የመምህራን እገታ በሰሜን ጎጃም
ረቡዕ፣ የካቲት 12 2017በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን፣ ጎንጂ ቆለላ ወረዳ «ኮሬ ገረገራ» በተባለ ትምህርት ቤት ያስተምሩ የነበሩ 14 የሚደርሱ መምህራን በታጣቂዎች ከተወሰዱ አንድ ሳምንት እንደሆናቸው ጓደኞቻቸው ተናግረዋል ። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ታጋቾች ከየካቲት 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ጀምሮ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ አመልክተዋል ።
ከታገቱ መምህራን ምንም ሳይሰማ አንድ ሳምንት ሞላ
መምህራኑ በሥራ ላይ እንዳሉ የካቲት 5 ቀን፣ 2017 ዓም በታጣቂዎች ተወስደው እስላሁን የት እንዳሉና ከአጋቾቹም ሆነ ከታጋቾቹ ወገን እስካሁን የተሰማ ነገር እንደሌለ የታጋች ጓደኞችና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሠዎች አመልክተዋል።
ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታትሉ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዱ ለዶይቼ ቬሌ እንዳሉት እርሳቸው ባላቸው መረጃ ታጋች መምህራን 13 ያክል ናቸው። ቁጥራቸው ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት አስተያየት ሰጪው፣ መምህራኑን ለማስለቀቅ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም እስካሁን ሊሳካላቸው እንዳልቻለ ገልጠዋል፣ ከዚህ በፊትም በጎንጂ ቆለላ ወረዳ 11 መምህራን ታግተው ከተወሰዱ በኋል ገንዘብ ከፍለው መለቀቅቸውን አስረድተዋል ።
ከታጋቾችም ሆነ ከአጋቾች እስካሁን የተሰማ ነገር የለም
መንግሥት መምህራኑን ለማስለቀቅ ጥረት እያደረገ እንደሆነ የገለፁልን ሌላ አስተያየት ሰጪ ሆኖም ከመምህራኑ እስካሁን የተሰማ ነገር የለም ብለዋል ፡፡ አስተያየት ሰጪው አክለውም፣" የታጋቾች ስልክ በአጋቾች ስለሚያዝ መምህራኑን ማግኘት አልተቻለም፣ የታገቱት መምህራን 8ቱ ሴቶች ሲሆኑ 6 ወንዶች ናቸው፣ ሰጎዳ፣ አንጎፌና አዳጎ በሚባሉ በረሀማ አካባቢዎች ነው የሚያዘዋውሯቸው፡፡” ብለዋል ።
በመምህራን ላይ እንግልቱና ውክቢያው መጠን አልፏል የሚሉት መምህራኑ ሠርቶ ቤተሰብ ለማስተዳደር፣ ከቦታ ቦታ ለምንቀሳቀስ ለመምህራን ፈተና እንደሆን ገልጠዋል ። መምህራኑ በማስተማር ላይ እያሉ በታጣቂዎች መወሰዳቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ መምህራን ምን እንዳጠፉ ባይታወቅም እንደጠላት እየተቆጠሩ እንደሆነ አብራርተዋል፣ "ያለችን አንድ አገር ናት፣ ሌላ መሸሻ አገር የለንም የት እንሂድ?” ሲሉ ነው አንድ መምህር የገለፁት ፡፡
ችግሩ በጎጃም ቀጠናዎች ይበረታል
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ሰሞኑን በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ላይ እንዳመለከቱት በመምህራን ለይ ግድያን ጨምሮ እገታዎች እየተፈፀሙ እንደሆነ ተናግረዋል። ችግሩ በተለይ በጎጃም ቀጠናዎችና በደቡብ ጎንደር ዞን እንድሚከፋ አመልክተዋል ። በሌሎች አካባቢዎችም ቢሆን በአንፃራዊ የተሻለ ነገር አለ ቢባልም ችግሩ በሁሉም ቦታ እንዳለ ነው ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የገለፁት ።
ከአማራ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮና ከክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊዎችና ለሰሜን ጎጃም ዞን አሰተዳዳሪ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው የስልክ ጥሪ ስልክ ባለመነሳቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም ። አስተያየት ሰጪዎቹ ለእገታው በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን የፋኖ ታጣቂ ተጠያቂ ያደርጋሉ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ከፋኖ በኩል አስተያየት ለማግኘት ያደረነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም ።