የመምህራን የኅብረት ሥራ ባንክ፣ የትግራይ መምህራን ውዝፍ ደመወዝ እና በኮሪደር ልማት መፈናቀል
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 9 2017የኢትዮጵያ የመምህራን ኅብረት ሥራ ባንክ በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ሊጀምር እንደሚችል የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ማክሰኞ ዕለት ተስፋቸውን ገልጸዋል። ብርሀኑ ጉዳዩን ያነሱት የትምህርት ሚኒስቴርን የ2017 የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው። ፕሮፌሰር ብርሀኑ ስለ መምህራን ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ተጠይቀው ሲመልሱ ሥሪያ ቤታቸው በተናጠል የደመወዝ ማሻሻያ ማድረግ እንደማይችል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለመምህራን የምትከፍለው ደመወዝ “በምንም መስፈርት በቂ” እንዳልሆነ ያመኑት ብርሀኑ የተቸገሩ አስተማሪዎችን ለመርዳት የመምህራን የኅብረት ሥራ ባንክ ማቋቋምን እንደ አማራጭ መወሰዱን ገልጸዋል። መንግሥት ለአስተማሪዎች ለቤት መሥሪያ የሚሆን መሬት ቢያቀርብ የሚቋቋመው ባንክ በአነስተኛ ወለድ ብድር የሚሰጥ ይሆናል።
ፕሮፌሰር ብርሀኑ የጠቀሱት ባንክ ዝቅተኛ ደመወዝ ለሚከፈላቸው እና የኑሮ ውድነት ለሚፈታተናቸው የኢትዮጵያ መምህራን ምን ያክል መፍትሔ ያመጣል የሚለው ጉዳይ ግን አነጋጋሪ ይመስላል። ከድር መሐመድ “የባንክ ሱስ የለብንም፤ የደመወዝ ማነስ እንጂ” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል። ሔኖክ ጉቡላ “የመምህራን ባንክ ጥሩ ነዉ” ይበሉ እንጂ “ባንኩን ለማቋቋም የሚያስፈልገዉ የገንዘብ ምንጩ ከየት ነዉ? ከተቋቋመ በኋላ የሰዉ ኃይል ማሟላት፤ በየከተሞች ማዳረስ እንዴት ማድረግ ይቻላል?” የሚሉ ጥያቄዎች አሏቸው።
“ለመተግበር ትንሽ አስቸጋሪ ይመስለኛል” ያሉት ሔኖክ “እንደዚህ አይነት ነገር ዉስጥ ከመግባት ለምን ንግድ ባንክ ጋር አትደራደሩም? ንግድ ባንክ በአነስተኛ ወለድ ለምን ለመምህራን ብቻ ማቅረብ የሚችልበት ሁኔታ አትፈጥሩም? ሲሉ ጠይቀዋል።
በባንክ “አካውንቱ 100 ብር የሌለውን ምስኪን አስተማሪ ስለ ባንክ እና ፋይናንስ የሚያስተምርበት እርባና ቢስ ጩኸት እና ድካም ሊቆም ይገባል” የሚሉት ጸደቀ አባይ “የመምህራን ባንክ የተባለው ነገር ከአጀንዳም ሆነ ከፕሮፖጋንዳ ተለይቶ ሊታይ ይገባል” የሚል አቋም አላቸው። ጸደቀ “ይህንን እውን ለማድረግ የመምህራንን ባንክ ማደራጀት እና ማቋቋም የሀገር ወዳድ መንግሥት እና ሕዝብ ኃላፊነት ነው። ሀገር የሚፈርሰው እውቀት እና እውነትን የሚጠላ ሥርዓትና ትውልድ ሲፈጠር እና ሲበዛ ነው” ብለዋል።
ኤፍሬም “ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፦ ባሉበት” በሚል ያሠፈሩት መልዕክት ግን በዕቅዱ እምነት እንደሌላቸው የሚጠቁም ነው። “ፕሮፌሰር ባንክ መክፈት ከፈለጉ ከባለ ሐብቶች ጋር ተደራጅተው ለምን አይከፍቱም?” ሲሉ የጠየቁት ኤፍሬም “በየመድረኩ ‘የመምህራን ባንክ ልከፍት ነው’ እያሉ የዳቦ ጥያቄያችን ላይ ለምን ያላግጣሉ? የእርሶ ባንክ የእኛን ወቅታዊ እና አንገብጋቢ ጥያቄ ይመልሳል እንዴ?” ሲሉ ጽፈዋል።
“በቂ ክፍያ ነው ጥያቄያችን፤ በቂው ክፍያ ሲኖረን ነው መቆጠብም፤ መበደርም ሆነ አክሲዮን መግዛት የምንችለው” የሚሉት ኤፍሬም “ደመወዙ ለዳቦ ላልበቃው መምህር በስሙ ባንክ መክፈት ምን ማለት ነው?” እያሉ ተቃርኖውን ገልጸዋል።
ደመወዛቸው 10,000 ብር መሆኑን የጠቀሱት ኤፍሬም በአዲስ አበባ ከቤተሰባቸው ጋር ሲኖሩ ለቤት ኪራይ 8,000 ብር እንደሚከፍሉ ገልጸዋል። “ከቤተሰብ እና ከዘመድ ሳልደጎም የምኖርበትን ጥበብ ይንገሩኝ” የሚል ጥያቄ ለትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ አቅርበው “በመበደር እና በመለመን ተስልችቻለሁ፤ ሰዎች እየሸሹኝ ነው” ሲሉ የገቡበትን አጣብቂኝ በግል የፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።
