የመገናኛ ብዙኃን ያጋለጡት የኬንያ ህገ ወጥ የሰው አካል ዝውውር
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 11 2017
ዋነኞቹ የጀርመን የመገናኛ ብዙኃን ዶቼ ቬለ ፣ ደር ሽፒግል እና ዜድ ዲ ኤፍ በጥምረት ለወራት ያደረጉት የምርመራ ዘገባ አንድ ከምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኬንያ አስደንጋጭ ዜና ይዞ ወጥቷል። የሰው አካል ገበያ እና ዝውውር በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ፈሰስ ተደርገዉበት ፤ ጨካኝ እና ዓለማቀፍ የሰው አካል አዘዋዋሪዎችን ማሳተፉ በርግጥ ጉዳዩ ለኬንያ እና ኬንያውያን ብቻም ሳይሆን ለመላው አፍሪቃ አስደንጋጭ ሆኗል።
የህይወት ውጣ ውረድ ያደከመው የሃያ ሁለት ዓመቱ አሞን ኪፕሩቶ ሜሊ ኩላሊቱን በመሸጥ አዲስ እና የተሻለ ኑሮ ለመጀመር መንገዱን ያማትራል። ከኮቪድ 19 ወረርሺኝ በኋላ በምእራብ ኬንያ ውስጥ በምትገኝ መንደር ውስጥ የሚኖረው ወጣት በርግጥ ሕይወት ፈተና ሆናበታለች። ከአንዱ ሥራ ወደ ሌላው ተፍ ተፍ ብሏል ። የመኪናድለላ ስራ ሞክሯል፤ በግንባታ እና በሌሎች በሌሎችም የስራ መስኮችም ቋሚ ገቢ ለማግኘት እንዲሁ ሲታገል ቆይቷል።
ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተቆጣጣሪ ም/ቤት
ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ከጓደኛው የሰማው እና ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ በአቋራጭ የሚያልፍበት ዜና ለአፍታም ቢሆን እፎይታን ሰጥቶታል። አንዱን ኩላሊቱን በመሸጥ እስከ 6 ሺ ዶላር ድረስ ማጋበስ እንደሚችል የሰማው አሞስ ህይወቱ በተስፋ ተሞላች ። በአንድ ጀምበር ሀብት የቸበጠ የመሰለው ወጣቱ ነገር ግን ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ ፤ ከደብዛዛ ብርሃን ወደ ጨለማ እየተጓዘ መሆኑን አልተረዳም ነበር።
ዶቼ ቬለን ጨምሮ ዋነኞቹ የጀርመን የመገናኛ ብዙኃን ወራት በወሰደው የትብብር የምርመራ ዘገባቸው የሰው አካል ሻጭ እና ገዢዎች እንደምን አድርገው ኬንያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ ከሚደርጉት ግብይት ዓለማቀፋዊ ትስስር በፈጠሩ ድርጅቶች አማካኝነት ባህር አሻግረው ጀርመን የሚያደርሱበትን ሂደት ተከታትለው ደርሰውበታል። የመገናኛ ብዙኃኑ ለምርመራ ዘገባቸው ሐኪሞችን ጨምሮ ከዚሁ ጉዳይ ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸውን ሰነዶች አገላብጠዋል፤ አስተንትነዋል።
ይህ ሕይወት ፈተና የሆነችባቸው ወጣቶች ሀብት ኖሯቸው ጤና ለራቃቸው አዛውንት መስዋዕት የሚሆኑበት እውነታ ነው።
ወጣቱ አሞን ከጓደኛው ባገኘው መረጃ ተማርኮ ኩላሊቱን ሸጦ በሺ የሚቆጠር ዶላር በእጁ ለማስገባት በደረሰበት ስፍራ ያገኙት ሰዎች የነገሩት የሰውነት አካሉን በመለገሱ ምንም እንደማይደርስበት እና ፍጹም ጤናማ እንደሚሆን ነበር።
"በዝርዝር የነገሩኝ ነገር አልነበረም ። በዙሪያዬ የነበሩ ሰዎችን እየጠቆሙኝ ፤ ተመልከት እነዚህ የሰውነት አካላቸውን የለገሱ ናቸው ። እንደምታየው ደህና ናቸው ፤ ወደ ስራቸው ተመልሰዋል።"
ኤልዶሬት ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የቀዶ ህክምና ከተደረገለት እና ካገገመ ጥቂት ቀናት በኋላ አሞን ቃል ከተገባለት ገንዘብ ውስጥ 4ሺ ዶላር ብቻ ነበር የተከፈለው። ይህ ብቻ አልነበረም፤ ሌላ አስከፊ ነገር ገጠመው ጤንነቱ ታወከ በኋላም ራሱን ስቶ ወደቀ።
እናትየው አፋፍሰው ወደ ህክምና ወሰዱት ። ሆስፒታል ደርሰው ምርመራ ከተደረገ በኋላ አንዱ ኩላሊቱ እንዳልነበር ሲነገራቸው እናት የሰሙትን ማመን ነበር የተሳናቸው ። ልጃቸው ኩላሊቱን መሸጡን ባወቁ ጊዜ ግን ጊዜ አላባከኑም በቀጥታ ለፖሊስ ነበር ያመለከቱት።
