የመብት ተሟጋቹ ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥትን ሊከሥ ነዉ
ረቡዕ፣ ግንቦት 27 2017ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ የተባለ አገር በቀል የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይን በማስመልከት መንግስትን ለመክሰስ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ።አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የድርጅቱ ኃላፊ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው ሳይመለሱ ለረጅም ጊዜ በቆዩበት በትግራይ፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ዓለማቀፋዊ እና ብሔራዊ መብቶቻቸው በመጣሱ ለዚህ ቀዳሚው ተጠያቂ መንግስት ነው ብለዋል፡፡
ትኩረት ተነፍጓል የተባለው የአገር የተፈናቃዮች
የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ አሳስቦናል ያሉት የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተስፋለም በርሔ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ ድርጅታቸው መንግስት በትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ ላይ አሳይቷል ባሉት የተለሳለሰ አቋም፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ዝግጅቱን እያጠናቀቁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “ያሳሰበን ጉዳይ በተለይም እኛ በቅርበት መረጃው ያለን ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉና በሽሬ፣ ቴምቢየን እና መቀሌ አከባቢ ያሉ ተፈናቃዮች በተለይም በሽሬ ካምፕ በዚህ አንድ ወር ውስጥ ብቻ አራት ሰዎች በርሃብ እና በማያቧራ ችግር ምክንያት ራሳቸውን ያጠፉ መኖራቸው ነው” ያሉት አቶ ተስፋለም ጉዳዩን መንግስት መፍትሄ እንዲሰጥበት ለማሳሰብም ጭምር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የአገር ተፈናቃዮች ስፋትና የሰብዓዊ መብቱ አሳሳቢነት
በመላው ኢትዮጵያ ትኩረት አድርጎ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ እንደሚሰራ የተገለጸው ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ድርጅት በሶሰረቱ ክልሎች በተለያዩ አከባቢዎች ተፈናቃዮች መኖራቸውን እንዲያምውቅም አመልክቷል፡፡ አቶ ተስፋለም አክለው እንዳሉትም፤ “ሰብዐዊ መብት ድንበር የለውምና በሁሉም አከባቢ ላይ ነው የምንሰራው፡፡ ከአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ደብረብርሃን ለአብነት 24 ሺህ ተፈናቃዮች በችግር ላይ መሆናቸውን እንዲሁም በትግራ ማዕከላዊ ዞን ከ750 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰብናቸው መረጃዎች አሉን” ብለዋል፡፡ በዚህም ክስ የመመስረቱ ውጥን ህገመንግስታዊ መሆኑን የገለጹት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ ኃላፊ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የትም የመኖር መብት እንዳለውና በካምፓላ ኢትዮጵያ የፈረመችው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ደህንነት የመጠበቅና ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ዓለማቀፋዊ ህግ ለክስ ምስረታው መነሻ የሚሆኑ የሰዎች መብት ጥሰት ሲሆኑ በሲቪል ሶሳይቲ የተሰጣቸው እውቅና የተጎዱትን ሰዎች የመወከል ኃላፊነት የሚሰጣቸውም በመሆኑ ክሱን እንደሚመሰርቱ አስታውቀዋል፡፡
እንደ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮችአስተባባሪ (UN-OCHA) የሰኔ 2024 መረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የአገር ውስት ተፈናቃዮች ቁጥር 4.5 ሚሊየን ይገመታል፡፡ ከጎርጎሳውያኑ 2022-2024 ወደ 3.3 ሚሊየን ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው መመለሳቸውን ያስታወቀው የተመድ ኤጄንሲው፤ የእርዳታ አቅርቦት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተዳከመ መምጣቱ ለተፈናቃዮቹ ህይወትን አስከፊ እንደሚያደርግባቸው ያትታል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በፊናው በተለያዩ የሰውሰራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስና በአገር ውስጥ አቅም ጭምር ለችግሮቹ እልባት ለመስጠት እንደሚሰራ ይገልጻል፡፡
የተራዘመው የተፈናቃዮች ሁኔታ በቀጥታ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የሚገናኝ ነው የሚሉት የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች -ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሌም በርሔ አሁናዊ ትኩረታቸውም መንግስት ለጉዳዩ የበዛ ምልከታ እንዲሰጥ ነው ብለዋል፡፡ “እና መነሻችን ሁከት ግርግር ማስነሳት አይደለም፡ መንግስትን ወደ ትኩረት ማምጣትና የተፈናቃዮቹ አስከፊ ህይወት እልባት እንዲያገኝና ደህንነታቸው ተጠብቆላቸው ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