ተስፉ ቶጋ “መምህራን ማስተማር አቁመው፤ ወደ ባንክ ገብተው ስራ በመጀመር ህይወታቸውን እንዲቀይሩ ነዉ አይደል? በጣም ጥሩ ሀሳብ ነዉ” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ተስፉ በኃይል እየተሳለቁ ይመስላል።
የትግራይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ
የኢትዮጵያ መምህራን በደመወዝ ማነስ ወይም በኑሮ ውድነት ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ በበረታው ግጭት እና ጦርነትም ሰለባ ናቸው። በትግራይ ክልል የሚገኙ መምህራን ለምሳሌ የ2014 እና 2015 ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው ሲሟገቱ ቆይተዋል። የትግራይ ክልል የመምህራን ማህበር በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ላይ በትግራይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የከፈተው ክስ በተያዘው ሣምንት መቋጫ አግኝቷል።
ፍርድ ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት ፌድራል መንግሥት እና ሉቴናት ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሚመሩት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የ17 ወራት የመምህራን ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፍሉ ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ጉዑሽ ተስፋሁነኝ “የትግራይ መምህራን ማህበር እንኳን የትግላችሁን ፍሬ አገኛችሁ። በአፋጣኝ እንዲከፈሉ ውሳኔው ለፌደራሉ እና የትግራይ መንግሥት መድረስ አለበት” ብለዋል።
ምዓሾ ብርሀነ ግን “አፈፃፀሙ የሚመለከት የጊዜ ገደብ የለም? ካልከፈሉስ ተጠያቂነት እንዴት ይረጋገጣል? የፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያከብር መንግሥት ያለበት ሀገር ውስጥ ነው እንዴ ያለነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ኪሮስ ገብረዮሐንስ ደግሞ “ያለምንም ድካም ሊሰጠኝ ይገባ የነበረ ደመወዝ፣ የሕግ ሒደት አልፎ የትግራይ መምህራን ማሕበር አመራር አድክሞ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱ ትልቅ ድል ነው። የትግራይ ፍርድ ቤት በዚህ ጉዳይ ያላ ያሳየው ነጻነት ደግሞ ክብር ይገባዋል” ብለዋል።
ኪሮስ “ከአሁን በኋላ ያለው የአፈፃፀም ሥርዓት የሚመለከት ቀጣይ ትግል ያሻል” የሚል አቋም አላቸው።
ሙሉጌታ አብርሐ “ጥሩ ውሳኔ ሰለሆነ በአፋጣኝ ወደ ተግባር መግባት አለበት። የትግራይ መምህራን ማህበር እስካሁን ላደረጋችሁት ትግል በሃገረሰላም አስተማሪዎች ስም እናመሰግናለን” ብለዋል። ክብሮም ገብረኪዳን “ከመምህራን ጎን የወገናችሁ እና የደከማችሁ ምስጋና ይገባችኋል። ማንም ከሕግ በላይ እንደማይሆን አሳይታችኋል” የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “በጣም ትልቅ ብሥራት ነው” የሚሉት ገብረኪዳን ወልደገሪማ የትግራይ መምህራን ማህበርን አመስግነዋል። “የቀሩ ሥራዎች ደግሞ ወደ ተግባር ተሸጋግሮ በአፋጣኝ መምህራን ደመወዛቸው ሊከፈላቸው ጫና መፍጠር፤ አስተማሪዎች ካሳ ሊከፈሉ ይገባል። ምክንያቱም የገንዘብ ዋጋ ከሶስት እና አራት ዓመት በፊት እና አሁን የተለየ ነው” የሚል አስተያየት ሙሉጌታ አብርሐ አስፍረዋል።
የኮሪደር ልማት እና በግዳጅ ማፈናቀል
የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ እያደረገ ለሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሰዎችን በግዳጅ ማፈናቀል በአፋጣኝ እንዲያቆም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠይቋል። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ለፕሮጀክቱ ሲባል “በግዳጅ የተፈናቀሉ ሰዎች ውጤታማ መፍትሔ እስከሚያገኙ” የኮሪደር ልማት ሊቆም እንደሚገባ የጠየቀው ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ነው።
አምነስቲ ጥያቄውን ያቀረበው የኮሪደር ልማት በመጋቢት 2016 በተጀመረባት አዲስ አበባ በተለይ በሁለት ክፍለ ከተሞች ምርመራ ካካሔደ በኋላ ነው። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ባደረገው ምርመራ በቦሌ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ቢያንስ 872 ሰዎች በሕዳር 2017 ብቻ ለኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግዳጅ መፈናቀላቸውን አስታውቋል።
በግዳጅ ከተፈናቀሉት መካከል 254 ሰዎች የ47 የቤት ባለቤት የነበሩ የቤተሰብ አባላት ናቸው። ሌሎቹ 618 ሰዎች ተከራዮች መሆናቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጥናቱ ይፋ አድርጓል። ከተፈናቃዮቹ ውስጥ 114 ሕጻናት እና 13 አረጋውያን ይገኙበታል። በሁለቱ ክፍለ ከተሞች በሕዳር ወር በግዳጅ የተፈናቀሉ ሰዎችን አጠቃላይ ቁጥር ማወቅ እንዳልቻለ የገለጸው አምነስቲ በጥናቱ ከተገለጸው በላይ “እጅግ የላቀ” ሊሆን እንደሚችል እምነቱን ገልጿል።
ሰዒድ በሀሩ “የሚሰሙ ፉጡራን ባይሆኑም፣ የሚሰሩትን በደል አምነስቲ ማስተዋሉ እና ዶይቼ ቬለም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱ ለአምባገነኖቹ ሰላም ቢነሳም ለተጎጂዎች ግን ድምፅ ይሆናል” ሲሉ ጽፈዋል።
አቤል ቦጋለ “መንግሥት ለህዝብ ግድ ከሌለው ቆይቷል። አሁን በመንግሥት እየተበደለ ያለ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው” ብለዋል። ከድር “ተለዋጭ መንገድ እንዲሁም ኮሪደር እያሉ ደሴ ላይ እያስለቀሱን ነዉ” ብለዋል። ማሜ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ “ኮሪደሩ ቀርቶብን ለወጣቱ የሥራ ዕድል እና አንጻራዊ ሰላም ብቻ ነው የምንፈልገው። ስንቱ መሰላችሁ ቤቱ ተበትኖ ግራ የገባው” የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
ዮዳሔ“ኧረ መጀመሪያ ዳቦ የሚያመነጭ ነገር ይገንባ። ብልጭልጩ ለበለጸጉ እና መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ላሟሉት ነው። እኛም እንደርስበታለን” ሲሉ መሆን ይገባዋል ያሉትን አስፍረዋል።
ወንደሰን ብሩ “በግዳጅ የተፈናቀለ የለም። ሀገር ለማልማት ከነበሩበት ቦታ ማዛወር የግድ ነው። ካለበለዚያ እንዴት አርገህ ነው የምትሰራው? አምነስቲ ዓላማችሁ ምን እንደሆነ ስለሚታወቅ ከልማት አታቆሙንም” የሚል አቋም አላቸው። ወንጌል ሚልኪያስ “ይህ መሰረተ ልማት እኮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈልጎ እና አምኖበት እየሰራ የለው ሥራ ነው። ደግሞም ከጉዳቱ ጥቅሙ ይበልጣል” ሲሉ ጽፈዋል።
ሐሚድ ሰዒድ “ልማት አቁም የሚል ድርጅት በአሁኑ ሰዓት መኖሩ ይገርማል። ለሚፈናቀሉት ቦታ እና ቤት መሥሪያ ገንዘብ መንግስት መስጠት አለበት እንጂ ልማት አይቆምም። ልማት ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው” የሚል አስተያየት አስፍረዋል።
ከመጋቢት 2016 ጀምሮ በአዲስ አበባ ለተከናወነው የኮሪደር ልማት የመጀመሪያ ምዕራፍ ብቻ 33 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረው ነበር። ሥራው በተጀመረበት በአዲስ አበባ በመካሔድ ላይ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሁለተኛ ምዕራፍ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የኮሪደር ልማት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እና ሌሎች 65 ከተሞች ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ የመንግሥትን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን በገመገመበት ስብሰባ ላይ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