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና መፍትሄው
በኬንያ የሰውነት አካሉን በመሸጥ አደጋ ላይ የወደቀ አሞን ብቻ አልነበረም ። ልክ እንደር,ሱ ሁሉ በርካታ ወጣቶች በተመሳሳይ መንገድ ተታለው ህይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጡ ጥቂት አይደሉም ።
የጀርመን የመገናኛ ብዙኃኑ ጥምረት በምርመራቸው የኩላሊት ንቅለ ተከላዎችን ከሚያደራጁ ኩባንያዎች መካከል አንዱ "ሜድ-ሊድ" ተብሎ የሚጠራ መሆኑን ደርሰዉበታል። ኩባንያው የገበያ መዳረሻው ካደረጋቸው ሃገራት ጀርመን አንዷ ናት ።
ምክንያቱ ደግሞ በጀርመን በተለይ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን እና በቀላሉ በልገሳ ማግኘት አለመቻሉ ለዚህ በር መክፈቱ ታይቷል።
ሳቢኔ ፊሸር ሜድ ሊድ ወደ ተሰኘው ኩባንያ ሄዳ ለኩላሊት ንቅለ ተከላ በመቶ ሺ የሚቆጠር ዶላር መክፈሏን አምናለች ። በውሳኔዋም ጸጸት እንደማይሰማት ነው የተናገረችው ።
ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ
"የእኔ ራስ ወዳድነት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ኩላሊቱ ያስፈልገኝ ነበር። በህጋዊ መንገድ ነው ውል ያሰርነው ። አሁን ግን ያ ትክክል እንዳልነበር ግልጽ ሆኖልኛል."
የሰውነት አካል በህገ ወጥ መንገድ እየተዘዋወረ መሆኑ መናፈሱን ተከትሎ የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኩላሊት ንቅለ ተከላ በተካሄደባቸው ሆስፒታሎች የመርማሪ ቡድን አሰማርቷል። የምርመራ ቡድኑ በምርመራው በርግጥም የሰውነት አካል ንቅለ ተከላ ከጤና እና ተዛማጅ ጉዳይ ውጭ መከናወኑን አረጋግጧል።
አንድ የምርመራ ቡድኑ ባልደረባ በኤልዶሬት ሆስፒታል ችግር መኖሩን እንደተመለከቱ ነው የሚናገሩት ።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሩዋንዳ
"የውጭ ኃይሎች እጅ እንዳለበት ይሰማኛል። በነዚህ የተደራጁ ወንጀሎች ውስጥ ደግሞ በጣም ኃይለኛ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለዚህ ብዙ የማገጃ መንገዶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ።"
ሜድ-ሊድ በአካል ንቅለ ተከላ 98 በመቶ ስኬታማ እንደሆነ ይገልጻል። ኩባንያው የአካል ክፍሎችን አለመቀበል በግለሰብ ጉዳዮች ላይ ሊከሰት እንደሚችል ቢጸጸትም፤ ስህተት መስራቱን ግን አይቀበለውም። የሁሉንም ለጋሾች ጤንነት በቂ ምርመራ እንደሚያደርግም ይገልጻል።
አጥኚዎች እንደሚሉት በሰው አካል ንቅለ ተከላ ላይ የተሰማሩ ኃይሎች በተለይ በድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ዒላማ ያደርጋሉ ። የኬንያ የደህንነት ጥናት ተቋም ባልድረባ ዊሊስ አኩሞ እንደሚሉት ደግሞ ግለሰቦች የሰውነት አካላቸውን እንዳይለግሱ የሚከላከል ህግ አለመኖሩ ክፍተት መፍጠሩን ነው።
" እዚህጋ የህግ ክፍተት ይታየኛል። ኩላሊታቸውን በገንዘብ በመቀየራቸው እና ይህንኑ የሚከለክል ህግ ስለሌለ በዚህ ምክንያት ሊከሰሱ አይችሉም።"
የወጣቱ አሞን እናት ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ከወሰዱት ወዲህ ፖሊስ ምን ላይ እንዳደረሰው ምንም መረጃ አልደረሳቸውም ።
አሞን ግን አሁን ጤናው ተዛብቷል። ጉልበት የሚጠይቁ ስራዎችን መስራትም አይችልም። በጸጸት የተሞላ ህይወት መግፋትም እጣ ፈንታው ሆኗል።
" ወደ ኋላ መመለስ ብችል ምንም ነገር 'አሺ' አልልም ነበር፣ ኩላሊቴን እንዲያወጡብኝ አልፈቅድም ነበር። ሊያባብሉኝ ቢሞክሩም አልስማማም። ምክንያቱም አሁን ተስፋ እንደቆረጥኩ ነው የሚሰማኝ
ታምራት ዲንሳ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር