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከል፥ አስጨንቆ በመጫወት እና ኳስ ሲነጠቁ በእልህ ኳሷን አስጥሎ መልሶ በመቆጣጠር ተሳክቶላቸው ነበር ። የመጀመሪያው አጋማሽ በጀርመን ቡድን 3 ለ0 መሪነት መጠናቀቁ በእርግጥም ለጀርመን ተጨዋቾች የሚገባቸው ነበር ማለት ይቻላል ። ዶርትሙንድ ውስጥ የትናንት በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከልም ሆነ በማጥቃት የጀርመን ቡድን ከረዥም ዘመን በኋላ የተሳካ እንቅስቃሴ ያሳየበት ነበር ። የመጋቢት 8 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በሁለተኛው አጋማሽ ግን አሰልጣኝ ዩሊያን ናገልስማንም አምነው እንደተቀበሉት ቡድናቸው በመከላከል ላይ ማተኮሩ ለጥቃት ዳርጎታል ። ጣሊያኖች በአንፃሩ ተጠናክረው በማጥቃት ላይ አተኩረው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት ። ያም ወደ ውጤት ተቀይሮ ጨዋታው ሦስት እኩል ተጠናቋል ። በደርሶ መልስ የ5 ለ4 ውጤት የጀርመን ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ ችሏል ።
በመጀመሪያው አጋማሽ ጣሊያኖች ላይ ሁለተኛው ግብ የተቆጠረው በተጨዋቾቹ አሳፋሪ ድርጊት ነበር ። የ15 ዐመቱ ኳስ አቀባይ ኖኤል ዑርባኒያክ ለዮሹዋ ኪሚሽ የማእዘን ምቱን ቶሎ እንዲመታ በፍጥነት ኳስ በማቀበል ሁለተኛዋ ግብ እንድትቆጠር አስተዋፅኦ አድርጓል ። ኳስ አቀባዩ ኳሷን ከማቀበሉ ጥቂት ቀደም ሲል የጀርመን ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገር ያሻማትን ኳስ አጥቂው ቲም ክላይንዲንስት በጭንቅላት ገጭቶ ግብ ጠባቂው ጂያንሉጂ ዶማ ሩማ በድንቅ ሁኔታ አጨናግፎ ከግቡ ጀርባ ኳሷን ይልካል ። ከዚያም ጂያንሉጂ ዶማሩማ የማእዘን ምት መሰጠቱን ዘንግቶ እንዴት ኳሱን አስመታችሁ በሚል ከተከላካዮች ጋር ለመጨቃጨቅ የግብ ክልሉን ጥሎ ወደፊት ይሄዳል ። ከኋላው ያሉትን ዮሹዋ ኪሚሽ እና ጃማል ሙሳይላን አላስተዋለም ።
የጀርመን ቡድን ንቃት
በዐይን እይታ ብቻ የተግባባው ኳስ አቀባዩ ቶሎ ኳሷን ለዮሹዋ ኪሚሽ ይወረውርለታል፥ ዮሹዋ ኪሚሽ ለጃማል፥ ግብ ጠባቂውም ተከላካዮችም ከጭቅጭቃቸው ሳይወጡ እና ሳይነቁ ጃማልም ኳሷን ከመረብ ያሳርፋል ። እን ዶማሩማ ዞር ሲሉ ግቡ ተቆጥሯል ። የጃማል ሙሳይላ፤ ዮሹዋ ኪሚሽ እና የኳስ አቀባዩ ኑኤል የጋራ ጥረት የታከለባት ግብ ልትባል ትችላለች ። ለቅፅበት ተዘናግተው ጭቅጭቅ ላይ ማተኮራቸው ጣሊያኖችን ጉድ አድርጓቸዋል ። የጀርመን ተጨዋቾች በተለይ ከረፍት በፊት በተገኘው አጋጣሚ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣታቸውን ያስመሰከሩበት ግጥሚያ ነበር ። ዮሹዋ ኪሚሽ ከጣልያን ጋር በነበረው የደርሶ መልስ ግጥሚያ በተቆጠሩት እምስት ግቦች በአጠቃላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል ። አንዷን በመልሱ ግጥሚያ ትናንት በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል ።
ከእረፍት መልስ፦ የጣሊያን ቡድን ወደ ማጥቃቱ አጨዋወቱን ቀይሮ ማስጨነቁም ተሳክቶለት ነበር ። የሌሮይ ሳኔ ስህተት ሰበቡም ይኸው አስጨንቆ የመጫወት ስልት ውጤት ነው ። ሌሮይ ሳኔ በቀኝ ክንፈ ጫና ሲበዛበት ኳሷን ባልተመጠነ ሁኔታ ወደ መሀል ለዮሹዋ ኪሚሽ ይልካል፥ ሆኖም ኳሷ የጣሊያን አጥቂ ሞይሴ ኪን እግር ላይ ታርፋለች ። ። በዚያም ሞይሴ ለጣሊያን አስቆጥሮ ቡድኑ ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጓል ። ሁለተኛውንም ይኸው ፀጉረ ጉዱሩው ሞይሴ ኪን አስቆጥሯል ።
ጀርመን ላይ ሁለተኛው ግብ ሲቆጠርም የመጨረሻው ተከላካይ ታህ ወደፊት ከመውጣት ይልቅ ወደኋላ እያፈገፈገ ለመከላከል መሞከሩ ግቡ እንዲቆጠር አድርጓል ። የማታ ማታ የጣሊያን ቡድን ሦስት እኩል ቢወጣም በደርሶ መልስ ግን ጀርመን ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል ። በሩብ ፍፃሜው የዶርትሙንዱ ኤዱና ፓርክ ስታዲየም በደጋፊዎች ደምቃ አምሽታለች ። ሽቱትጋርት እና ሙይንሽን የግማሽ ፍፃሜ ጨወታዎችን ያስተናግዳሉ ።
የጣሊያን ልፋት እና ሽንፈት
የጣሊያን አቻውን በሩብ ፍጻሜው ያሸነፈው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ሙይንሽን እና ሽቱትጋርት ከተሞች ውስጥ በሚካሄዱ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ተሳታፊ ይሆናል ። ሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ለረቡዕ፤ ግንቦት 27 እና በነጋታው ቀጠሮ ተይዞላቸዋል ። የፍጻሜ ግጥሚያው እሁድ ሰኔ 1 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ቱሪን ጣሊያን ውስጥ ይካሄዳል ።
ትናንት በነበሩ የኤሽንስ ሊግ ግጥሚያዎች ፖርቹጋል ከዴንማርክ ጋር ተጫውታለች ። የ40 ዐመቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ለግብ ጠባቂው አስታቅፎታል ። ሆኖም 38ኛው ደቂቃ ለይ ብሩኖ ፈርናንዴሽ በግራ በኩል ያሻማትን ኳስ ክርስቲያኖ በጭንቅላት ሊገጭ ሲዘል የዴንማርኩ ተከላካይ ዮአኺም አንደርሰን ኳሷን አጨናግፋለሁ ብሎ በገዛ መረቡ ላይ በጭንቅላት ገጭቶ አሳርፏል ። 72ኛው ደቃ ላይ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ፖርቹጋል 2 ለ1 እንድትመራ ያደረገውን ግብ ከማእዘኑ በቀኝ በኩል ሰውነቱ አጠማዝዞ በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሯል ። 76ኛ ደቂቃ ላይ ክርስቲያን ኤሪክሰን ዴንማርክን ሁለት እኩል ያደረገችውን ግብ አስቆጠረ ።
መደበኛ 90 ደቂቃው 3 ለ2 ቢጠናቀቅም በደርሶ ምልስ ውጤት ሦስት እኩል በመሆኑ ጨዋታው እንዲራዘም ደቂቃ ተጨምሯል ። በተራዘመው ጨዋታ ፖርቹጋል ዴንማርክን 5 ለ2 ድል አድርጋ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፋለች ። በግማሽ ፍፃሜው ከጀርመን ጋር ትጋጠማለች ።
ስፔን ከኔዘርላንድ በደርሶ መልስ ግጥሚያው 3:3 ተጠናቆ በመለያ ምት ስፔን ኔዘርላንድን 5 ለ4 በአጠቃላይ 8 ለ7 ድል አድርጓል ። የ16 ዐመቱ ላሚን ጃማል ለስፔን ሦስተኛዋን ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል ። ፈረንሣይ ክሮሺያን በመልሱ ጨዋታ በኦሊሴ እና ዖስማን ዴምቤሌ ግቦች 2 ለ0 ብታሸንፍም በደርሶ መልስ 2 ለ2 በመጠናቀቁ ጨዋታው እንዲራዘም ተደርጓል ። በተራዘመው ጨዋታ አሸናፊውን መለየት ባለመቻሉም በመለያ ምት ፈረንሣይ ክሮሺያን 5 ለ4 አሸንፋለች ። የመጋቢት 01 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የፎርሙላ አንድ
በሻንጋይ የቻይና ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ ሽቅድምድም፦ የማክለረን አሽከርካሪዎች አንደኛ እና ሁለተኛ ወጡ ። በትናንቱ ሽቅድምድም ዖስካር ፒያስትሪ አንደኛ በመውጣት 25 ነጥብ ሲያገኝ፤ የቡድን አጋሩ ላንዶ ኖሪስ ሁለተኛ በመውጣት 18 ነጥብ አግኝቷል ። የመርሴዲሱ ጆርጅ ሩሴል በትናንቱም ውድድር እንዳለፈው ሽቅድምድም ሦስተኛ ደረጃ አግኝቶ 15 ነጥብ አግኝቷል ። በ4ኛነት ያጠናቀቀው የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን 12 ነጥብ አግኝቷል ። ሌዊስ ሐሚልተን በፌራሪ ተሽከርካሪው ሳያጠናቅቅ በመቅረቱ የ19ኛ ደረጃ ይዟል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሐይ ጫኔ